Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 01 September 2012 09:14

በየአምስት አመቱ አብዮት የማያጣው የጠ/ሚ መለስ ህይወት 1967/68 ዓ.ም..... እድሜ 20 አመት

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ጠ/ሚ መለስ በሃያ አመታቸው ነው በረሃ የገቡት። በ1967 ዓ.ም ህወሃትን የመሰረቱ አባላትና መሪዎች እንደሚናገሩት፤ በቀጣዩ አመት በ1968 ዓ.ም የድርጅቱ ፖለቲካዊ መዋቅር ሲቀረፅ የአቶ መለስ ድርሻ ከፍተኛ ነበር። እነዚያ ሁለት አመታት፤ ድርጅቱ ህልውናውን ለመጠበቅና ለማስተዋወቅ፤ የድርጅት መመሪያዎችንና አላማዎችን በስርዓት ለማዘጋጀት የተፍጨረጨረባቸው ፈታኝ አመታት ናቸው። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወጥቶ ወደ በረሃ መግባት፤ የፖለቲካና የትጥቅ ድርጅት ማቋቋም... ለአንድ ወጣት ቀላል የህይወት ለውጥ አይደለም - ራሱን የቻለ አብዮት ነው።

የያኔው የአገሪቱ ኋላቀርነትና ድህነት... በእርግጥም “አብዮት... አብዮት” ሊያሰኝ እንደሚችል አያጠራጥርም - በተለይ ዘመናዊ ትምህርት ለቀሰሙ ወጣቶች። በእርግጥ፤ የያኔው “የአብዮት ትኩሳት”፤ ብዙ መዘዞችን ያዘለና በበርካታ ጣጣዎች የታጨቀ ነበር። በመንግስት ስልጣንና በጉልበት መሬት የሚወረርበት፤ የሳይንስ ትምህርት እንደሃጥያት የሚቆጠርበት፤ የሚሰራና የሚነግድ ሰው የሚናቅበት ኋላቀር አስተሳሰብንና አኗኗርን ለመለወጥ፤ “አብዮት! አብዮት!” ብሎ መነሳት የግድ ነው።

ያ አይነት የ“አብዮት” እንቅስቃሴ ከ100 አመታት በፊት ቢፈጠር ኖሮ፤ የእነ ቶማስ ጃፈርሰንን ስም የሚያነግብ፤ የአሜሪካን የነፃነት አብዮት በአርአያነት የሚያሞግስ የካፒታሊዝም አብዮት መሆኑ አይቀርም ነበር። የ1960ዎቹ ዓ.ም የአብዮት ትኩሳት ግን፤ በማርክስና በሌኒን ስም የሚምል፤ በስታሊንና በማኦ ስም የሚገዝት፤ በራሺያና በቻይና አብዮት የሚፎክር የሶሻሊዝምና የብሄር ብሄረሰብ አብዮት ነው - ንብረትን ለመውረስ የሚዝት፤ የግል ነፃነትን አጥላልቶ በመደብና በብሄር ብሄረሰብ ሰልፍ ለማስያዝ የሚመኝ፤ “አንድ አገር አንድ መሪ ፓርቲ” የሚል ትኩሳት።

እንደ ኢህአፓ በከተማ የመሸጉትም ሆኑ እንደ ህወሃት በረሃ የገቡት የዘመኑ አብዮተኞችና ፋኖዎች በሙሉ፤ በሶሻሊዝምና በብሄር ብሄረሰብ ፓለቲካ የተቀኙ ናቸው። አንዳንዶቹ ላይ ሶሻሊዝሙ ገናና ይሆናል፤ አንዳንዶቹ ላይ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካው ገናና ይሆናል - ለምሳሌ በህወሃት። ነገር ግን ጭልጥ ብሎ የሄደ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካና አዝማሚያው፤ ለወጣቱ መለስ ዜናዊ ብዙም የተስማማው አይመስልም። መቼም፤ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ በቀላሉ ወደ አስቀያሚ ዘረኝነት ሊንሸራተት እንደሚችል ስለተገነዘበ ሊሆን ይችላል።

