Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 07 April 2012 09:02

ይህች ናት አገርህ!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የባል ድብደባን ጨምሮ ከትዳር እስከ ሱስ ድረስ፤ የጉዲፈቻ ልጆች ቁጥርን ጨምሮ ከወሊድ ብዛት እስከ ትምህርት ደረጃ ድረስ... ብዙ ነገሮችን ይዳስሳል - ሰሞኑን በይፋ የተሰራጨው የጥናት ሪፖርት። በ450 ገፅ የቀረበው ጥናት፤ የህዝብ እና የጤና ዳሰሳ በሚል ይታወቃል። ጥናቱ በየአምስት አመቱ የሚካሄድ ሲሆን፤ ከሌሎች የአገራችን ጥናቶች ይልቅ በእጅጉ የተሻለ ጥራትና ተአማኒነት እንዳለው ይነገርለታል። እኔም በተራዬ የዳሰሳ ጥናቱን በመዳሰስ፤ የተወሰኑ መረጃዎችን ላካፍላችሁ።

ሲጋራ፣ አልኮልና ጫት

የሲጋራ ወይም የቶባኮ ልምድ በሰፊው የሚታየው በአዲስ አበባ ሊመስለን ይችላል። ግን አይደለም። ሰሞኑን ይፋ የሆነው የህዝብ እና የጤና ዳሰሳ ሪፖርት እንደሚገልፀው፤ ሲጋራና ቶባኮ በጣም የተስፋፋው በሃረሪ፣ በሶማሌ፣ በአፋር እና በድሬዳዋ እንደሆነ  ይገልፃል። ከ15 አመት እድሜ በላይ ከሆናቸው ወንዶች መካከል፤ ቢያንስ ሃያዎቹ እንደሚያጨሱ ጥናቱ ይጠቁማል። በአዲስ አበባ ግን፤ የሲጋራ ልምድ በስምንት በመቶ ያህሉ ወንዶች ላይ ይታያል። ብዙም ያልተስፋፋባቸው ክልሎች ትግራይ፤ አማራ እና ደቡብ ናቸው - ከሶስት በመቶ በታች ተመዝግቦባቸዋል (ገፅ 71)።

በአልኮል በኩል፤ ነገሩ ሁሉ የተገላቢጦሽ ይመስላል። በመጠጥ ፍጆታ ቀዳሚዎቹ ክልሎች ትግራይና አማራ ናቸው - ከመቶ ወንዶች መካከል፤ 55ቱ በወር ውስጥ ቢያንስ ስድስት ቀን ይጠጣሉ። ቢያንስ በ5 ቀን አንዴ እንደማለት ነው። አፋርና ሶማሌ ግን፤ ያን ያህልም መጠጥ አይዘወተርባቸውም። በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ፤ ከጎረምሳው ጀምሮ እስከ አዛውንቱ ድረስ፤ ከመቶ ወንዶች መካከል 29 ያህሉ፤ በወር ውስጥ  ስድስት ቀን ወይም ከዚያ በላይ ይጠጣል። መጠጥ የሚያዘወትሩ ተብለው ሊጠቀሱ ይችላሉ (ገፅ 72-73)።

ለነገሩ የሴቶችም ቀላል አይደለም። ከወጣት እስከ አዛውንት ድረስ፤ ከመቶ ሴቶች መካከል 20ዎቹ መጠጥ ያዘወትራሉ። በትግራይ 37 በመቶ፤ በአማራ 50 በመቶ ያህሉ ሴቶች መጠጥ ሲያዘወትሩ፤ በአዲስ አበባ ግን ከመቶ ሴቶች አምስቱ ናቸው አዘውታሪዎች። በጥቅሉ ሲታይ፤ መጠጥ ከቀመሱ ሰዎች መካከል ግማሾቹ፤ መጠጥ አዘውታሪ እንደሚሆኑ ጥናቱ ያረጋግጣል። ሱስ የሚያስይዙ ነገሮች ላይ የሚስተዋል የተለመደ የሰዎች ባህርይ ነው - ማዘውተር። ጫትን ማየት ይቻላል።

