Saturday, 26 October 2024 19:56

ነጋዴዎች በመርካቶው የእሳት አደጋ ከፍተኛ ዝርፊያ ተፈጽሞብናል አሉ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 11 ቀን 2017 ዓ.ም አመሻሽ ጀምሮ በመርካቶ ሸማ ተራ የደረሰውን የእሳት አደጋ ተከትሎ ከፍተኛ ዝርፊያ እንደተፈፀመባቸው ነጋዴዎች ተናገሩ፡፡
የእሳት አደጋውን እንደ አመቺ አጋጣሚ ተጠቅመው ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ግለሰቦች ሱቆችን እየሰበሩ በመግባት ዘረፋ መፈፀማቸውን ነጋዴዎች ይገልፃሉ፡፡
“እሳት ከሚበላው እኛ ብንበላው ይሻላል” እያሉ በርካቶች ሱቆችን ሰብረው በመግባት ሲዘርፉ እንደ ነበር ተነግሯል፡፡ በመርካቶ ሸማ ተራ የጫማ ሱቅ እንደነበራቸው የገለፁ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ነጋዴ፣ የእሳት አደጋው በተከሰተበት ምሽት ስለተፈፀመው ዘረፋ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል “ቀሪ ንብረቴን ለማዳን ወደ ሱቄ ስገባ፣ ማንነታቸውን የማላውቃቸው ግለሰቦ ሰብረው ገብተው “የአክስታችን ሱቅ ነው፤ አሁኑኑ ውጣልን ብለውኛል” ይላሉ- እኒሁ ነጋዴ፡፡ በዚያው ሰፈር አጠቃላይ ፍተሻ ቢደረግ ብዙ የተሰረቁ ንብረቶ እንደሚገኙ ግምታቸውን የገለፁት እኒሁ ነጋዴ፤ ከዝርፊያ የተረፈ ንብረታቸው በእሳት አደጋው መበላቱን ተናግረዋል፡፡ በዚሁ የእሳት አደጋ ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት እንደወደመባቸውም ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
እዚያው መርካቶ በአስመጪነት የስራ ዘርፍ የተሰማሩ ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሌላ ነጋዴ በቤተሰቦቻቸው የጫማ መደብርና በሌሎች ነጋዴዎች ንብረት ላይ በመኪና ጭምር የታገዘ ዘረፋ መፈፀሙን ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የእርሳቸው የዕቃ መጋዘን በእሳት አደጋ ሙሉ በሙሉ መውደሙን ነው የገለፁት ነጋዴው፤ በአጠቃላይ የ30 ሚሊዮን ብር ንብረት እንደወደመባቸው ተናግረዋል።
“ብዙ ሰው ንብረቱን ለማትረፍ ከሱቅ ወደ ውጭ ሲወረውር ነበር። በዚህም አጋጣሚ እንኳ የተወረወረውን ንብረት አንስተው የሚወስዱ ሰዎች ነበሩ” ሲሉም፣ በአደጋው ወቅት የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል።
ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ በመርካቶ፣ ሸማ ተራ ከተደራጁ የነጋዴ ማሕበራት አመራሮች ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ነጋዴዎቹ ለአዲስ አድማስ ገልጸዋል። በዚህ ውይይት ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በማሕበራቱ ውስጥ አባል የሆኑ ነጋዴዎች በእሳት አደጋው ሳቢያ የደረሰባቸው የንብረት ውድመት ምን ያህል እንደሆነ ለመለየት ጥረት ማድረጋቸው ተጠቁሟል፣ “አብረናችሁ እንሰራለን፣ እናንተን ለማገዝ ከጎናችሁ ነን። እናንተ መስራት በምትችሉበት መልኩ ይገነባል!” ሲሉ ቃል እንደገቡላቸውም ነው የተናገሩት።
መርካቶ ሸማ ተራ በርካታ የቤተሰብ አባላትን የሚያስተዳድሩ ዜጎች የሚሰሩበት አካባቢ እንደነበር የመጠቆሙት ነጋዴዎቹ፣ መንግስት በአፋጣኝ መፍትሔ ሰጥቶ ወደ ስራ እንዲመልሳቸው ጠይቀዋል። ነጋዴዎቹ በነበሩበት አካባቢ እንደገና ተመልሰው መስራት እንደሚፈልጉም ገልፀዋል።
የእሳት አደጋው በደረሰበት ወቅት አብዛኛው ነጋዴ የራሱን ንብረት ለማሸሽ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ የእሳት አደጋው ከፍተኛ ስለነበር ብዙ ንብረት መውደሙን ነው ነጋዴዎች የደተናገሩት፡፡ እሳቱ በርካታ ንብረት ካወደመ በኋላ “ተለቀቀ” የተባለው የእሳት ማጥፊያ ውሃ መጀመሪያ ላይ ተለቅቆ ቢሆን ኖሮ፣ “የአደጋውን መጠን ሊቀንስ ይችል እንደነበር ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል፣ አደጋውን እንደ አመቺ ሁኔታ በመጠቀም የስርቆት ወንጀል የፈጸሙ 33 ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። በአደጋው ጋር በተያያዘ በሰባት ሰዎች ላይ ቀላል ጉዳት ሲደርስባቸው፣ በሁለት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት መድረሱን ተገልጿል፡፡
አደጋውን ለመከላከል የጸጥታና ሌሎች ተቋማት እንዲሁም የአካባቢው ሕብረተሰብ ከፍተኛ ድጋፍ ማድረጋቸው ሲገለጽ፣ የአደጋውን  መንስዔ ለማጣራት የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ ከፌደራል ፖሊስ የፎረንሲክ ምርመራ ቡድን ጋር በመቀናጀት ምርመራ መጀመሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡ አደጋውን ለመከላከልና በአደጋው ምክንያት ሌላ ወንጀል እንዳይፈጸም ብሎም የአደጋ መከላከል ሰራተኞች ተግባራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዲችሉና ተጨማሪ ጉዳት እንዳያጋጥም የመከላከያ ሰራዊት፣ ሪፐብሊካን ጋርድ፣ ብሔራዊ መረጃና ደሕንነት አገልግሎት፣ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ርብርብ ማድረጋቸውን ኮሚሽኑ ያወጣው መግለጫ ያሳያል፡፡

Read 1405 times