ቅድመ ታሪክ
ማግባት ምፈልገው
አሪፍ ገንዘብ ያለው
ምርጥ ቪላ ያለው
ሐብታም ነጋዴ ነው ማለትሽ መልካም ነው።
በተዘዋዋሪ
እንደዚህ ዓይነት ሐሳብ
ሊፈጠር “ሚችለው ከቆንጆ ሴት ላይ ነው .....
ይህ ማለት ምንድ ነው?....
እንዲህ ዓይነት ሐሳብ በብዛት ሚሰማው
በየቡና ቤት ነው።
ስለዚህ .....
በዛም አለ በዚህ
አንቺም በውበትሽ የምትፈልጊው
የቡና ቤቷም ሴት የምትፈልገው
ቪላና ገንዘብ ነው።
ታዲያ በዚህ አገር - የፍቅር ማደርያው የትኛው ልብ ነው?
(ከኤፍሬም ሥዩም፤ “ፍቅር እዚህ ቦታ ፈገግ ብሎ ነበር” ከተሰኘው መድበል)
****
ጭር ያለውን ሰፊ ሜዳ የመረጥኩት፣
ለመሮጥ ሳይሆን ለዕረፍት፣
በኑሮ ላይ የሸፈትኩት፣
ራሴ መንፈስ ውስጥ ለመተኛት፡፡
ከእንግዲህ---፤ ባዶ አዳራሽ ውስጥ ቦታ ስትመርጪ.
በድካም ሰዓት ጥግ ስታጪ፣
አስታውሺኝ፣
ጥጉ እኔ ነኝ፡፡
ያልተቀመጥሽበትም ወንበር፣
በሃዘን ሰዓት ትንሽ ፈገግታ ስትሰሚ፣
በጨለማ ውስጥ የሚያጠራጥር ቅርጽ
ስታይ፣
አስታውሽኝ፣
ትንሷ ፈገግታ እኔ ነኝ፡፡
የተጠራጠርሽውም ነገር፣
ከዕለታት አንድ ቀን ምን አልባትም ሌላ ቀን፣
እታይሽ ይሆናል በጨለማው፣
እሞቅሻለሁም በሚበርደው፡፡
(ከሰዓሊ መስፍን ሀብተ ማርያም)

