Friday, 20 September 2024 20:56

7 ሚ. ዶላር ዋጋ ወጥቶበት የነበረው የሂዝቦላህ አመራር በእስራኤል ጦር ተገደለ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

•  ሊባኖሳዊያን በእጃቸውና በቤታቸው ያሉ የቴክኖሎጂ
መሳሪያዎችን እየጣሉ ነው ተባለ


7 ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ወጥቶበት የነበረው የሂዝቦላህ አመራር በእስራኤል ጦር መገደሉ ተዘግቧል፡፡ ከአንድ ዓመት በፊት የሐማስ ታጣቂዎች በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘራቸውን ተከትሎ የተጀመረው ጦርነት መልኩን ቀይሮ አሁን ወደ ሊባኖስ ፊቱን አዙሯል፡፡

የእስራኤል ጦር ከትናንት ጀምሮ በደቡባዊ ሊባኖስ በኩል ከፍተኛ ጥቃት በማድረስ ላይ ሲሆን፤እስራኤል ከደቂቃዎች በፊት በሀገሪቱ መዲና ቤሩት የአየር ላይ ጥቃት መሰንዘሯ ተሰምቷል፡፡  በዚህ ጥቃት ከዚህ በፊት በአሜሪካ ይፈለግ የነበረው የሂዝቦላህ ሬድዋን ሀይል ኮማንደር የሆነው ኢብራሂም አኪል መገደሉን የፈረንሳዩ የዜና ወኪል  ኤኤፍፒ ዘግቧል፡፡

ከኢብራሂም አኪል በተጨማሪ ስምንት ሰዎች ሲገደሉ፣ 60 ሰዎች ገደማ ደግሞ ቆስለዋል፡፡  እስራኤል ከሂዝቦላህ ከፍተኛ አመራር መካከል ባለፈው ሀምሌ ወር ላይ ፉአድ ሽኩርን በደቡባዊ ሊባኖስ መግደሏ ይታወሳል፡፡ ኢብራሂም በፈረንጆቹ 1983 ዓ.ም  ላይ በቤሩት በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ በደረሰው የቦምብ ጥቃት እንዲሁም በዚሁ ተመሳሳይ ዓመት በሊባኖስ በነበሩ የአሜሪካ ባህር ሃይል  አባላት ላይ የተፈጸመውን ጥቃት አቀነባብሯል ተብሎ ሲፈለግ እንደነበር ይታወቃል፡፡  
በመላው ሊባኖስ የኮሙኒኬሽን መሳሪያዎች መፈንዳታቸውን ተከትሎ፣ ከ37 በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከዚህ ሴራ ጀርባ እስራኤል እጇ እንዳለበት ሂዝቦላህ ገልጿል፡፡ ፍንዳታዎቹን ተከትሎ ሊባኖሳዊያን በእጃቸውና በቤታቸው ውስጥ ያሉ የቴክኖሎጂ መሳሪያዎችን እየጣሉ ነው ተብሏል፡፡

Read 1125 times