የትካል እግሪ ምትካል ትግራይ (ትእምት/ኤፈርት) ባለአደራ ምክር ቤት አባላት ስብሰባ እንዲጠራ ለምክር ቤቱ ሰብሳቢ ጥያቄ አቅርበዋል። ትእምት በበኩሉ፤ የተጠራ ስብሰባ የለም ሲል ጥያቄውን አስተባብሏል።
የትግራይ የወጣቶች፣ የሴቶች እና የታጋዮች ማሕበራትን ጨምሮ ሌሎች ሶስት የትእምት ምክር ቤት አባል የሆኑ ማሕበራት በጻፉት ደብዳቤ፣ ተቋሙን በበላይነት እንዲመራ ሃላፊነት የተሰጠው የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት መሆኑን አውስተዋል። ምክር ቤቱ የቁጥጥር ስርዓት የመዘርጋት፣ በጀት እና ዕቅዶችን የማጽደቅ፣ የስራ አፈጻጸም የመገምገም፣ የትእምት ሃብት እና ንብረት ግልጽነትና ተጠያቂነት በሰፈነበት መልኩ የመቆጣጠር ስልጣን እንዳለውም ጠቅሰዋል።
“ይሁን እንጂ ባለፉት ሶስት ዓመታት ስለተሰሩ ስራዎች እና አጠቃላይ የተቋሙ ሁኔታዎች የምናውቀው ነገር የለም” ሲሉ ያመለከቱት እነዚሁ ማሕበራት፣ ከዚህ በመነሳት የባለአደራ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ “በአጭር ጊዜ ውስጥ” ስብሰባ እንዲጠሩ ጥያቄ አቅርበዋል። ይሁንና ስብሰባው መቼ መጠራት እንደሚኖርበት በጻፉት ደብዳቤ ላይ አልጠቀሱም።
ይህንኑ ጥሪ ተከትሎ ትእምት (ኤፈርት) ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ “የተጠራ ስብሰባ የለም” ሲል በማሕበራቱ የቀረበውን ጥሪ አጣጥሏል። “የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት ለጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. የስብሰባ ጥሪ እንዳቀረበ የሚገልጽ እና የስድስት ማሕበራት ማሕተም ያረፈበት ደብዳቤ ተመልክተናል” በማለት የገለጸው ትእምት (ኤፈርት)፣ ደብዳቤው እና “ተጠርቷል” የተባለውን ስብሰባ በተመለከተ የትእምት ባለአደራ ቦርድ ምንም የሚያውቀው ነገር እንደሌለ ጠቅሷል።
የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት እና ቦርድ ሰብሳቢ በሆኑት አቶ ቴዎድሮስ ሃጎስ በተፈረመ እና ጥር 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ በተደረገው ደብዳቤ እንደተገለጸው፣ የባለአደራ ምክር ቤቱ ለጥር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. የጠራው ስብሰባ የለም። የትእምት የሕግ መምሪያ በበኩሉ፣ የማሕበራቱ ስብሰባ “ይጠራልን” ጥያቄ የትእምት መመስረቻ ጽሑፍ እና መተዳደሪያ ደንብን “ያልተከተለና ሕጋዊነት የሌለው ነው” ብሏል።
መምሪያው አክሎም፣ የምክር ቤቱን መደበኛ ወይም አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ መጥራት የሚችሉት የትእምት ቦርድ አባላት፣ የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት እና ቦርድ ሊቀ መንበር እና የትእምት ምክር ቤት አባላት መሆናቸውን አመልክቷል። “ከእነዚህ ውጪ በተቋማት ወይም በማሕበራት አማካይነት ስብሰባ አይጠራም” ሲል፣ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል።
በጉዳዩ ዙሪያ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በጻፉት ማብራሪያ፣ በትእምት (ኤፈርት) ስር የሚገኙ ተቋማትን በመጀመሪያ በኮሜርሻል ኖሚኒስ ድርጅት አማካይነት እንዲተዳደሩ ተደርጎ መቆየቱን በማውሳት፣ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ከተቋቋመ በኋላ የትእምት ባለአደራ ቦርድ እና የኢንቨስትመንት ማዕከል ከፌደራል መንግስት ጋር ባደረጉት ድርድር ወደ ቀድሞ ስራቸው መመለሳቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም፣ የትእምት ባለአደራ ምክር ቤት ከተከሰቱ ልዩ ልዩ ሁኔታዎች ጋር ተጣጥሞ እንዴት መስራት እንደሚችል በጥናት እየተመለሰ ያለ ጉዳይ መሆኑን እና ይኸው ጥናት ሲጠናቀቅ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እና የትእምት አመራር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት አቅጣጫ እንደሚቀመጥ አስታውቀዋል።
“ከዚህ አሰራር ውጭ የሚደረግ ማንኛውም እንቅስቃሴ ተቋማቱን አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ መቆጠብ ያስፈልጋል ሲሉ፣ አቶ ጌታቸው ረዳ አሳስበዋል።
በትግራይ ክልል የተከሰተውን የፖለቲካ ውጥረት ተከትሎ፣ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካዔል በሚመራው የህወሓት ቡድን እና በአቶ ጌታቸው ረዳ በሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር መካከል ፍትጊያዎች እንደሚስተዋሉ የሚታወቅ ሲሆን፣ በትእምት ውስጥ የተከሰተው ጉዳይም ከዚህ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የክልሉን ፖለቲካ የሚታዘቡ አካላት አስተያየታቸውን እየሰጡ ነው።
ትእምት በ1987 ዓ.ም. የተቋቋመ ሲሆን በስሩ በተለያዩ ዘርፎች የተሰማሩ 17 ድርጅቶችን አቅፎ ይዟል። ተቋሙ በሰሜኑ ጦርነት ወቅት አጠቃላይ ንብረቱ ታግዶ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን፣ በኋላ ላይ በኮሜርሻል ኖሚኒስ አማካይነት እንዲተዳደር መደረጉ የማይዘነጋ ነው።
Published in
ዜና