ጫት ቀምሰው ከሚያውቁ ሰዎች መካከል ግማሾቹ የጫት አዘውታሪ ሆነዋል - በወር ቢያንስ 6 ቀን ጫት ይቅማሉ። በጫት በኩል ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት፤ ሃረሪ፣ ድሬዳዋ፣ ሶማሌ እና ኦሮሚያ ናቸው። በሃረር፤ ከመቶ ወንዶች መካከል ስድሳ አምስቱ ጫት ያዘወትራሉ፤ (በድሬዳዋ 55ቱ፤ በሶማሌ 40 በመቶ፣ በኦሮሚያ 30 በመቶ)። የአዲስ አበባ 10 በመቶ ገደማ ነው - የአዘውታሪ ወንዶች ቁጥር። በአጠቃላይ በአገር ደረጃ ከመቶ ወንዶች መካከል 15ቱ፤ ከመቶ ሴቶች 5ቱ የጫት ደንበኛ ሆነዋል - በወር ቢያንስ ስድስት ቀን ይቅማሉ። ጫት አዘውታሪ ሴቶች የሚበዙት በሃረር ነው፤ ከዚያም በድሬዳዋና በኦሮሚያ (ገፅ 74-75)።

በጣም የሚያስገርመው የሲጋራ ልማድ፤ በከተማና በገጠር በጣም ተቀራራቢ ነው። በከተማ፤ ከመቶ ወንዶች መካከል ዘጠኙ ሲጋራ ወይም ቶባኮ የቀመሱ ናቸው፤ በገጠር ደግሞ ስምንቱ። ቀምሰውም አልተዉትም። በከተማ ስምንቱ በገጠር ደግሞ ስድስቱ፤ በቀን ከ3 ሲጋራ በላይ እንደሚያጨሱ ጥናቱ ይጠቁማል።

መጠጥና ጫት የማዘውተር ልማድ ግን፤ በገጠር ይብሳል። መጠጥ የሚያዘወትሩ ሴቶች በገጠር 24 በመቶ፤ በከተማ 14 በመቶ ሲሆኑ፤ መጠጥ አዘውታሪ ወንዶች ደግሞ፤ በገጠር 29 በመቶ በከተማ 24 በመቶ ናቸው። ከተማሩት ይልቅም ባልተማሩት ላይ ይጎላል። ካልተማሩት መካከል 41 በመቶ ያህል፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ከጨረሱት መካከል ደግሞ 18 በመቶ ያህሉ መጠጥ ያዘወትራሉ። የሲጋራ ሱስም፤ ባልተማሩት ላይ እንደሚብስ ጥናቱ ያሳያል።

 

ሚስትን መደብደብ - ዳቦውን ካሳረረች

ባል በአንዳች ምክንያት ሚስቱን ቢደበድብ ተገቢ ሊሆን ይችላል ብለው የሚያስቡ ኢትዮጵያውያን ጥቂት አይደሉም። ከመቶ ኢትዮጵያዊያን ሴቶች መካከል ወደ ሰባ ያህሉ፤ በዚህ ሃሳብ እንደሚስማሙ ጥናቱ ይገልፃል። ተስፋ አስቆራጩ ነገር ምን መሰላችሁ? በአዛውንቶቹና በወጣቶቹ መካከል ያን ያህልም ሰፊ የአስተሳሰብ ልዩነት የለም። ለምሳሌ ከ45 አመት በላይ ከሆናቸው ሴቶች መካከል 74 በመቶዎቹ፤ የባል ድብደባ ተገቢ ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ። ሃያ አራት አመት ከማይሞላቸው ወጣቶችስ፤ ስንቶቹ ይህን አስተሳሰብ ይከተላሉ? 64 በመቶዎቹ።

ሚስትን ሊያስደበድቡ ይችላሉ ተብለው የተጠቀሱትን አምስት ምክንያቶች ተመልከቱ። ለምሳሌ ምግብ ቢያርባትና ባሏ ቢደበድባት ተገቢ ነው? ከመቶ ሴቶች መካከል 47ቱ፡ “አዎ ተገቢ ነው” ብለው ያምናሉ። ከባሏ ጋር ከተከራከረችም እንዲሁ፤ ተገቢ የድብደባ ምክንያት እንደሚሆን ያስባሉ፤ 45 በመቶ ያህሉ። የት እንደምትሄድ ሳትናገር ከቤት ወጣ ካለችም ያስደበድባታል። ህፃኑን ልጅ ችላ ብላለች በሚል ምክንያትም፤ ባል ሚስቱን ቢደበድብ ተገቢ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ (52 በመቶ ያህሉ)።

ከሁሉም በላይ ግን፤ ሚስት ለወሲብ ፈቃደኛ ካልሆነች ልትደበደብ ይገባታል በማለት 68 በመቶ ያህሉ ሴቶች ሃሳባቸውን ገልፀዋል። ይሄ ሁሉ ሰው የእለት ተእለት ድብደባንና ስቃይን በሚደግፍበት አገር፤ የሰውን መብትና ነፃነት የሚያከብር መንግስትና ስርአት በአንዳች ተአምር እንዲመጣ መጠበቅ የዋህነት አይመስላችሁም?

ብዙም ባይሆን ትንሽ የተስፋ ብርሃን የሚታየው በከተሞች አካባቢ ነው። በገጠር፤ ከመቶ ሴቶች መካከል 75ቱ የባል ድብደባ ተገቢ ሊሆን እንደሚችል ያምናሉ፤ በከተሞች ደግሞ 45 በመቶ ያህሉ። የድብደባ እምነት ይበልጥ ተስፋፍቶ የሚታየው፤ በሶማሌ፤ በደቡብ፤ በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች ሲሆን፤ አዲስ አባባ ከሁሉም ትሻላለች፤ 24 በመቶ ሴቶች ናቸው ድብደባን የሚፈቅዱት።

በአገር ደረጃ፤ ከሴቶች መካከል 68 በመቶ ያህሉ ድብደባውን ይፈቅዱ የለ? ሊገርማችሁ ቢችልም፤ ባል ሚስቱን ቢደበድብ ተገቢ ሊሆን ይችላል ብለው የሚያስቡ ወንዶች ግን 45 በመቶ ያህሉ ናቸው። (በገጠር 50 በመቶ፤ በከተማ ደግሞ 25 በመቶ)። (ገፅ 276-78)

 

የገጠሬውና የከተሜው ጎጆ ይመሳሰላሉ?

በአብዛኛው ከተሜና በአብዛኛው ገጠሬ መካከል አንዳንድ ጉልህ ልዩነቶች ቢታዩም፤ የዚያኑ ያህልም አኗኗራቸው ይመሳሰላል። እንግዲህ በገጠር 15 ሚሊዮን በከተማ ደግሞ ከ3.5 ሚ. በላይ ቤተሰቦች እንዳሉ ይገመት የለ? ብዙዎቹ በመኖሪያ ቤቶቻቸው ሁኔታ ይመሳሰላሉ።

እንደሚገመተው፤ በገጠር ከ95 በመቶ ያህል መኖሪያ ቤቶች፤ ወለላቸው በጭቃ ወይም በእበት የተለቀለቀ ነው። በከተማም፤ 48 በመቶ ያህሉ፤ የጭቃና የእበት ወለል ውስጥ ይኖራሉ (ገፅ 37)። ግቢ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ቤት ውስጥ ድረስ የውሃ ቧንቧ የገባላቸው የከተማ መኖሪያ ቤቶች አራት በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ። ለብቻ የመፀዳጃ ቤት ያላቸው ከተሜ ቤተሰቦች ከ14 በመቶ አይበልጡም። በውሃ የሚቸለስ መፀዳጃ ቤት ያላቸውማ፤ አራት በመቶ ብቻ ናቸው።(ገፅ 36) ከግማሽ በላይ የሚሆኑ የከተማ ቤተሰቦች፤ ለንፅህና የሚመች መፀዳጃ ቤት የላቸውም።

መኝታ ቤትም፤ እንደ ገጠሩ ሁሉ በከተማም ችግር ነው። በገጠር፤ 71 በመቶ ያህል ቤተሰብ ከአንድ ክፍል በላይ መኝታ ቤት የለውም። ቤተሰቡ ሁሉ እዚያችው ውስጥ ታጉሮ ይታኛል። በከተማ ደግሞ፤ 68 በመቶው ቤተሰብ፤ በአንድ መንታ ቤት ያድራል።

