Sunday, 01 September 2024 20:14

“የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የዕድሜ ማራዘምያ ነው”- እናት ፓርቲ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 “እጅ መንሻ የሚቀበሉ” ባለስልጣናቱን መንግስት አደብ እንዲያስገዛ ጠይቋል


       መንግስት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ማሻሻያው መድሃኒት ሳይሆን የዕድሜ ማራዘምያ ክኒን ነው ያለው እናት ፓርቲ፤ “እጅ መንሻ መቀበል ሥራዬ ብለው የያዙትን ባለስልጣናቱን መንግስት አደብ እንዲያስገዛ አሳስቧል ያስገዛ” ሲል እናት ፓርቲ አሳሰበ። ፓርቲው ባለፈው ሰኞ ነሐሴ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. ባወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ አጠቃላይ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ትችቷል።
“በያለፉት ስድስት ዓመታት ኢኮኖሚው ወዴት እንደሚሄድ ፍኖተ ካርታ ባለመቀመጡ ለትንበያ እንኳን እስከሚያስቸግር ድረስ ሲታመስ ቆይቷል፡፡” ያለው ፓርቲው፣ “በቅርበት ለሚከታተል ሰው ግን አንድ ቀን  የማይወጣው ማጥ ውስጥ ገብቶ ኢኮኖሚው በዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ጫና ውስጥ እንደሚወድቅ ሳይታለም የተፈታ ነበር፡፡” ብሏል።
“የገንዘብ የመግዛት አቅም መዳከም፣ ለምርት ግብዓት የሆኑት እንደማዳበሪያ፣ ትምሕርትና ጤና መሰል አገልግሎቶች ላይ የሚደረገው ድጎማ መቆም በህብረተሰቡ ላይ መጠነ ሰፊ ጫና እያሳረፈ ነው” የሚለው እናት፤ “ሰሚ በመጥፋቱ የማታ ማታ መንግስት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት ከነአደገኛ ግዴታዎቹ ብድር ለመውሰድ ተገድዷል” ብሏል።   
“እነዚህ ዓለምአቀፍ አበዳሪ ድርጅቶች ለደሃ የሚራራ ልብ የላቸውም። አሁን የአንድ ወታደር፣ የመንግስት ሰራተኛ፣ የአስተማሪ ደመወዝ በግማሽ ወርዷል። 11 ሺህ ብር ይከፈላቸው የነበሩ ሰራተኞች ደመወዛቸው 500 ዶላር ነበር፤” በአሁኑ የዶላር ምንዛሪ ይህ ደመወዝ 100 ዶላር ወይም ከዚያ በታች ሆኗል ብሏል በመግለጫው።
 “የሚፈራው ማሕበራዊ ቀውስ ሊታከም ከማይችልበት ደረጃ ከመድረሱ በፊት መንግስት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራውን እንደገና እንዲያጤነው”  መንግስትን ያሳሰበው እናት ፓርቲ፣ “መንግስት፤ የሰራተኛውና ደመወዝተኛው የዛሬ ስድስት ዓመቱ የኑሮ ደረጃን የሚመልሰውን የደመወዝ ጭማሪ በአስቸኳይ እንዲያደርግ” ጥሪውን አቅርቧል።
በናይጄሪያ፣ ኬንያ፣ ሱዳንና ግብጽን ጨምሮ በተለያዩ የዓለማችን አገራት “ዕድገትን ለማነሳሳት” ሲባል የተፈጸሙ የገንዘብ አቅርቦት መጨመርን የመሳሰሉ የማስፋፊያ የገንዘብ ፖሊሲዎች የተተለሙባቸውን የስራ አጥነትን ማስወገድ ዓላማ ሳያሳኩ፣  ከፍተኛ የዋጋ ንረት ማስከተላቸውንም ነው የፓርቲው መግለጫው የጠቀሰው። አያይዞም፣ “መንግስት ራሱ ፈቅዶና ፈርሞ ያመጣው ፖሊሲ የፈጠረውን ምስቅልቅል በነጋዴው ማሕበረሰብ ላይ እያመካኘ፣ ሱቅ ማሸግና እጅ መንሻ መቀበል ‘ስራዬ’ ብለው የያዙትን ባለስልጣናቱን አደብ እንዲያስገዛ” እናት ፓርቲ አሳስቧል፡፡

Read 639 times