Saturday, 05 October 2024 20:37

በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪ ቅበላ ጊዜያቸውን አራዘሙ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

•  በክልሉ በቀጠለው የጸጥታ ችግር ሳቢያ ነው ተብሏል


በአማራ ክልል የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በክልሉ እየተባባሰ በመጣው የጸጥታ ችግር ሳቢያ የዘንድሮን የተማሪዎች ቅበላ ጊዜ  ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘማቸው ተነገረ፡፡

ዩኒቨርሲቲዎቹ ተማሪዎቻቸውን ለመቀበል በይፋ ጥሪ አድርገው የነበረ ቢሆንም፣ በክልሉ በቀጠለው ግጭት ሳቢያ የቅበላ ጊዜያቸውውን ላልተወሰነ ጊዜ ማራዘማቸው ታውቋል፡፡ ደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ፣ኢንጅብራ ዩኒቨርሲቲ፣ ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ፣ ወሎ ዩኒቨርሲቲና ደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የቅበላ ጊዜያቸውን ያራዘሙ ሲሆን፤ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ለተማሪዎች ያደረገውን ጥሪ ከትስስር ገጹ ላይ ማንሳቱ ተዘግቧል፡፡

የባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ካሉት 9 ካምፓሶች ውስጥ ሁለቱ ማለትም፡- ዘንዘሊማ እና ሰባታሚት ጥበበ ጊዮን ካምፓሶች በጸጥታ ችግር ሳቢያ መዘጋታቸው  ተነግሯል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአማራ ክልል ከመንግሥት ጋር በመዋጋት ላይ  የሚገኘው ታጣቂው የፋኖ ቡድን፣ የክልሉን ዋና መንገዶች ሙሉ በሙሉ መዝጋቱ ተነግሯል፡፡ መንገዶቹ የተዘጉት ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጀምሮ ሲሆን፤በዚህም የተነሳ የተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ በእጅጉ መገደቡ ነው የተጠቆመው፡፡

የፋኖ ታጣቂዎች ከመንግሥት ጋር ግጭት ውስጥ የገቡት ባለፈው ዓመት ሲሆን፤ ይህም በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችም ከትምህርት ገበታቸው መስተጓጎላቸው ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል፣ ባለፈው ሳምንት የመከላከያ ሃይልና የአማራ ክልላዊ መንግሥት በፋኖ ታጣቂዎች ላይ ከፍተኛ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡

Read 1584 times