ለነገሩ የሶሻሊዝም ነገርም ለወጣቱ መለስ ዜናዊ ሙሉ ለሙሉ የተዋጠለት አይመስልም - ለምሳሌ እንደ ብዙዎቹ አብዮተኞች፤ ስለ ምዕራቡ የካፒታሊዝም ስርዓት ፈፅሞ መስማት አልፈልግም የሚል እንዳልነበረ አብረውት የነበሩ ታጋዮች ይናገራሉ። ሌላው ቀርቶ የቢቢሲ የሬዲዮ ስርጭትን ማዳመጥ በብዙ አብዮተኞች ዘንድ እንደ ድክመት በሚታይበት ወቅት፤ ወጣቱ መለስ ዜናዊ ዘወትር ከማዳመጥ ወደኋላ አላለም። ይህም በጎ ዝንባሌን ብቻ ሳይሆን፤ ለተፅእኖ እጅ አለመስጠትንም የሚጠቁም አዝማሚያ ነው። በኮሙኒስቶች መሃል ሮብና አርብ መፆምም፤ ለትችትና ለስላቅ የሚዳርግ እንደነበር የሚገልፁ አንድ የቀድሞ ታጋይ በበኩላቸው፤ ወጣቱ መለስ ግን የሚያምንበትን ነገር ከመፈፀም ወደ ኋላ አይልም ነበር ብለዋል።

ስለ አሜሪካ መፅሃፍ ማንበብና ቢቢሲን ማዳመጥ፤ ዛሬ ላይ ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ፤ ያኔ በአብዮቱ የትኩሳት ዘመን ግን ፅናትን የሚጠይቁ ከባድ ነገሮች ነበሩ። በሌላ በኩል ሲታዩ ግን በእርግጥም ቀላል ናቸው - ፅናት ያለው ወጣት በግሉ ሊፈፅማቸው የሚችሉ ነገሮች ናቸው። አስቸጋሪውና ፈታኙ ነገር፤ የድርጅቱን አዝማሚያና አቅጣጫ ማስተካከል ነው - የብዙ ሰዎችን አስተሳሰብና አዝማሚያ ወደ በጎ አቅጣጫ መሳብንና መማረክን የግድ ይላል። ያ ደግሞ በርካታ አመታትን ይፈጃል።

ከ1968 ዓ.ም በኋላ በነበሩት አመታት በድርጅቱ ውስጥ ሁለት ነገሮች ተከስተዋል። በአንድ በኩል ተከታታይ ውጊያዎች ተካሂደዋል - አንዳንዶቹም የድርጅቱን ለመበተንና ለማፍረስ የተቃረቡ ውጊያዎች ናቸው። በሌላ በኩል ደግሞ፤ ወደ ዘረኝነት የተንሸራተተው (ጠባብ ብሄረተኝነት ይሉታል በኢህአዴግ ቋንቋ) የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ፤ ለዘብ እንዲል ዘመቻ ተካሂዷል። ይህንን የፖለቲካ ዘመቻ ሲመሩ ከነበሩት ሶስት ሰዎች መካከል አንዱ አቶ መለስ ዜናዊ እንደሆኑ፤ በወቅቱ ባላንጣቸው የነበሩት አቶ አረጋዊ በርሄ ሳይቀሩ ፅፈዋል።

