አንቺ አዲስ አበባ
የኑሮ መልክ ሰገባ፡፡
ከአየር ጤና እስከ ኮተቤ፣ ካራ
ከሳሪስ አቃቂ እስከ አውቶብስ ተራ
ከሸጎሌ እስከ ቦሌ
ከአዲስ ከተማ እስከ ቃሊቲ
ከአራዳ እስከ ገርጂ
ከፒያሳ እስከ ሲ ኤም ሲ
ከመርካቶ እስከ ጉለሌ
ከሀያ ሁለት እስከ ቀጨኔ
እንደምን አለሽ?
እንደምን ከረምሽ? እንደምን ባጀሽ?
ከዶሮ ማነቂያ እስከ ጨርቆስ
ከእሪ በከንቱ እስከ ቂርቆስ
ከፈረንሳይ እስከ ጃል ሜዳ
ከኮልፌ እስከ ሽሮ ሜዳ
ከመገናኛ እስከ ካዛንቺስ
ከመስቀል አደባባይ እስከ ሜክሲኮ
ከለገሀር እስከ አስኮ
ከአራት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ
ከሚኒልክ እስከ አምስት ኪሎ
ከንፋስስልክ እስከ ልደታ
ከአምባሳደር እስከ ቀበና
እንደምን አለሽ?
እንደምን ከረምሽ?
እንደምን ባጀሽ?
ደህና ብትሆኚ አለሽ
ደህና ባትሆኚም ያው አለሽ
ዘመን ይቀየር እንጂ፣
ተዋናዮች ይለዋወጡ እንጂ
አንቺ ወዴት ትሄጃለሽ፡፡
አንቺ አዲስ አበባ
የህይወት መልክ ሰገባ፡፡
ተፈትሎ የማያልቅ ጎፍላ
ታጥቦ የማይጠራ ሽንፍላ፡፡
የደላው በውልውል መኪና የሚፈስብሽ
ነባሩ የዛገ ክብሩን ለማስጠበቅ በአሮጌ
ዲኤክስ የሚንኮረኮርብሽ
ምስኪኑ በአውቶብስና ባቡር ተፋፍጎ ላቡን
እየጠረገ የሚባዝንብሽ
ባለረብጣው ሰማይ ጠቀስ ፎቅ
የሚገትርብሽ
ለፍቶ አዳሪው በደሳሳ ጎጆ የሚጠቀለልብሽ
ስንቱን ቻልሺው?
ስንቱን በጉያሽ ሸጎጥሺው?
ወይ አዲስ አበባ
የህይወት መልክ ሰገባ፡፡
በአራት በአምስት በስድስት ኪሎ
ተማሪና አስተማሪ እንደ ጉንዳን
ተጥመልምሎ
ሲሄድ ሲመላለስ ሲርመሰመስ
መጓዝ እንጂ የትም ላይደርስ
ስራ አጡ ማስታወቂያ ለማንበብ ወረቀት
ባየበት
አንገቱ ሲቅለሰለስ
ወይ አዲስ አበባ
የህይወት መልክ ሰገባ፡፡
በመርካቶ ገበያ ሁሉ የሚቸረቸርብሽ
የሚሸጥብሽ፣ የሚለወጥብሽ፣ የሚዘረፍብሽ
አንዱ በደስታ ሲፍለቀለቅ ሌላው በአርምሞ
የሚያለቅስብሽ
ነጋዴው፣ የቀን፣ የመንግስት ሰራተኛው፣
ደላላው
ለማኙ፣ ሾፌሩ፣ ወያላው፣ ጀዝባው
በዶላር በፓውንድ ሸብረብ የሚለው
አውደልዳዩ፣ የሚሰራው፣ የማይሰራው
አንበጣው፣ በጉ፣ ተኩላው
በከርስሽ የታጨቀብሽ
በልቶ ወይም ቀምሶ የሚጋደምብሽ
አንቺ አዲስ አበባ
የዚህ ሁሉ መጠራቀሚያ የህይወት መልክ
ሰገባ፡፡
ሰሜን ምስራቅሽን በእንጦጦ ተራሮች ከበሽ
በገነገነ የባህር ዛፍ ታጥረሽ
ረጃጅም እግሮችሽን ደቡብ ምእራብ
ዘረጋግተሽ
የሚመጣውን ሁሉ ትከቻለሽ እንጂ ወደ
ሰገባሽ
የገባ መቼ ይወጣል፣ መቼ ትለቂያለሽ፡፡
ሸገር መልከ- ብዙ
ፊንፊኔ ግብረ- ብዙ
አዲስ ህዝበ- ብዙ፣
በሌሊት እየገባሁ ወደ ማይለቀው ጉያሽ
እንጦጦ ላይ ሆኜ በተመስጦ ቁልቁል ሳይሽ
በሰፊ ምድጃ ላይ የተበተነ ረመጥ ትመስያለሽ!
ስንቱን ሆድሽ ይዘሽ ስንቱን ጉድ አፍነሽ
በሰገባሽ ከተሽ ታሽሞነሙኛለሽ
በሰገባሽ ከተሸ ታርመጠምጫለሽ፡፡

