የብልፅግና አባል ያልሆኑ መምህራን ለፓርቲው የገንዘብ ድጋፍ ተጠይቀዋል
በሲዳማ ክልል፣ ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን፣ ደራራ ወረዳ የሚገኙ መምህራን የጥቅምት ወር ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው ተናግረዋል። መምህራኑ አክለውም፣ በጉዳዩ ዙሪያ ጥያቄ ያነሱ መምህራን ለእስር መዳረጋቸውን አመልክተዋል።
ደራራ ከተማ ውስጥ በሚገኝ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት የሚያስተምሩ አንድ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ መምህር ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፣ በመጀመሪያ መስከረም 27 ቀን 2017 ዓ.ም. የወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊን ጨምሮ ሌሎችም የወረዳው ካቢኔ አባላት መምህራኑን ሰብስበው አነጋግረዋቸዋል። በዚህ መድረክ ላይ ለወረዳው የፓርቲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ የሚውል ገንዘብ ከደመወዛቸው ላይ ተቆራጭ እንዲሆን ለመጠየቅ እንደመጡ ለመምህራኑ መናገራቸውን አውስተዋል።
ይሁንና መምህራኑ ኑሮ እንደከበዳቸውና የሚከፈላቸው ደመወዝ እንደማይበቃቸውና የፓርቲ አባል እንዳልሆኑ፣ በዚህም ግዴታ እንደሌለባቸው ለአወያዮች መናገራቸውን የሚያስረዱት እኚሁ መምህር፣ ከጠዋቱ 3፡00 እስከ ከሰዓት 9፡00 ስብሰባው ቢከናወንም፣ በመጨረሻም መምህራኑ ከአወያዮቹ ጋር ለመግባባት ባለመቻላቸው መድረክ ረግጠው እንደወጡ ጠቅሰዋል። “ስብሰባው የተደረገው በስራ ቀን ሲሆን፣ ትምህርት ቤቱ እንዲዘጋ ተደርጓል” ብለዋል።
በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ መምህራን፣ መስከረም 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ተመካክረው ፊርማ በማሰባሰብ፤ ለወረዳው የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ ከደመወዛቸው ተቆራጭ ማድረግ እንደማይችሉና ለስብሰባ ተብሎ የወረዳው የመንግስትና የፓርቲ አመራሮች ወደ ትምህርት ቤት እንዳይመጡ ጥያቄ ማቅረባቸውን መምህሩ ያብራራሉ። ያሰባሰቡትን ፊርማ ለወረዳው የፓርቲ ጽሕፈት ቤት፣ ለወረዳው ፐብሊክ ሰርቪስ ጽሕፈት ቤትና ለሌሎች የሚመለከታቸው ተቋማት ማስገባታቸውንም አስታውቀዋል።
የወረዳው መምህራን ማሕበር ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ዘውዴ አዲስ አድማስ ከ5 ት/ቤቶች የተውጣጡ 160 መምህራን ፊርማ ማሰባሰባቸውን የገለጹ ሲሆን፣ ከ5 ትምሕርት ቤቶች የተውጣጡ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የተሰበሰበው ፊርማ ለሚመለከታቸው ተቋማት ገቢ በተደረገ በሳምንቱ፣ (ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም.) “መምህራኑ ሳያውቁ ነበር የወረዳው የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ምክትል ሃላፊ ለብቻቸው የመጡት። የመጡትም ከረፋዱ 4፡00 ላይ ሲሆን፣ በዚያ ሰዓት ተማሪዎች ከትምህርት ቤት እንዲወጡ ተደረገ።” ሲሉ የነበረውን ሁኔታ ያስታውሳሉ። አያይዘውም፣ ምክትል ሃላፊው “መጀመሪያ ለክልሉና ለዞኑ ቃል የገባነው እናንተን ተማምነን ነው። ከወረዳው ሰራተኞች ስድስት ሚሊዮን ብር እንደሚሰበሰብ ቃል ገብተናል። ያንን ቃል እኛ ምን እናድርገው?” ብለው መናገራቸውን ገልጸዋል።
መምህራኑ ግን እነርሱ በይፋ ቃል እንዳልገቡ፣ ቃል የገቡት አመራሮቹ እንደሆኑና ራሳቸው አመራሮቹ እንዲወጡት በማስታወቅ፣ ኑሮ እንደከበዳቸው መግለጻቸውን የሚናገሩት መምህሩ ይናገራሉ። “ደመወዜ በወር 4 ሺሕ 700 ብር ነው። አብዛኛው መምሕር ከእኔ የደመወዝ መጠን በላይ አያገኝም። የተወሰኑት ከፍ ያለ ደመወዝ ካገኙ ደግሞ፣ 5 ሺሕ 300 ብር ነው።” በማለት ተናግረዋል።
ከደመወዛቸው ላይ ለሕንጻው ግንባታ 100 ፐርሰንት እንዲቆረጥ በወረዳው አመራሮች እንደተጠየቁ ገልጸው፣ በ10 ወር ጊዜ ውስጥ አብዛኛው ደመወዛቸው ለግንባታ ስራው ገቢ እንደሚደረግም ለማወቅ መቻሉን መምሕሩ ጠቅሰዋል።
በግልጽ ከደመወዛቸው ተቆራጭ ገንዘብ መወሰዱን የተቃወሙ ሦስት መምህራን በፖሊሶች ታስረው ሐዋሳ እንደሚገኙ ያመለከቱት እኚሁ መምህር፣ “ከደመወዛቸው የተወሰነው ገንዘብ ለፓርቲ ጽሕፈት ቤት ግንባታ እንዲውል በፍራቻ የፈረሙት መምህራን ቁጥር 17 ነው።” ብለዋል። ይህን ተከትሎ ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. ለፈረሙ መምህራን ብቻ ደመወዝ ገቢ ሲደረግ፣ ደመወዝ ያልተከፈላቸው መምህራን ለምን እንዳልተከፈላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ መጀመሪያ ወረቀቱን እንዲፈርሙ ቅድመ ሁኔታ እንደቀረበላቸው ለማወቅ ተችሏል።
የወረዳው መምህራን ማሕበር ለምን ለተወሰኑ መምህራን ደመወዝ እንዳልተከፈለ ጥያቄ ሲያቀርብ፣ ተመሳሳይ ምላሽ እንደተሰጠው መምህሩ አስታውቀዋል። የማሕበሩ ሰብሳቢ አቶ ዘላለም ስለተሰጣቸው ምላሽ ሲናገሩ፣ “ችግሩ እንዲቀረፍ ጥረት ብናደርግም፣ የመንግስት አመራሮች ግን ለመተባበር ፈቃደኞች አይደሉም” ብለዋል። ደመወዝ በወቅቱ ስላልተከፈለው በተፈጠረበት አዕምሯዊ ጫና ምክንያት ተሾመ ታደሰ የተባለ መምህር ራሱን ማጥፋቱን የሚናገሩት አቶ ዘላለም፣ የወረዳው አመራሮች ከመምህራኑ የህዳር ወር ደመወዝ ተቆራጭ ለማድረግ ማሰባቸውን አስታውቀዋል። ይህንን ጉዳይ እስከ ፌደራል ተቋማት ድረስ ለመውሰድ እርሳቸው የሚመሩት ማሕበር ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ የሲዳማ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካልንም።