Saturday, 30 November 2024 20:23

ሕብረት ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 74.65 ቢ.ብር መድረሱን አስታወቀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

- 27ኛውን ዓመታዊ የባለአክሲዮኖች ጉባኤ አካሂዷል

ሕብረት ባንክ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 74.65 ቢሊዮን ብር ማድረሱን አስታወቀ። ባንኩ ይህን ያስታወቀው ከትላንት በስቲያ ሀሙስ ህዳር 19 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል 27ኛውን የባለአክሲዮኖች ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ባካሄደበት ወቅት ነው።
የቦርድ ሰብሳቢዋ ሳምራዊት ጌታመሳይ (ኢ/ር) ባቀረቡት የባንኩ አመታዊ አፈፃጸም ሪፖርት፣ በተለይ ከድህረ ኮቪድ በኋላ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችንና በባንክ ዘርፉ ላይ ያሳረፉትን ተፅዕኖ አብራርተው፣ ሕብረት ባንክ ዓለም አቀፍም ሆነ የሀገር ውስጥ ተፅዕኖዎችን ተቋቁሞ አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።
የቦርድ ሰብሳቢዋ አክለውም፤ በሀገር ውስጥ ያሉ ተግዳቶችን የዘረዘሩ ሲሆን፤ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተከሰተው አለመረጋጋት፣ በሰዎችና በሸቀጦች እንቅስቃሴ ላይ የፈጠረው ጫና በፋይናንስ ሴክተሩና በአጠቃላይ በኢኮኖሚው ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን አውስተው፣ ብሄራዊ ባንክ ለንግድ ባንኮች የሚሰጠው የአስቸኳይ ጊዜ ብድር የወለድ ምጣኔ መጨመር፣ የብድር እድገቱን የሚገድብ መመሪያ መውጣቱ፣ የልማት ባንክ ቦንድ ግዢ ግዴታዎች፣ የውጪ ምንዛሬ እጥረትና ሌሎችም የውጭና የውስጥ ተፅዕኖዎች በባንክ ዘርፉ ላይ ጫና እንደፈጠሩ ተናግረዋል።
ሕብረት ባንክ በእነዚህ ሁሉ ጫናዎች ውስጥ ቢያልፍም፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት አጠቃላይ የተቀማጭ መጠኑን 74.65 ቢሊዮን ብር ማድረሱን የገለጸ ሲሆን ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ10.11 ቢሊዮን ብር ወይም የ15.66 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱንና አጠቃላይ የባንኩ የብድር መጠንም ከወለድ ነፃ ፋይናንስን ጨምሮ በ15.09 በመቶ በማደግ 68 ነጥብ 89 ቢሊዮን መድረሱ ተገልጿል።
በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ባንኩ ከታክስ በፊት 3.08 ቢሊዮን ትርፍ ማስመዝገቡን የገለፁት የቦርድ ሰብሳቢዋ ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃጸር የ22.57 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱን ተናግረዋል።
በዚሁ በተጠናቀቀው ዓመት ባንኩ በ60 ቀናት ውስጥ ከ2 ነጥብ 22 ቢሊዮ ብር ወይም በ46 ነጥብ 44 በመቶ በማሳደግ 7 ቢሊዮን የተከፈለ ካፒታል እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል። ከላይ በተዘረዘረው የባንኩ አመርቂ ውጤት መሰረት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ሙሉ በሙሉ የተከፈሉ አክሲዮኖች ላይ ባንኩ የ24 ነጥብ 08 በመቶ ትርፍ ድርሻ እንዲከፈል ቦርዱ ምክረ ሀሳብ ማቅረቡን ሰብሳቢዋ አክለው ገልጸዋል። ባንኩ በሰራው አመርቂ ስራ የሰው ሃብቱን ከ9ሺ በላይ ያደረሰ ሲሆን የቅርንጫፎቹን መጠን ደግሞ ወደ 499 ማሳደጉ ተገልጿል።
ባንኩ ማህበራዊ ኃላፊነቱን በመወጣት በኩል ከፍተኛ ሥራ የሰራ ሲሆን መስፈርቱን ለሚያሟሉ 19 የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ከ20 ሚሊዮን ብር በላይ መለገሱን የቦርድ ሰብሳቢዋ ሳምራዊት ጌታመሳይ (ኢ/ር) ገልጸዋል።

 

Read 333 times Last modified on Monday, 02 December 2024 17:11