Saturday, 11 January 2025 12:10

በኮሬ ዞን በገና ዕለት በተፈጸመ ጥቃት ንጹሃን ዜጎች ተገደሉ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን በገና ዋዜማና በበዓሉ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ የዞኑ ነዋሪዎችና አንድ የመንግሥት ሃላፊ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ። ጥቃቱን የፈጸሙት አዋሳኝ ከሆነው የምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጎርካ ወረዳ፣ ከሬዳ እና ጀሎ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፣ ታሕሳስ 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት ሁለት በግብርና ስራ ሲተዳደሩ የነበሩ ዜጎች ተገድለዋል። ነዋሪዎቹ አያይዘውም፣ አርሶአደሮቹ የተገደሉት በጥይት ተደብድበውና አካላቸው ተቆራርጦ መሆኑንም አብራርተዋል።ሟቾቹ አርሶአደሮች አንታዮ ዦላና አድማሱ አሰፋ የተባሉ ሲሆን፣ ታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የቀብር ስነ ስርዓታቸው መፈፀሙን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። አክለውም፣ “አቶ አንታዮ ዦላ የተገደሉት ታሕሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 11:30 ኬረዳ ቀበሌ ውስጥ ነው። ገዳዮቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ከምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ጋላና ወረዳ፣ የተለያዩ የጦርና ስለታማ መሳሪያዎች ታጥቀው ወደ ኮሬ ዞን ዘልቀው ገብተው ነው። የቡልቶ ጃልደሳ ታጣቂዎች ናቸው።” ብለዋል።“በዚሁ ቀበሌ ጥቃት ከመፈጸም ባሻገር፣ የቤት እንስሳትን ዘርፈዋል” ያሉት ነዋሪዎቹ፣ “አድማሱ አሰፋ ደግሞ ታሕሳስ  29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 6:30 ገደማ ጄሎ ቀበሌ ውስጥ ተገድሏል ” ሲሉ ገልጸዋል። ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ከምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች ጥቃት እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
የዞኑ የሕዝብ ተወካይ የሆኑት አቶ ዘናነም አዱላ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፣ ከ2009 ዓ.ም. አንስቶ ጥቃት መፈጸሙን አጽንዖት ሰጥተው፣ ከ300 በላይ ዜጎች ሕይወታች እንደተቀጠፈ ተናግረዋል። ከባድ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ በታጣቂዎቹ ሲፈጸም መቆየቱን ገልፀዋል።“መንግስት የሕዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ቸልተኝነት አሳይቷል። ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም” የሚሉት የሕዝብ ተወካዩ፣ “ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ክፍተት አለ” በማለት ያስረዳሉ። በምዕራብ ጉጂ በኩል አልፎ ወደ ዲላ እና ሃዋሳ ለመጓዝ የሚያስችለው መንገድ መዘጋቱን ጠቁመው፣ ይህም በዞኑ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ከመፍጠሩ ሌላ፣ ከመስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጥቃቱ እንዳገረሸ ጠቅሰዋል።አቶ ዘናነም ግጭቱን ለዝርፊያና የኮንትሮባንድ ንግድ የሚጠቀምበት ሃይል እንዳለ የተናገሩ ሲሆን፣ ስለዚሁ ሃይል በግልጽ ከማብራራት ተቆጥበዋል። ታጣቂዎቹ ከብቶችና ሌሎች የቤት እንስሳት እንደሚዘርፉም ተናግረዋል።
የኮሬ ዞን ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ትግሉ ዘብዶስ የጥቃቱን መደጋገም አንስተው፣ “ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋር የጸጥታ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
 ይሁንና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለመግለጽ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

Read 666 times