Saturday, 12 October 2024 13:09

የቀጠናው ትርምስ ማንን ይጠቅማል? ማንንስ ይጎዳል?

Written by 
Rate this item
(5 votes)

 በዚህ ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ የቀጣናው የዲፕሎማሲ ጉዳዮች መካከል የሦስቱ አገራት - ማለትም ኤርትራ፣ ሶማሊያና ግብጽ - በአስመራ ተገናኝተው መምከራቸው ነው፡፤ ይህ ምክክር ብዙ የዲፕሎማሲና ፖለቲካ ተንታኞችን ትኩረት የሳበው ያለምክንያት አይደለም፡፡ ሦስቱም አገራት ከሞላ ጎደል ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ በመምጣቱ ይመስላል፡፡
የሆርን ኢንተርናሽናል የስትራቴጂክ ጥናቶች ተቋም ዳይሬክተር ሃሰን ካሕንኔጂ፣ ይህንን የሦስትዮሽ ምክክር፤ “አዲስ አበባን በተቃራኒ አቅጣጫ የሚቀናቀን ስብስብ” ሲሉ ይጠሩታል፡፡
 ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ  ጋር በነበራቸው ቆይታ።
እነዚህ አገራት በኢትዮጵያ ላይ  የተቀናቃኝነት ፍትጊያ ማነሳሳት የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ሩቅ ዘመናትን ወደ ኋላ ይጓዛል፡፡ ቀዳሚዋ ተቀናቃኝ ደግሞ  ግብጽ ነች። የዓባይ ተፋሰስ አገር የሆነችው ግብጽ፣ በቅኝ ገዢዎቿ ዘመን የተፈረሙ የውሃ ስምምነቶች ዘንድሮም እንዲከበሩላት ስትሟሟት ትታያለች፤ እንደማይሳካ ብታውቅም፡፡
ከጥንትም ቢሆን ግብጽ፣ ኢትዮጵያ እንዳትለማና የማልማት አቅሟ እንዲሽመደመድ ያልፈነቀለችው ድንጋይ የለም፡፡ የኤርትራ ነጻ አውጪ ንቅናቄ በካይሮ ቢሮ እንዲያገኝ፣ የፕሮፓጋንዳ ልፈፋውን በራዲዮ ሞገድ እንዲያሰራጭ የማመቻቸት ሁነኛ ስራ በወቅቱ የግብጽ መንግስት ተሰርቶ ነበር፤ በ1950ዎቹ አጋማሽና በ1960ዎቹ መጀመሪያ ላይ ማለት ነው።
በኋላም በሓምድ እድሪስ ኣዋተ የተጀመረውን የጀብሐ (የኤርትራ ነጻነት ግንባር) የትጥቅ ትግል ለመደገፍ ዓይኗን አላሸችም፡፡ በአጭሩ ኢትዮጵያ የውስጥ ሰላሟ ተረጋግጦ ፊቷን ወደ ልማት እንዳታዞር የግብጽ የዲፕሎማሲና ትጥቅ-አከል ተጽዕኖ የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሲጀመር፣ እንዲሁም በዓባይ ተፋሰስ ላይ የተለያዩ አነስተኛና መካከለኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ግድቦችን ለመገንባት ኢትዮጵያ ወገቧን አስራ የገንዘብ ድጋፍ ወይም ብድር ስታፈላለግ፣ ግብጽ በይፋም ሆነ በስውር የማደናቀፍ ሥራ ስትሰራ መኖሯ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡
 ዘንድሮም የግብጽ ኢትዮጵያን የማደናቀፍ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል፡፡  የዓባይ ወንዝ ፍላጎቷን፣ የአፍሪካ ቀንድ የበላይነቷን የማረጋገጥ ፍላጎቷን ለማሟላት መውጣት መውረዷ አልቀረም፡፡ የሰሞኑ የአስመራው የሦስትዮሽ ምክክርም የዚሁ ፍላጎቷ መገለጫ ነው፡፡
ሶማሊያም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራት የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ምዕራፍ ጉራማይሌ ነው። አንዴ ሲሰክን፣ አንዴ ሲደፈርስ፤ አንዴ በሰላም አየር ሲታደስ፣ ሌላ ጊዜ በደም አበላ ሲታጠብ ረዥም ዓመታትን አስቆጥሯል። ይልቁንም በ1969 ዓ.ም. የዚያድ ባሬ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ የ”ይገባኛል” ጥያቄ ባነሳባቸው ግዛቶች ወረራ በመፈጸም እስከ ሲዳሞ ድረስ ዘልቋል። በርግጥም፣ ይህ የመተንኮስ ተግባር በዘመነ ደርግ ብቻ ሳይሆን በቀዳማዊ ሃይለስላሴ ዘመነ መንግስትም ጭምር የተስተዋለ መሆኑን ልብ ይሏል።
የሆነው ሆነና ቀደም ያለውና የኋለኛው ዘመን ጦርነቶች በኢትዮጵያ አሸናፊነት ተደምድመዋል። ቀጥለው የመጡት ዓመታት ኢትዮጵያ በሶማሊያ ላይ ዲፕሎማሲያዊ የበላይነትን ተቀዳጅታ ባጅታለች። በተለይም አል ሸባብንና መሰል የሽብርተኛ ቡድኖችን በመዋጋት ረገድ የኢትዮጵያ ሚና አይተኬ ነበር። ይሁንና ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር ባደረገችው የመግባቢያ ስምምነት ምክንያት፣ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ደፍርሶ፣ ግብጽን ወደ ሞቃዲሾ እንድትመጣ በሩን ከፍቷል።
የአስመራው ምክክር ምን ምን ይዘቶችን እንዳካተተ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን በሰፊው እየተነገረ ነው። የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ የግብጽ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ እና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼክ መሃሙድ በአስመራ የሦስትዮሽ ውይይት ሲያደርጉ፣ የተስማሙባቸው ሃሳቦች በአብዛኛው ለሶማሊያ ያደሉ የሚመስሉ ጉዳዮችን አጭቀው ይዘዋል። በተለይ በኤርትራና ግብጽ መካከል ከተነሱ ሃሳቦች መሃል በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የፖለቲካ ምክክር ኮሚቴ ለማቋቋም የተስማሙ ሲሆን፤ በአህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና ጂኦፖለቲካዊ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያግዝ ነው። ይህ ነጥብ የወደፊቱን የሃይል አሰላለፍ ሊወስን እንደሚችል የፖለቲካ ተንታኞች በአጽንዖት ይናገራሉ። ሁለቱም በቀይ ባሕር የወሰን ጠገግ እንደመገኘታቸው መጠን፣ ሁለቱንም የሚያስተሳስራቸው ጉዳይ እንደማይጠፋ ነው የሚነገረው።
በሌላ በኩል፣ ሦስቱም አገራት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ የፖለቲካ ምክክር ኮሚቴ ለማቋቋም የተስማሙ ሲሆን፤ በአህጉራዊ፣ ዓለም አቀፋዊና  ጂኦፖለቲካዊ የጋራ ተጠቃሚነት ጉዳዮች ላይ ምክክር ለማድረግ የሚያግዝ ነው። እንግዲህ የግብጽና ኤርትራ ግንኙነት ዋና ጥንስሱ ከሶማሊያና ኢትዮጵያ ጋር በሚኖሩ የዲፕሎማሲ ግንኙነቶች እንደሚሆን ተንታኞች ሲናገሩ፣ የሰሞኑ ምክክር በኤርትራ መንግስት ጋባዥነት መዘጋጀቱ የጉዳዩን እየከረረ መምጣት እንደሚያመለክት የአካባቢው የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡
ነገሮችን በማጠቃለል፣ ምን ዓይነት መልክ እንደተጎናጸፉ እንመልከታቸው!
የግብጹ ፕሬዚዳንት ከሚኒስትሮቻቸው ባለፈ የአስመራን መሬት የረገጡት በስልጣን ዘመናቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ነው። ይህም ለጉዳዩ የተሰጠውን ትኩረት የሚያመለክት ይመስላል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ የሚያዋስኗቸውን የድንበር በሮች በሙሉ ተዘግተው ይገኛሉ። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ታድሶ የነበረው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣  የፕሪቶሪያ ስምምነትን ተከትሎ መልሶ መሻከሩ በታዛቢዎች ዘንድ ይገለጻል። ከዚህ ከፍ ሲል በአፍሪካ ቀንድ ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጋጋለ መጥቷል። በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ እንዲሁም በግብጽ እና በኢትዮጵያ መካከል ውጥረቶች ነግሰዋል፤ ከላይ በጠቀስናቸው ምክንያቶች። በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት መሻከር በመገናኛ ብዙሃን እየተገለጸ በሚገኝበት ወቅት፣ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ከሶማሊያ እና ከግብፅ ጋር ያላቸውን ግንኙነት እያጠናከሩ ነው።
ኢትዮጵያ ራሷን እንደ ነጻ አገር ካወጀችውና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላገኘችው ሶማሊላንድ ጋር 20 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የባሕር ጠረፍ ለማግኘት የፈረመችው የመግባቢያ ሰነድ፤ ሶማሊያን በእጅጉ አስቆጥቶ በቀጠናው ከፍተኛ ውጥረትን ያስከተለ ሆኗል። በኢትዮጵያና በሶማሊያ መንግስት ባለስልጣናት መካከል እየተካሄደ ያለው የቃላት ጦርነት እየተባባሰ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ወደ ቀጥተኛ አሊያም የእጅ አዙር ግጭት እንዳያመራ ብዙዎችን አስግቷል፡፡
በታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት ለዓመታት ከኢትዮጵያ ጋር ስትወዛገብ የነበረችው ግብጽ፤ ከሶማሊያ ጋር የወታደራዊ ትብብር ስምምነት መፈራረሟ ኢትዮጵያን እንዲሁም የአፍሪካን ቀንድ ቀጣናን ስጋት ላይ ጥሏል። ግብጽ ራሷን በነጻ አገርነት ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር በተገባው የባሕር በር መግባቢያ ስምምነት፣ ከኢትዮጵያ ጋር ውዝግብ ውስጥ ለገባችው ሶማሊያ በሁለት ዙር በአይሮፕላን እና በመርከብ የተጫኑ የጦር መሳሪያዎች መላኳን ተከትሎ ውጥረቶቹ ተካርረዋል።
የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ትብብር ስጋት ውስጥ የጣላት ኢትዮጵያም የአፍሪካ ቀንድ ቀጣናን ለማተራመስ እየተወሰደ ያለውን እርምጃ በዝምታ እንደማትመለከት አስታውቃለች። የሶማሊያ መንግስትንም “ቀጣናውን ለማተራመስ ከሚሹ የውጭ ሃይሎች ጋር እየሰራ ይገኛል” ስትል ከስሳለች።
የዚህ  ሁሉ ቀጣናዊ ትርምስ መጨረሻ ከምን ይደርስ ይሆን? ለአገራችን ትርፍን ያመጣል? ወይስ ኪሳራን ይጋብዛል?...አብረን የምናየው ነው የሚሆነው።

Read 1160 times