አቶ መለስ በእነዚያ የመጀመሪያ አምስት አመታት ውስጥ ተሰሚነታቸውና ተደማጭነታቸው ሊጨመር የቻለው፤ በአጋጣሚ አይደለም። የድርጅቱ መሪ ባይሆኑም፤ ድርጅቱ ያቋቋመውን የፖለቲካ ትምህርት ቤት እንዲመሩ መመደባቸው ለአቶ መለስ መልካም እድል የሆነላቸው ይመስላል። በብሩህ አአምሮ እውቀታቸውን ለማስፋትና አስተሳሰባቸውን ለመሳል፤ መፃህፍት ለማንበብና አለማቀፍ ዜናዎችን ለመከታተል፤ ከዚያም እውቀታቸውን ለሌሎች ለማስተላለፍ በቅተዋል፤ በርካታ አድናዊዎችንም ለማፍራት ጠቅሞዋቸዋል። በዚያ ትምህርት ቤት እና በአቶ መለስ አስተማሪነት ያለፉ ሰዎች ናቸው የድርጅቱን የወደፊት አቅጣጫ የሚወስኑ ካድሬዎች። እናም የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካን በመጠኑ ለዘብ ለማድረግ በተካሄደው ዘመቻ የአቶ መለስ ድርሻ ጎላ ብሎ መታየቱ አይገርምም።

1972/73 ዓ.ም .... እድሜ 25 አመት

ድርጅቱ ለተከታታይ አመታት በደርግ በተካሄደበት ዘመቻ እንዲሁም ከሌሎች ድርጅቶች ጋር በተፈጠረ የተቀናቃኝነት ውጊያ፤ አንዳንዴ ሊፈራርስ ቢቃረብም፤ በአምስት አመታት ውስጥ ዘመቻዎችን መቋቋም የሚችል ጠንካራ ወታደራዊ አቅም ለማደራጀት በቅቷል። ከዚህም በተጨማሪ፤ እስከ ጥግ ድረስ ተለጥጦ የነበረው የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ በትንሹም ቢሆን ለዘብ በማለት፤ ስለ ጠቅላላ አገሪቱ የማሰብና የማለም አቅጣጫ ብቅ ብሏል።

በርካታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በደርግ ዘመቻ ክፉኛ ተጎድተው በተዳከሙበት ወቅት፤ ህወሃት ህልውናውን ማስጠበቅና መጠንከር መቻሉ እንዲሁም የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካውን ለዘብ ለማድረግ መቻሉ አንድ ስኬት ቢሆንም፤ ከፈተናዎች አልተላቀቀም። በወታደራዊ አቅም የድርጅቱን ህልውና ማስጠበቅ ብቻውን ግብ አይደለም፤ “እንዴት ነው ደርግን የማሸንፈው?” የሚል ነው ዋናው ጥያቄ። የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ በትንሹ ለዘብ ቢደረግ እንኳ፤ በድርጅቱ ውስጥ ገናና የፖለቲካ አቅጣጫ መሆኑ አልቀረም። በዚህ አቅጣጫ እየተጓዘ፤ በአገር ደረጃ ለውጥ የሚያመጣ ሃይል መሆን አይቻልም። አቶ መለስ በ25 አመታቸው ለዚህ ችግር መፍትሄ ይሆናል የሚሉትን ሃሳብ ይዘው መጣር ጀምረዋል።

በእርግጥ በመፍትሄነት የቀረበው ሃሳብ፤ በድርጅቱ ውስጥ ከነበሩት የሶሻሊዝምና የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካዎች መካከል፤ የአንዱን ገናናነት በሌላው ለመተካት ያለመ ነው። በብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ገናናነት ምትክ የሶሻሊዝም ፖለቲካ ገንኖ እንዲወጣ ለማድረግ፤ በድርጅቱ ውስጥ ሌላ “መሪ ድርጅት” መቋቋም አለበት ተባለ - በድብቅ ሳይሆን በይፋ። “መሪው ድርጅት” ... “ማሌሊት” ይባላል - (ማርክሲስት ሌኒኒስት ሊግ ትግራይ) ማለት ነው። ነገርዬው ጥሩ መፍትሄ እንዳልሆነ አሁን አከራካሪ አይመስለኝም። በማርክስና በሌኒን ስም የሚጠራው የኮሙኒዝም ስርአት፤ ያኔም ቢሆን በአለም ደረጃ ውድቀቱ እየታየ፤ የሚፈራርስበት እለት እየተቃረበ ነበር። ያኔኮ ካፒታሊዝም እንደገና ማንሰራራት የጀመረበት ጊዜ ነው - ሮናልድ ሬገን በአሜሪካ፣ ማርጋሬት ታቸር በእንግሊዝ ስልጣን የያዙበት ዘመን ነው። በዚያ ጊዜ ማሌሊትን መመስረት ብዙ የሚያስኬድ ባይሆንም፤ የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ ገናና ሆኖ ከሚቀጥል ግን፤ የሶሻሊዝም ፖለቲካ ገናና ቢሆን ይሻላል - ቢያንስ ቢያንስ በትውልድና በዘር ላይ ሳይሆን በሃሳብና በአስተሳሰብ ዙሪያ የተመሰረተ ፖለቲካ ነውና። ቢያንስ ቢያንስ በአገር ደረጃ ለማሰብና ለመስራት ያስችላል። አቶ መለስ ድርጅቱን ወደዚህ አቅጣጫ እንዲገባ ለማድረግ የጣሩት፤ በዚህ ምክንያት ከሆነ መልካም ነው። አስተዋይነት ነው።

1977/78 ዓ.ም.... እድሜ 30 አመት

ከአምስት አመታት በላይ ለሆነ ጊዜ፤ በድርጅቱ ውስጥ ሲሰባሰብና ሲዋቀር የቆየው “ማሌሊት” በሃምሌ 1977 ዓ.ም በይፋ ተቋቋመ። በ1978 ዓ.ም ደግሞ አቶ መለስ የድርጅቱ መሪ ሆኑ። በእርግጥ፤ እንዲህ ቀላል አልነበረም። ድርጅቱን ሲመሩ ከቆዩት አንጋፋ መሪዎች ጋር ለመከራከር መድፈርና ሌሎችን ለማሳመን መጣር ቀላል አይደለም። ከአንድም ሁለት ጊዜ፤ የመታሰር እጣ አጋጥሟቸዋል። ግን ብዙ አልቆዩም። ከብዙ ክርክር፤ ከብዙ ንትርክ፤ ከብዙ ሽኩቻ በኋላ፤ የቀድሞ መሪዎች ተሽረው ወረዱ። ደግነቱ፤ በኮሙኒስት ፓርቲዎች ውስጥ ተዘውትሮ እንደሚስተዋለው፤ ከሹም ሽሩ ጋር እስርና ግድያ አልተፈፀመም። ለነገሩ ሹክቻውም ያን ያህል በውስብስብ ሴራ የተተበተበ እንዳልነበረ የያኔው ሰዎች ይገልፃሉ።

ሌላው ቀርቶ የአቶ መለስ ዋና ባላንጣ የነበሩት አቶ አረጋዊ በርሄም፤ ስለ አቶ መለስ ብዙ መጥፎ ነገር ቢፅፉም፤ የስልጣን ሽግግሩ የተካሄደው በአብዛኛው በሃሳብ ፍጭትና በክርክር እንደነበረ ይጠቁማሉ። በወቅቱም የአቶ መለስን ያህል አሳማኝ ሃሳቦችን ለማቅረብ የሚችል ሰው በድርጅቱ ውስጥ እንዳልነበረ አቶ አረጋዊ ፅፈዋል። በተለይ በኮሙኒዝም ሃሳቦችና በሶሻሊስት ስርአት ዙሪያ አቶ መለስ ተራቅቀውበታል ይላሉ - አቶ አረጋዊ (እንዲህ የሚሉት በትችት መንፈስ መሆኑ ሳይዘነጋ)። አስገራሚው ነገር፤ ከበርካታ አመታት በኋላ በ1992/93 ዓ.ም ተመሳሳይ የመሪዎች ክፍፍል ሲፈጠር፤ በአቶ መለስ ላይ ሌላ አይነት ትችት ቀርቧል (በካፒታሊዝም ሃሳቦች ዙሪያና በምእራባዊያን ስርዓት ዙሪያ ብዙ ተራቅቀዋል የሚል ነው ከተቀናቃኞች የቀረበው ትችት።)

