Monday, 07 October 2024 20:01

የግጥም ጥግ

Written by 
Rate this item
(5 votes)

ውሽንፍር ለብሼ

ይኸው ሰማይ በራ… ህዋው ቦገግ አለ፣
 የኮከቦች መንደር ….ተመሰቃቀለ፣
 ከበደ ነጎድጓድ…. በረዶም ወረደ፣
 ዘመናት የፀናው… አለት ተንጋደደ፣
  …………………….
በዚህ ምፅዓት መሀል…ወንጀሌን ቆጥሬ፣
መጥፋቴ ነው አልኩኝ፣
ከሃያል ክንዱ ላይ… ቅንጣት ቢልክብኝ፣
እንክርዳድ አከልኩኝ፣
በቆምኩበት ራድኩኝ፣
………………………..
እናም ባሻገሬ…በፅናት የቆመ
ታየኝ እና ፃድቅ፣
ሸሸሁኝ ወደ እርሱ…ቢሸሽገኝ ብዬ
ከዚያ ሁሉ ድቅድቅ፣
ግን ከፋ ነጎድጓድ…ብልጭታ ጨመረ፣
ምድርን ይንጣት…ያስጮሃት ጀመረ፣
ፍጥረት ተከተተ፣
ከፃድቅ ሰው ጉያ… ከእግሮቹ ስር ሆኜም
ቁጣ በረከተ፣
…………………………
አዘንኩ ለዚያ ሰው… እኔ በእሱ ልድን
ስገባ በእቅፉ፣
እሱ በእኔ ሰበብ..ታሰበኝ መርገፉ፣
ለኃጥዓን የመጣ… እንዲል መፅሐፉ፣
………………………
ፃድቅ ከሚጠፋ…ልጥፋ ከአጠገቡ
ከእቅፉ ወጥቼ፣
ሄድኩኝ ከእርሱ ርቄ
ቆምኩኝ ለብቻዬ…አንገቴን አቅንቼ፣
    ድንገት ልብ ገዛሁ፤
ምህረቱ እንደማያልቅ… ሲታወሰኝ ክብሩ
ጀገንኩኝ በዶፉ፣
ሊያጠፋኝ በበራው…ሄድኩኝ በብልጭታው
     በብርሃን አክናፉ፣
ፍፁም ጠፋሁ ካለም…ከመቅደሱ ገባሁ
    ቆምኩኝ ከደጃፉ፣    
    ወንጀሌን ሳልቆጥር…በምህረቱ ሳምን
    እንደ ንስር ፀናሁ…ጀገንኩኝ በዶፉ፣
    ዙፋኑ ስር ሆኜ…ቅጣቶቼ አለ.፡፡ (አብዱራሕማን ጀማል፤ ከ“ደቦ 60 ደራስያን” መድበል)


Read 1061 times