 

ድህነትና ወሊድ አብሮ ይጨምራል

ባለፉት አምስት አመታት የወሊድ መጠን እንደቀነሰ የሚገልፀው የህዝብና የጤና ዳሰሳ ጥናት፤ በተለይ በአዲስ አበባ የወሊድ መጠን በጣም ዝቅተኛ ከመሆኑ የተነሳ የነዋሪውን ቁጥር ለመተካት የሚበቃ እንዳልሆነ ያመለክታል።

1993 አ.ም ተደርጎ የነበረው ተመሳሳይ ጥናት እንደሚያመለክተው፤ በአማካይ አስር ሴቶች በህይወት ዘመናቸው 55 ልጆችን ይወልዱ ነበር። በ1998ቱ ጥናት የተገኘው ውጤትም ተቀራራቢ ነው። አስር ሴቶች ለ54 ልጆች። አዲሱ የጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው ግን፤ ባለፉት አምስት አመታት የሴቶች የወሊድ መጠን ቀንሷል። በአማካይ አስር ሴቶች በህይወት ዘመናቸው፤ 48 ልጆችን ይወልዳሉ ይላል ጥናቱ።

በእርግጥ፤ የወሊድ መጠን በከተማና በገጠር ይለያያል። እንደ ሴቶቹ የትምህርት ደረጃም፤ በእጅጉ ይራራቃል።

በከተማ አካባቢዎች፤ አስር ሴቶች በአማካይ 22 ልጆችን ይወልዳሉ። በገጠር ደግሞ 55 ልጆችን። በጣም ዝቅተኛው የወሊድ መጠን የአዲስ አበባ ነው። አስር የአዲስ አበባ ሴቶች፤ በእድሜ ዘመናቸው 15 ልጆችን ነው የሚወልዱት። ምናልባትም በአውሮፓና በአሜሪካ ከሚታየው ዝቅተኛ የወሊድ መጠን ጋር ይቀራረባል ማለት ይቻላል። ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ አዲስ አባባ የሚፈልሱ ሰዎች ባይኖሩ ኖሮ፤ አሁን ባለው የወሊድ መጠን የከተማዋ ነዋሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየቀነሱ ይሄድ ነበር። በሃምሳ አመታት ውስጥ በ25 በመቶ ያህል ሲቀንስ ይታያችሁ።

በወሊድ መጠን ላይ ከፍተኛ ለውጥ የሚያመጣው ምን መሰላችሁ? የትምህርት ደረጃ ነው። ጥናቱ እንደሚለው ከሆነ 10 ያልተማሩ ሴቶች በአማካይ በህይወት ዘመናቸው ወደ 60 የሚጠጉ ልጆችን ይወልዳሉ። ከሃይስኩል በላይ አለፍ ብለው የተማሩ አስር ሴቶች፤ በህይወት ዘመናቸው 13 ልጆችን ብቻ ይወልዳሉ።

ሃብትና ድህነትም እንዲሁ፤ ያለያያል። የቤተሰቡ ሃብት ዝቅተኛ በሆነ ቁጥር፤ የወሊድ መጠኑ ከፍ እንደሚል ጥናቱ ይገልፃል። በድሃዎቹ ሰፈር፤ አስር ሴቶች 60 ልጆችን ይወልዳሉ፤ በሃብታሞቹ ሰፈር ግን 28 ልጆችን ብቻ።

 