ለማንኛውም በ1977/78 ዓ.ም የተካሄደው የስልጣን ሽግግር ንትርክ የበዛበት ቢሆንም፤ እስርና ግድያ አልነበረውም። የምር ባይሆንም፤ የተሻሩት መሪዎች ከፈለጉ፤ እዚያው ከጎን ሌላ ድርጅት ማቋቋምና መንቀሳቀስ እንደሚችሉ ተነግሯቸዋል። ከተሻሩት መሪዎች መካከል አንዱ፤ ለተወሰነ ጊዜ ሞክሯል። እውነትም እንዳይንቀሳቀስና ሌላ ድርጅት እንዳያቋቁም አልተከለከለም። ግን፤ ...ያው “ሂድ አትበለው፤ እንዲሄድ አድርገው” እንደሚባለው ሆነበትና እንደመሰሎቹ ተሰናብቶ በሱዳን ተሰደደ። “ሌላ ድርጅት አቋቁመህ መንቀሳቀስ ትችላለህ” የተባለው የውሸት ነው በሚል ትችት መሰንዘር ይቻላል። ትክክለኛ ትችት ነው። ግን ደግሞ፤ እንደሌሎች ኮሙኒስት ፓርቲዎች፤ ከሹም ሽረት ጋር ግድያና እስር አለመከሰቱ፤ በዚያ ላይ... እንዲሁ ለአፍ ያህል ቢሆን እንኳ፤ ሌላ ድርጅት ማቋቋም መብትህ ነው መባሉ ጥሩ አዝማሚያ መሆኑ አይካድም።

አዝማሚያ ግን፤ ብቻውን ስኬት አይደለም። ጥሩ አዝማሚያ፤ ወደ ጥሩ ጉዞ መለወጥ አለበት። ያኔ ገና አልተለወጠም። ጨርሶ የሚለወጥም አይመስልም ነበር። ለምን ቢባል፤ በኮሙኒስቶች አስተሳሰብ፤ በአንድ አገር ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ፤ ብዙ ፓርቲዎች እንዲንቀሳቀሱ ቢፈቀድ እንኳ፤ ለዘለቄታው ግን አገሪቱ በአንድ “ሃቀኛ ኮሙኒስት ፓርቲ” ብቻ መመራት አለበት። ለጊዜው አነስተኛ የግል ንግዶችን ማካሄድና ንብረት ማፍራት ቢፈቀድም፤ ለዘለቄታው ግን፤ ቢዝነስና ንግድ የመንግስት መሆን እንዳለበት ኮሙኒስቶች ያምናሉ። በዚሁ አስተሳሰብ ዙሪያ ነው፤ ኢህአዴግ የተቋቋመው። ነገር ግን፤ ቢያንስ ቢያንስ በቀላሉ ወደ ዘረኝነት (ወደ “ጠባብ ብሄረተኝነት”) ሊንሸራተት የሚችለው የብሄር ብሄረሰብ ፖለቲካ በመጠኑ ረግቦ ገናናነቱን ለሶሻሊዝም ስለለቀቀ፤ በአገር ደረጃ የሚንቀሳቀስ ኢህአዴግ ተፈጠረ። በዚህ በኩል አቶ መለስ ተሳክቶላቸዋል። ነገር ግን ይህም ገና በርካታ ተጨማሪ ፈተናዎች ይጠብቁታል። ከደርግ ጋር እጅግ ብዙ ጥፋትን ያስከተለ ጦርነት ማካሄድ ብቻ አይደለም ፈተናው። ኢህአዴግ የራሱን ሶሻሊስት አስተሳሰብ የመቀየር ፈተና ተደቅኖበታል።

1982/83 ዓ.ም... እድሜ 35 አመት

ኢህአዴግ በጦርነት ደርግን ቢያሸንፍ እንኳ፤ እንደ ደርግ ሶሻሊስት ለማስፈን መሞከር ለተጨማሪ ውድቀት እንደሚዳርግ ግልፅ ነው። አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በሶሻሊዝም ተማሯል - ድህነትንና አፈናን ነው ያተረፈለት። በዚያ ላይ፤ በአለማቀፍ ደረጃ እየተብረከረከ የነበረው የሶሻሊስት ስርዓት ተራ በተራ መፈራረስ ጀምሯል። ኢህአዴግ አቅጣጫውን ማስተካከል ነበረበት። ይህንን ማስተካከያ የቀየሱት አቶ መለስ ናቸው። ለጊዜውም ቢሆን፤ በርካታ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የፖለቲካ ስርዓት እንፈጥራለን ተባለ። ለጊዜውም ቢሆን፤ የግል ቢዝነስን የሚፈቅድ ቅይጥ ኢኮኖሚ (“ገበያ ቀመስ ኢኮኖሚ”) እንመሰርታለን ተባለ። ለጊዜውም ቢሆን፤ የግል ጋዜጣ ለማሳተም የሚቻልበት የፕሬስ ነፃነትን እናሰፍናለን ተባለ። ለኢህአዴግ፤ ይሄ ትልቅ አብዮት ነው።

1987/88 ዓ.ም ... እድሜ 40 አመት

ደርግን አሸንፎ ስልጣን የያዘው ኢህአዴግ፤ በ1987 ዓ.ም ህገመንግስት አፅድቋል። በቀጣዩ አመት ደግሞ፤ አቶ መለስ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ። በወቅቱ እንደ ትልቅ ለውጥ ባይታይም፤ “ለጊዜው” ተብለው የተጀመሩት “የሃሳብ ለውጦች” በህገመንግስቱ ቋሚ ሃሳብ ተደርገው ተካትተዋል። ብዙ ፓርቲዎች የሚሳተፉበት የፖለቲካ ስርዓት፤ የግል ቢዝነስ መስራትና ንብረት ማፍራት የሚፈቀድበት ኢኮኖሚ፤ የግል ጋዜጣ ማሳተም የሚፈቀድበት የፕሬስ ነፃነት... እነዚህ ሁሉ “ካፒታሊዝም ቀመስ” ሃሳቦች፤ በህገመንግስቱ ውስጥ በቋሚነት ተፅፈዋል። ይሄም ራሱን የቻለ አብዮት ነው - በዝምታ የተካሄደ አብዮት።

1992/93 ዓ.ም.... እድሜ 45

“ለጊዜው” ተብለው የተጀመሩት ሃሳቦች፤ “በዝምታ” ህገመንግስት ውስጥ በቋሚነት ቢካተቱም፤ ሁሉንም የኢህአዴግ መሪዎች የሚያስማሙ ሃሳቦች ሆነው አልተገኙም። በ1992/93 ዓ.ም ለተከሰተው የመሪዎች ፀብና ክፍፍል አንዱ መንስኤም፤ ከዚህ ነጥብ ጋር የተያያዘ ነው። የመሪዎቹ ክፍፍል፤ አቶ መለስን ከስልጣናቸው ለማውረድ ተቃርቦ እንደነበር በተደጋጋሚ ተነግሯል። በህገመንግስት ውስጥ የሰፈሩት “ካፒታሊዝም ቀመስ ሃሳቦች” ለረዥም ጊዜ የሚቀጥሉ ቋሚ መርሆች ናቸው? ወይስ ወደ ሶሻሊዝም ለመሸጋገር ምቹ አጋጣሚ እስኪፈጠር ድረስ የሚያገለግሉ ጊዜያዊ መርሆች ናቸው? በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የተከፋፈሉት የኢህአዴግ መሪዎች፤ ለበርካታ ወራት ተነታርከዋል፤ ተሰብስበዋል፤ ተገማግመዋል፤ በቃልና በፅሁፍ ተከራክረዋል - ለዚያውም የመፅሃፍ ያህል በረዛዘሙ የፅሁፍ ክርክሮች።

