Thursday, 30 January 2025 20:54

የህንድ የልዑካን ቡድን ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታልን ጎበኘ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)
• ሆስፒታሉ ከህንድ ሆስፒታሎች ጋር በትብብር ሊሰራ ነው
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቴዎስ ሣልሳዊ የህንድ ማላንካራ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መልዕክተኛ፣ የልዑካን ቡድን፣ ሜትሮ ፖሊታን ማር ዩልዮስና ፋዘር ጆሲ ጃኮብ በዛሬው ዕለት ጠዋት ረፋድ ላይ የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታልን ጎብኝተዋል፡፡
የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ብርሃን ተድላ በጉብኝቱ መርሐ ግብር ወቅት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ከህንድ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር መቀራረቡ በተለይ ከፍተኛ ህክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለማድረግ ሆስፒታሉ ያለውን ራዕይ ለማሳካት የሚረዳ ነው።
የኢትዮ-ኢስታንቡል ጠቅላላ ሆስፒታል፤በቴክኖሎጂ በታገዙ ዘመናዊ የህክምና መሳሪያዎችና ከፍተኛ ልምድ ባካበቱ ስፔሻሊስትና ሰብ-ስፔሻሊስት ባለሙያዎች በመታገዝ፣ ዜጎቻችንን ለህክምና ወደ ውጭ አገር በመጓዝ የሚያወጡትን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪና እንግልት ለማስቀረት እንዲሁም ወደ ውጭ አገር የሚያስኬዱ ሕክምናዎችን በሀገር ውስጥ ለመስጠት አልሞ የሚንቀሳቀስ መሆኑ ተነግሯል፡፡
በዋናነትም ሆስፒታሉ በአዋቂና በህፃናት የልብ ቀዶ ህክምና ላይ የተሰማራ የሕክምና ተቋም ስለመኾኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አብራርተዋል። በተጨማሪም፣ የደረትና የሳንባ ቀዶ ጥገና ሕክምና፥ የጭንቅላትና ህብለሰረሰር ህክምና፥ የነርቭ ህክምና፥ የኩላሊት እጥበትና ህክምና፥ የአጥንት ቀዶ ሕክምና እና ጠቅላላ ህክምና ይሰጣል ተብሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት ለልብ ሕሙማን ህፃናት ያለ ክፍያ የቀዶ ህክምና በመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ብርሃን ገልፀዋል። በዚህ ረገድም እስካሁን ድረስ ከ60 በላይ ለሆኑ የልብ ህሙማን ሕፃናትና አዋቂዎች ያለክፍያ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት መስጠቱን ጠቅሰዋል።
የህንድ ኦርቶዶክስ የፓትያርኩ ተወካይ በጉብኝቱ ወቅት ባዩት ሁሉ መደሰታቸውን ገልፀው፤ ከሆስፒታሉ ጋር በትብብር መሥራት የእነሱም ፍላጎት መሆኑን ተናግረዋል።
በአገራቸው ህንድ አራት ሆስፒታሎች ላይ በቦርድ አባልነትና ሊቀመንበርነት እንደሚያገለግሉ የገለጹት ተወካዩ፤ ኢትዮ ኢስታንቡል ሆስፒታል ከእነዚህ ተቋማት ጋር አብሮ የሚሰራበትን ሁኔታ እንደሚያመቻቹ ጠቁመዋል፡፡ እዚህ የማይሰጡ ህክምናዎችን እሳቸው ከሚያስተባብሯቸው ሆስፒታሎች ጋር አብሮ እንዲሰራ በማድረግ፣ ድጋፍ እንዲያገኝ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉም ነው ቃል የገቡት፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
Read 609 times