• በስሙ አደባባይ ለመሰየምና ሐውልት ለማቆም ከከተማ
አስተዳደሩ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ተብሏል
ከ60 ዓመታት በላይ በተወዳጅነት ያቀነቀነው “የትዝታው ንጉስ” ማህሙድ አህመድ፣ በነገው ዕለት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በአድናቂዎቹ በክብር ከመድረክ ይሸኛል።
ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ የመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ጆርካ ኢቨንትስ ኦርጋናይዘር እና ዳኒ ዴቪስ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ የስንብት ኮንሰርቱ ለጋሽ ማህሙድ በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ ነው። በኮንሰርቱም ላይ ተወዳጆቹ ድምጻዊያን ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ አደም መሐመድ፣ ወንዶሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) እና ዜና ሃይለማሪያም ታላቁን አርቲስት አጅበው ያቀነቅናሉ ተብሏል።
አርቲስቶቹ ከጋሽ ማህሙድ በተረፈው ሰዓት ታዳሚን ለማስደሰትና፣ አንጋፋውን ሙዚቀኛ በክብር ለመሸኘት በከፍተኛ ደረጃ እየተዘጋጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡
ጋሽ ማህሙድም “አሳድጎ ለዚህ ክብር ያበቃኝን አድናቂ፣ በተቻለኝና አቅሜ በፈቀደው መጠን በመጫወት አስደስቼ ለመሰናበት ተዘጋጅቻለሁ” ያለ ሲሆን፤ “ሁላችሁም መጥታችሁ ብትሸኙኝ ደስታውን አልችለውም” ሲል ሁሉም እንዲታደም ጥሪ አቅርቧል።
ጋሽ ማህሙድን አጅበው የሚያቀነቅኑት ለምን ወንዶች ብቻ ሆኑ፣ ሴት አቀንቃኞች ለምን አልተካተቱም? በሚል ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ለቀረበው ጥያቄ፣ ከስንብት ኮንሰርቱ አዘጋጆች አንዱ የሆነው ዳኒ ዴቪስ በሰጠው ምላሽ፤ " አስቴር አወቀ እንድትሳተፍ ፈልገን ጋብዘናት ነበር፤ ወደ ውጪ በመውጣቷ ልትገኝ አልቻለችም፤ እኛም የፈለግነው እሷን ነበር፤ አልሆነም" ብሏል።
የአንጋፋውን ሙዚቀኛ የጋሽ ማህሙድ አህመድን የህይወት ታሪክ የሚተርክ መፅሐፍ በትላንትናው ዕለት የተመረቀ ሲሆን፤ በስሙ አደባባይ ለመሰየምና ሐውልት ለማቆም ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል።