Saturday, 28 September 2024 20:05

የግብጽ ወታደራዊ ድጋፍ ቀጣናውን እንዳያተራ ምሰው ተሰግቷል

Written by 
Rate this item
(2 votes)

በነሐሴ ወር 2016 ዓ.ም.፡፡ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ሐሰን ሼኽ ሞሃሙድ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ወደ ግብጽ፣ ካይሮ ተጓዙ። በዚህ ጉብኝታቸው አልመው የሄዱትን አሳክተዋል፡፡ ከግብጽ አቻቸው አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ ስምምነቱ ከሚያካትታቸው ጉዳዮች ውስጥ ደግሞ ለሶማሊያ የሚደረገው የጦር መሳሪያ ድጋፍ ቁልፍ ነበር፡፡  
በዚሁ መሰረት የመጀመሪያው ዙር የጦር መሳሪያ ድጋፍ፣ ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም. ሞቃዲሾ ደረሰ። ይህም ድጋፍ ግብጽ በአስርት ዓመታት ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሶማሊያ ያደረገችው ወታደራዊ እንቅስቃሴ መሆኑ ነው።
ሶማሊያ ከተለያዩ አገራት ወታደራዊ ድጋፍ ቢደረግላትም፣ የግብጽ ድጋፍ ግን ከሌሎች የተለየ ተደርጎ እንደሚቆጠር የአፍሪካ ቀንድን አጠቃላይ እንቅስቃሴ በቅርበት የሚከታተሉ የፖለቲካ ተንታኞች ይናገራሉ። ምክንያቱም ወታደራዊ ድጋፉ የመጣው በሶማሊያና ኢትዮጵያ መካከል ውጥረቱ በተባባሰበት ወቅት ነው፡፡ የውጥረቱ መነሻ ደግሞ ኢትዮጵያ ከራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ ኪራይ የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟ ነው። ስምምነቱ ለኢትዮጵያ የወደብ አገልግሎት በኪራይ እንድታገኝ የሚያስችላት ሲሆን፤ በአንጻሩ ለሶማሊላንድ ደግሞ የአገርነት ዕውቅና ያጎናጽፋታል።
እንግዲህ ለራስ ገዟ ሶማሊላንድ ዕውቅና መሰጠቱ ነው፣ ሶማሊያን ኢትዮጵያ ላይ ጥርሷን እንድትነክስ ያደረጋት፡፡
ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ወደብ ባይኖራትም፣ ወታደራዊ አቅሟንና የንግድ እንቅስቃሴዋን ለማጠናከር በመሻት የባሕር በር ትፈልጋለች። ከ30 ዓመታት በላይ ከሶማሊያ ተነጥላ በአገርነት፣ ነገር ግን ከዓለም አቀፉ ማሕበረሰብ ዕውቅና ሳታገኝ ከኖረችው ሶማሊላንድ ጋር ኢትዮጵያ  የወደብ  ስምምነት መፈጸሟ ውጥረት እንደሚፈጥር ይጠበቃል፡፡ ከዚያም በላይ ግን ኢትዮጵያ ለሶማሊላንድ  የአገርነት ዕውቅና ለመስጠት መስማማቷ ሶማሊያን ያበገናት ይመስላል፡፡ በዚህም ምክንያት  የአጸፋ ምላሽ በሚመስል መልኩ፣ ሶማሊያ ከግብጽ ጋር የነበራትን አጠቃላይ ግንኙነት ማጠንከሩን ያዘች።
ባለፈው እሁድ መስከረም 12 ቀን 2017 ዓ.ም. ሞቃዲሾ የደረሱት የግብጽ ከባድ ጦር መሳሪያዎች በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ  ለሶማሊያ የተደረገ ወታደራዊ ድጋፍ ሲሆን፣ ያሁኑ በመጠንም በዓይነትም የላቀ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ የግብጽን ወታደራዊ ድጋፍ ተከትሎ፣ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ኒውዮርክ የነበሩት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ  መግለጫ እንዲሰጡ አስገድዷቸዋል፡፡ ግብጽ ለሶማሊያ ያደረገችው የከባድ ጦር መሳሪያዎች ድጋፍ፣ ዞሮ ዞሮ ወደ አሸባሪዎች እጅ ሰተት ብሎ የሚሄድና አሸባሪዎችን የሚያጠናክር ነው ሲሉ  አምባሳደሩ በአጽንዖት ተናግረዋል። በማያያዝም፣ ወትሮም በቋፍ ላይ የሚገኘውን የቀጣናውን የሰላም ሁኔታ ወደ ባሰ ውጥንቅጥ ሊመራ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸል፡፡ ቢዝነስ ኢንሳይደር እንደዘገበው፤ የሁለቱ አገራት ወታደራዊ ስምምነትና ድጋፍ፣ በኢትዮጵያ ዓይን በጥርጣሬ የሚታይ ነው።
