ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገና በዓልን አስመልክቶ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይቀርባል፡-
ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን ሕግ ጥሶ ከእግዚአብሔር ጋር የታጣላው ራሱ የሰው ልጅ ነበረ፡፡ ዕርቅን አውርዶ ሰላምን ለማስፈን በረት ድረስ የመጣው ግን እግዚአብሔር ነው፡፡ እንደ ቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ፣ አሸናፊ፣ የሚሳነው አንዳች የሌለ ነው፡፡ ነገር ግን ለዕርቅ እና ለሰላም ሲል ወደ ማይገባው ሥፍራ መጣ፡፡ አሸናፊ ቢሆንም እንደ ተሸናፊ ሆነ፡፡ ዐቅም ቢኖረው እንደ ዐቅመ ቢስ ሆኖ ታየ፡፡ በሁሉ ሀብታም ሲሆን፣ ራሱን ታናሽ አደረገ፡፡ ይህ ሁሉ ለዕርቅና ለሰላም የተከፈለ የታላቅነት ዋጋ ነው፡፡
እግዚአብሔር ለዕርቅ እና ለሰላም ሲል በደካማዋ ከተማ በቤተልሔም፣ በተናቀችው ሥፍራ በበረት መገኘቱ የገባቸውም ያልገባቸውም ነበሩ፡፡ የገባቸው፤ ከሰማየ ሰማያት ወርደው “ሰላም እና ዕርቅ በምድር ይሁን” ብለው ዘመሩ፡፡ የገባቸው፤ ከምሥራቅ ኮከቡን አይተው፣ እጅ መንሻውን ይዘው መጡ፡፡ የገባቸው፤ በረታቸውን ለቅቀው ለድንግል ማርያም እና ለኢየሱስ ክርስቶስ ሰጡ፡፡ የገባቸው፤ የሰማይ መላእክቱን ተከትለው ወደ በረት ሄደው እርቅና ሰላምን አመሰገኑ፡፡