Saturday, 06 July 2024 20:36

በአዲስ አበባ ከተማ የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሃግብር ተካሄደ

Written by 
Rate this item
(4 votes)

በአዲስ አበባ ከተማ የ2016 ዓ.ም. የአረንጓዴ አሻራ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር መካሄዱ ተገልጿል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት አዳነች አቤቤ፣ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፣ የአዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ጽሕፈት ቤት ሃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች፣ እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሕብረተሰብ ክፍሎች በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተዋል።

መርሃ ግብሩን በንግግር ያስጀመሩት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ "የምንተክለው ዛሬን አይደለም። ለነገም ጭምር ነው" ያሉ ሲሆን፣ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ መተባበርን እና በጋራ መስራትን በይፋ ያሳየ ስራ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

አክለውም፣ በአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴ የከተማዋ የደን ሽፋን ማደጉን በማውሳት፣ "ከባለፈው ዓመት በላቀ መጠን የመተከል እና የመከታተል ስራ መስራት አለብን" ብለዋል። እንዲሁም ችግኝ የመትከሉን ስራ ከማጠናከር ባሻገር የመንከባከብ ሂደት መከወን እንዳለበትም በአጽንዖት አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት 17 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች በከተማ አቀፍ ደረጃ እንደተተከሉ ያስረዱት ክብርት ከንቲባ አዳነች፣ በዘንድሮው የታቀደው 20 ሚሊዮን ስለመሆኑ ጠቅሰዋል። በተጨማሪም፣ "የችግኝ ተከላ ስራው በዓለም አቀፍ ስታንዳርድ ደረጃ ለማሳደግ በጋራ መስራት ይገባል" ሲሉ ነው የተናገሩት።

"በጋራ ስንተክል የምንተክለው ችግኝን ብቻ ሳይሆን መተባበር እና አብሮ የመስራትን አሻራ ጭምር ነው።" በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውበት እና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ይመኙሻል ታደሰ በበኩላቸው፣ የአረንጓዴ ልማት ከሌሎች መሰረተ ልማት ስራዎች ጋር አብሮ የሚሰራ መሆኑን በመጥቀስ፣ "ባለፉት አምስት ዓመታት ዜጎች ያለልዩነት አገር በቀል እጽዋት፣ የውበት እጽዋት፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ እጽዋት ተክለዋል" ብለዋል።

በእነዚሁ ዓመታት በከተማ አስተዳደሩ አማካይነት ከ58 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ችግኞች እንደተተከሉ የገለጹት የቢሮ ሃላፊዋ፣ የእነዚህ ችግኞች 89 በመቶ የጽድቀት መጠን ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።

ወደፊት በአምስት ኮሪደሮች ተለይቶ የሚሰራ ስራ እንደሚኖር የገለጹ ሲሆን፣ "የተገኙ ድሎች ላይ ሳንኮራ ሌሎች ስራዎችን መስራት ያስፈልጋል" ነው ያሉት።

"ለችግኞች ተገቢውን እንክብካቤ ካላደረግን ወልዶ እንደመጣል ይቆጠራል" ሲሉ የተተከሉ ችግኞችን መንከባከብ እንደሚያስፈልግ በአንክሮ ተናግረዋል። እስከዛሬ ለተገኙ ስኬቶች ባለድርሻ አካላትን፣ በተለይም ክብርት ከንቲባ እና አስተባባሪ ኮሚቴውን አመስግነዋቸዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም. ከነበረበት 2 ነጥብ 8 በመቶ ወደ 17 በመቶ ከፍ እንዳለ በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይ ተገልጿል።

በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የችግኝ ተከላ ስነ ስርዓት አከናውነዋል።

"የምትተክል አገር፣ የሚያጸና ትውልድ" በሚል መሪ ቃል የተጀመረው ሁለተኛ ምዕራፍ፣ ሁለተኛው ዙር የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል።

Read 693 times