Thursday, 28 November 2024 17:38

የመጀመሪያው የአትዮጵያ ቡና ፌስቲቫል ሊካሄድ ነው

Written by 
Rate this item
(3 votes)

• 10 ታዋቂ የቡና አምራች ኩባንያዎች በፌስቲቫሉ ይሳተፋሉ

• የኢትዮጵያ ቡና በጃዝ ሙዚቃ ይደምቃል ተብሏል

• 3ሺ ገደማ ጎብኚዎች እንደሚታደሙበት ይጠበቃል

 

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለለት የቡና ፌስቲቫል (ኮፊ ፌስት) የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በሸራተን አዲስ ሆቴል የሚካሄድ ሲሆን፤ በፌስቲቫሉ ላይ አሥር የሚደርሱ ታዋቂ የቡና አምራችና ላኪ ኩባንያዎች ይሳተፉበታል፡፡


የቡና አምራች ኩባንያዎቹ የተለያዩ ዓይነት የቡና ምርቶቻቸውን የሚያቀርቡ ሲሆን፤ ለኤክስፖርት የተዘጋጁ የቡና ምርቶችን ጨምሮ ለሸያጭ ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ የቡና ቀመሳ ሥነስርዓትም ይካሄዳል፡፡


ለሁለት ቀናት የሚካሄደውን የመጀመሪያውን የቡና ፌስቲቫል አስመልክቶ የኹነቱ ጠንሳሾችና አዘጋጆች ዛሬ ጠዋት ረፋዱ ላይ በሸራተን አዲስ ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡


ከፌስቲቫሉ ግንባር ቀደም ስፖንሰሮች አንዱ የሆነው ሸራተን አዲስ ዋና ሥራ አስኪያጅ - በመግለጫው ላይ የተገኙ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የቡና ፌስቲቫል በሆቴሉ መዘጋጀቱ ልዩ ደስታና ጉጉት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ቡና ፌስቲቫል የመካሄድ ዓላማን ያብራሩት አዘጋጆቹ፤የኢትዮጵያን ቡና በሚገባው ልክ ለማክበርና ለማጉላት ነው ብለዋል፡፡ ”እኛ ኮፊ ፌስትን እንደ በዓል ነው የምንቆጥረው፤ቡናችንን የምናከብርበትና የምናጎላበት ታላቅ በዓል፡፡” ሲሉም አስረድተዋል፡፡

እንደ ጀርመን ያሉ አገራት በኦክቶበር ፌስት (ዓመታዊ የቢራ ፌስቲቫል) እንደሚታወቁ የጠቀሱት አዘጋጆቹ፤ ኢትዮጵያም በቡና ፌስቲቫል (ኮፊ ፌስት) መታወቅ አለባት ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡

በአገራችን በየዓመቱ የተለያዩ የቡና ቀመሳ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ያወሱት አዘጋጆቹ፤ ኮፌ ፌስትን ለየት የሚያደርገው ለአምራቾችና ለላኪዎች ብቻ የተዘጋጀ ሳይሆን ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ብለዋል፡፡

”ለዚህም ነው መግቢያውን በነጻ ያደረግነው፤ ማንኛውም የቡና ወዳጅና አፍቃሪ የፊታችን ቅዳሜና እሁድ በሸራተን አዲስ መታደም ይችላል” ሲሉም ጋብዘዋል፡፡


በሁለቱም ቀናት ፌስቲቫሉ በታዋቂ የጃዝ ሙዚቀኞች የሚታጀብና የሚደምቅ ሲሆን፤ ይህም ኹነቱን አይረሴ እንደሚያደርገው ታምኗል፡፡ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያ የቡና ፌስቲቫል፤ ዳሸን ባንክና ሸራተን አዲስን ጨምሮ ሌሎች ስመጥር ድርጅቶች ስፖንሰር ያደርጉታል፡፡


ፌስቲቫሉን ያዘጋጁት ፕሮሎግ ማርኬቲንግ፣ ዩቦራ ኮሙኒኬሽን እና ቢዮንድ ቡና በመተባበር መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 488 times