Saturday, 30 November 2024 20:33

በሲቪል ድርጅቶች ላይ የተጣሉ ዕገዳዎች አሳሳቢ እንደሆኑ ተገለጸ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

“እገዳው ከባድ ጫና እየመጣ መሆኑን ጠቋሚ ነው”


ለሰሞኑ በ3 የሲቪል ማህበረሰብድርጅቶች ላይ የተጣለው ዕገዳ ከሲቪል ማሕበረሰብ ዓዋጅ ያፈነገጠ መሆኑ እንደሚያሳስብ “ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች” የተሰኘው ተቋም ገልጿል። ተቋሙ እንደገለጸው፤ ሕጉ በሚያዘው መሰረት ብቻ መርምሮ ለታገዱት የሲቪል ድርጅቶች ተገቢ መፍትሔ እንዲሰጣቸው ጠይቋል።
ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች ባለፈው ሐሙስ ሕዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን፤ በመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)፣ የሕግ ባለሞያዎች ለሰብዓዊ መብቶች እና በስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ በተባሉት ድርጅቶች ላይ የተጣሉ ዕገዳዎች የሲቪል ማሕበረሰብ እንቅስቃሴ “የሚያቀጭጩ ናቸው” ሲል ስጋቱን ገልጿል። በሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሰረት፤ ዓዋጁን እና ሌሎች ሕጎችን ለሚጠቀሱ ድርጅቶች ባለስልጣኑ በጽሑፍ ማስጠንቀቂያ እንደሚሰጥ፣ እንዲህም ባለስልጣኑ በሲቪል ድርጅቶች ላይ ምርመራ በሚያካሂድበት ወቅት ከባድ የሕግ ጥሰት መፈጸሙን ሲያረጋግጥ፣ ጊዜያዊ ዕግድ ሊጥል እንደሚችል መደንገጉን አብራርቷል።
ይሁን እንጂ በታገዱ ድርጅቶች ላይ በዓዋጁ መሰረት ቢሮ ድረስ በመምጣት ባለስልጣኑ ክትትል አለማድረጉን ማስጠንቀቂያ አለመስጠቱን፣ እንዲሁም ምንም ዓይነት ምርመራ አለመጀመሩንና “አስተካክሉ” የተባሉበት መነሻ ሳይኖር፣ ቀጥታ እግድ መጣሉን “ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች” ለመረዳት መቻሉን አትቷል። “መንግስት ዓዋጁን ሳይከተሉ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለሲቪል ማሕበረሰብ እንቅስቃሴ እጅግ የሚጎዳና የሚያቀጭጭ መሆኑን ተረድቶ፣ ጉዳዩን ሕጉ በሚያዘው መሰረት ብቻ መርምሮ ተገቢ መፍትሔ እንዲሰጣቸውና ወደፊትም ተገቢ ጥንቃቄ እንዲደረግ እንጠይቃለን” ሲል ጥሪ አቅርቧል።
የ”ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች” ዋና ሃላፊ አቶ ተስፋዓለም በርሄ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፣ “በእነርሱ ላይ የተጣለው ዕገዳ ለእኛም የማይመጣበት ምክንያት የለም” ብለዋል። አያይዘውም፣ ተቋማቸው መርህን መሰረት በማድረግ በሦስቱ የሲቪል ድርጅቶች ላይ የተጣሉትን ዕገዳዎች መቃወሙን አስታውቀዋል።
“የሲቪል ማሕበረሰብ ድርጅቶች ዓዋጅ መሻሻልን ተከትሎ፣ በሲቪል ድርጅቶች በኩል ጥሩ እንቅስቃሴ ሲደረግና ዕንቅስቃሴያቸውም ሲስፋፋ ነበር” ያሉት አቶ ተስፋዓለም፣ “አሁን ግን ፖለቲካዊ ጫናዎች እየመጡ፣ ብዙ የሲቪል ድርጅት መሪዎች ከአገር ወጥተዋል” ሲሉ ተናግረዋል። በሶስቱም ሲቪል ድርጅቶች ላይ የተጣለው ዕገዳ ከባድ የሆነ ጫና እየመጣ መሆኑንና የመንቀሳቀሻ ምህዳሩ እየጠበበ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ሲሉም ስጋታቸውን አጋርተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ከሰሞኑ ዕገዳ በተላለፈባቸው ሦስት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ እንደሚያስተላልፍ አስታወቋል። ከሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በሚፈጠሩ አንዳንድ ክስተቶች ምክንያት የሲቪል ምህዳሩ “ጠብቧል” ብሎ መደምደም ተገቢ አለመሆኑን የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ በዕገዳው ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

Read 383 times