ከሦስት አስርት ዓመታት በፊት ከሶማሊያ ራሷን ለይታ ነጻ አገርነቷን ያወጀችው ሶማሊላንድ፤ ግብፅ ለሶማሊያ ያስታጠቀቻቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በተመለከተ ቁጣዋንና ተቃውሞዋን በመግለጽ ማንም አልቀደማትም፡፡ ሶማሊላንድ የጦር መሳሪያ አቅርቦቱ በቀጣናው አሳሳቢ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስታውቃለች፡፡ የሶማሊላንድ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፤ ከግብፅ ወደ ሞቃዲሾ የገቡት ከባድ የጦር መሳሪያዎች ውስብስብ የደኅንነት ፈተና ያለበትን የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል ሲል ጥልቅ ስጋት መፈጠሩን ጠቁሟል።
አክሎም፤ የሞቃዲሾ አስተዳደር እነዚህን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ከባድ የጦር መሳሪያዎች በተገቢው ሁኔታ የመያዝ አቅም ስለሌለው አልሻባብን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ አንጃዎች እጅ በመግባት አሳሳቢ ሁኔታ ሊፈጠር ይችላል በማለት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
የቀድሞ የግብጽ ረዳት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ራካ አሕመድ ሐሰን ለኢምሬትሱ  ናሽናል ጋዜጣ ሲናገሩ፤ “ብዙዎች ይህ የከባድ መሳርያ ድጋፍ የተላከው ኢትዮጵያን ታሳቢ አድርጎ ሊመስላቸው ይችላል፡፡ ይሁንና ይህ ግምት ስህተት ነው›› ብለዋል፡፡ ንግግራቸውን ሲቀጥሉም፤ “የሶማሊያ መንግሥት ካይሮ ድረስ መጥቶ ወታደራዊ እርዳታ እፈልጋለሁ ያለው ራሱ ነው፡፡ በዚህ ደግሞ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ቅር ሊላቸው ይችላል፡፡” ብለዋል፡፡
እኚህ የቀድሞ የግብጽ ሚኒስትር ለጋዜጣው በሰጡት ማብራሪያ፤ “ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቅርቡ የፈጠሩትን ውዝግብ ተከትሎ በስፍራው የነበሩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ለቅቀው ሊወጡ ስለሆነ፣ የፀጥታ ክፍተት ይፈጠራል፡፡ ሶማሊያ ይህንን ክፍተት የሚሞላ አገር ስትፈልግ ግብጽን አገኘች” ባይ ናቸው፡፡  ከጦር መሳርያ ዕርዳታ በተጨማሪ ግብጽ የሶማሊያን ወታደሮች እንደምታሰለጥንም  ገልፀዋል፡፡ የግብጽ የጦር መሳርያና ወታደሮች ወደ ሶማሊያ በመግባታቸው ኢትዮጵያ እያሰማች ያለውን ወቀሳም፤ “ከጥፋተኝነት ስሜት የሚመነጭ” ሲሉ ለማሸሞር ሞክረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ምን እንዳጠፋች ግን አልጠቀሱም፡፡ “አንድ ሰው መጥፎ ነገር ከሰራ ሁሌም ጥፋተኝነት ይሰማዋል፡፡ ወይንም ላደረገው ነገር መልስ ሊሰጡኝ ነው ብሎ ይፈራል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡  