በአገሪቱ የምንገነባው የፖለቲካ ስርዓት፤ “ነጭ ካፒታሊዝም ነው” ብለው ተከራከሩ አቶ መለስ። እናም፤ ጊዜያዊ ተብለው የተጀመሩትና በዝምታ ህገመንግስት ውስጥ የተካተቱት ሃሳቦች፤ “ቋሚ ናቸው” ተባለ። በእርግጥ፤ በህገመንግስት ውስጥ የገቡት ሃሳቦች የተሟላ ነፃነትንና “ነጭ ካፒታሊዝምን” የሚያፍኑ አይደሉም። “ነፃነት ቀመስ፤ ካፒታሊዝም ቀመስ” ሃሳቦች ቢባሉ የተሻለ ነው። እንዲያም ሆኖ፤ ጠ/ሚ መለስ ካፒታሊዝምን እንገነባለን የሚለውን ሃሳብ በይፋ ይዘው መከራከራቸው፤ ለኢህአዴግና ለአገሪቱ እንደ አንድ ትልቅ አብዮት ሆኖ ሊቆጠር ይችላል።

በእርግጥም፤ ከ1993 ዓ.ም በኋላ በርካታ የቢዝነስና የኢንቨስትመንት መሰናክሎች እንዲሻሻሉ ተደርጓል። ኢኮኖሚውም ቀስ በቀስ ሲነቃቃ አይተናል። ይህም ብቻ አይደለም። የፕሬስ ነፃነት ከወትሮው በተሻለ ሁኔታ ሲከበርና ጋዜጦች እየበረከቱ ጥራታቸው ሲያድግ ተመልክተናል። ይህም ብቻ አይደለም። ሌላ ትልቅ ለውጥ አይተናል - በፖለቲካ ምርጫ።

1997/98 ዓ.ም ... እድሜ 50 አመት

ፓርቲዎች የሚሳተፉበት ብቻ ሳይሆን፤ የሚፎካከሩበት የፖለቲካ ምርጫ በ1997 ዓ.ም ለማየት መብቃታችን፤ “ራሱን የቻለ አብዮት ነው” ቢባል አትስማሙም? የያኔው አብዮት ግን፤ የፓርቲዎች ፉክክር የተሟሟቀበት የምረጡኝ ዘመቻንና የምርጫ ሂደትን ብቻ ሳይሆን፤ የምርጫ ቀውስንም አብሮ አስተናግዷል። ተስፋ የታየበት፤ ግን ደግሞ ብልጭ ያለው ብርሃን የደበዘዘበት አሳዛኝ ጊዜ ሆነና አለፈ።

2002/2003 ዓ.ም.... እድሜ 55 አመት

ፓርቲዎች የሚፎካከሩበት የ97ቱ አይነት ምርጫ አልነበረም - 2002ቱ። ፓርቲዎች የሚፎካከሩበትና ስልጣን ላይ የሚፈራረቁበት ሰላማዊ የፖለቲካ ስርዓት መገንባት ዘላቂ አላማችን ነው በማለት የተናገሩት ጠ/ሚ መለስ፤ ለጊዜው ግን ኢህአዴግ ውስጥ የስልጣን ሽግግር ማካሄድ አለብን የሚል ሃሳብ አስተጋብተዋል። በቀዳሚነት ከስልጣን ለመውረድም ጠይቀዋል - ፓርቲያቸው አልተቀበለውም እንጂ። ቢሆንም፤ እሳቸው በ2007 ዓ.ም በሚደረገው ምርጫ ላለመካፈል፤ በ2008 ዓ.ም ላይም ከስልጣን ለመውረድ ወስነው ነበር (በ60ኛ አመታቸው መሆኑ ነው)። ሌሎች በርካታ የድርጅቱ ነባር መሪዎች ግን፤ ከስልጣን ወርደው በአዳዲስ እንዲተኩ ተደርገዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳቀዱት ከስልጣን የሚወርዱበት ጊዜ ሳይደርስ በህመም ቢሞቱም፤ ያኔውኑ የመተካካት አብዮት መጀመራቸው ለዛሬው የተረጋጋ ሁኔታ አስተዋፅኦ አበርክቷል።

 

 

 

 

 

Read 2939 times Last modified on Saturday, 01 September 2012 09:28