አክለውም፤ “በቅርቡ ኢትዮጵያ ራሷ ከሞሮኮ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርማለች፡፡ ግብጽ ግን ይህንን አልተቃወመችም፡፡ ወይም በስምምነቱ ላይ ጣልቃ ለመግባት ፍላጎት አላሳየችም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ “ግብጽ ከሶማሊያ በተጨማሪ ከኤርትራ ጋር ተመሳሳይ ስምምነት ለማድረግ እየተንቀሳቀሰች መሆኑ በኢትዮጵያ ላይ ሙሉ ጦርነት ለመክፈት እየተዘጋጀች መሆኑን አያሳይም ወይ?” በሚል ከጋዜጣው ተጠይቀው ነበር፡፡ እኚህ የቀድሞ ባለስልጣን ሲመልሱም፤ “ኤርትራን ከግብጽ ጋር በደህንነትና በወታደራዊ ጉዳዮች ያገናኛት የራሷ የሆነ ምክንያት አላት፡፡
 ወደ ግብጽም ከመጣን ከእነርሱ ጋር የምንጋራው የጋራ ፍላጎት ይኖረናል፡፡ ይሁንና ከእኛ ይልቅ በድንበርም ሆነ በብሄር የጋራ የሆነ ጉዳይ ያላቸው ከኢትዮጵያ ጋር ነው፡፡ ስለዚህም ከእኛ ይልቅ ኢትዮጵያውያን ይቀርቧቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት  የሶማሊያ መንግስት ዋነኛ አጋር ነበረች። የሶማሊያ መንግሥትን በሚደግፈው፣ የአፍሪካ ሕብረት የሰላም አስከባሪ ሃይል ኢትዮጵያ 3 ሺህ ወታደሮችን ያሰማራች ሲሆን፣ በሌላ የሁለትዮሽ ስምምነት ከ5ሺ-7ሺ የሚደርሱ ወታደሮች አሰማርታለች፡፡ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት  የኢትዮጵያ ወታደሮች ከወጡ በኋላ እስከ 5 ሺህ የሚደርሱ የግብጽ ወታደሮች የአፍሪካ ሕብረት ሰላም አስከባሪ ሃይልን  ይቀላቀላሉ ተብሏል። ሌሎች 5 ሺህ ወታደሮች ደግሞ በሌላ ስምሪት ወደ እንቅስቃሴ እንደሚገቡ ተገልጿል።
 የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ለቅቀው መውጣት የሶማሊያን  የጸጥታ ስጋት እንደሚያባብሰው የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ የሆነው ሆኖ የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስትር አብዱልቃዲር ሞሃመድ ኑር፣ በማሕበራዊ ትስስር ገጻቸው፣ ግብጽ ላደረገችላቸው ወታደራዊ  ድጋፍ አመስግነዋል፣ ስለ መሳሪያዎቹ ምንም የጠቀሱት ነገር ባይኖርም፡፡ ሮይተርስ የዜና ወኪል  የወደብና የጸጥታ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ባለፈው እሁድ  ሞቃዲሾ የደረሱት የጦር መሳሪያዎች የአየር መቃወሚያና ሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ባለፈው ሳምንት ግብጽ፣ በሶማሊላንድ የሚኖሩ ዜጎቿ ከአገሪቷ ለቅቀው እንዲወጡ ማሳሰቧ ተዘግቧል፡፡
በግብጽና ሶማሊያ መካከል  የሁለትዮሽ ወታደራዊ ስምምነቱ የተፈረመ ሰሞን፣ ኢትዮጵያ ሌሎች አካላት ቀጣናውን ለማተራመስ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት፣ በዝምታ እንደማትመለከት አሳውቃ ነበር። የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር በምላሹ “ኢትዮጵያ ጩኸቷን ታቁም፣ እያንዳንዱ ወገን የዘራው ዘር ፍሬ ማፍራቱ አይቀሬ ነውና” ብለው ነበር። እንዲህ ያለው ፍጥጫ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ካልተፈታ ለቀጣናው መተራመስ የራሱን አደፍራሽ ሚና ሊወጣ እንደሚችል ተንታኞች ይናገራሉ፡፡
በቱርክ አሸማጋይነት እንደሚደረግ ቀን የተቆረጠለት የኢትዮጵና ሶማሊያ ንግግር የራሱን ፍሬ ሊያፈራ እንደሚችል ቢገመትም፣ የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት፣ የሦስተኛ አገራት ጣልቃ ገብነት ውይይቱ እንዳይሰምርና በአፍሪካ ቀንድ የሰላም አየር እንዳይነፍስ አደናቃፊ ሊሆን ይችላል፡፡

Read 887 times