የቀጨጩ ከሲታ ልጆች

ህፃናት ምን ያህል በምግብ እጥረትና እጦት እንደሚሰቃዩ ለማወቅ፤ የህፃናቱን አካልና ሰውነት ማየት ሁነኛ ዘዴ ነው። እስከ አምስት አመት እድሜ ድረስ ያሉ ህፃናትን በተመለከተ ጥናቱ ያቀረበው ሪፖርት፤ ግማሽ ያህሉ ልጆች የቀጨጩ እንደሆኑ ይገልፃል። ከመቶ ህፃናት መካከል 44ቱ ቀጭጨዋል። መሆን ከሚገባው በታች እጅጉን አጭር ናቸው። እንደ እድሜያቸው አልረዘሙም። ይህም ለረዠም ጊዜ ስር በሰደደ የምግብ እጥረት እንደሚሰቃዩ ያመለክታል። በዚያው መጠንም፤ በየጊዜው በሚያገረሹ ተደጋጋሚ በሽታዎች እንደሚጠቁ ጥናቱ ይገልፃል (ገፅ 176)።

ህፃናት፤ ሻል ያለ እድል የሚያገኙት በአዲስ አበባ፣ በጋምቤላ እና በሃረር እንደሆነ የሚገልፀው ይሄው ጥናት፤ የመቀጨጭ ጉዳት ጫን ብሎ የሚታየው፤ በአማራ፤ በትግራይ እና በአፋር ክልሎች እንደሆነ ያመለክታል (ከህፃናቱ መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የቀጨጩ ናቸው)።

ክፉኛ በምግብ እጦት የሚሰቃዩም አሉ። ከመቶ ህፃናት መካከል፤ 10 ያህሉ እጅጉን ከሲታ ናቸው (ገፅ 179)። የህፃናቱ ክሳት፤ ጥናቱ በተካሄደበት ወቅት የነበረውን ክፉ የምግብ እጦት የሚያሳይ ሲሆን፤ በአፋርና በሶማሌ ክልሎች በጣም ጎልቶ ይታያል (ቢያንስ 20 በመቶ ህፃናት ከሲታ ሆነዋል)። በመላ አገሪቱ ወፍራም ናቸው ሊባሉ የሚችሉት ህፃናት ጥቂት ናቸው። ከመቶ ህፃናት መካከል ሁለቱ ብቻ ወፍራም ይሆናሉ። በአዲስ አበባ ግን፤ ስድስት መቶ ያህሉ ወፍራም ናቸው።

የአዋቂዎች ክሳትና ውፍረትም ተመሳሳይ አዝማሚያዎችን ያሳያል - ጥናቱ። በመላ አገሪቱ፤ 67 በመቶ ሴቶችና 61 በመቶ ወንዶች ተመጣጣኝ የሰውነት ሁኔታ እንዳላቸው ጥናቱ ገልፆ፤ 22 በመቶ ሴቶች እና 34 በመቶ ወንዶች ከሲታ እንደሆኑ ያመለክታል። ከመቶ ወንዶች ስድስቱ ወፍራም ሲሆኑ ከሴቶች አስራ አንዱ ወፍራም ሆነዋል። የሁሉም ከተሞችና ክልሎች ሁኔታ እጅግ ተቀራራቢ ቢሆንም፤ በተወሰነ ደረጃ አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ሃረር እና ደቡብ ክልል ሻል ይላሉ። ሶማሌ፣ አፋር፣ ትግራይና አማራ ላይ ደግሞ ከሲታነት በርከት ይላል። አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሃረር ለየት ብለው የሚታዩት በወፍራሞች ብዛት ነው። በአዲስ አበባ ከመቶ ሴቶች መካከል አርባዎቹ ወፍራም ናቸው ማለት ይቻላል፤ ከወንዶች ደግሞ 25ቱ። (ገፅ 200-03)

 

ኤችአይቪ - ከወንዶች ይልቅ በሴቶች ላይ

በአጠቃላይ በአገሪቱ ውስጥ፣ ከአንድ ሺ ወንዶች መካከል አስሩ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ እንደሆኑ የሚገልፀው ይሄው ጥናት፤ ከአንድ ሺ ሴቶች መካከል ደግሞ 19 ያህሉ ፖዘቲቭ ናቸው ይላል (ገፅ 254)። ይሄው ውጤት በእድሜ የተከለለ እንደሆነ አትርሱ - ከ15 እስከ 49 አመት እድሜ የሆናቸውን ሰዎች ብቻ ያካትታል።

የኤችአይቪ ስርጭት፤ ከገጠር ይልቅ በከተሞች ከ6 እጥፍ በላይ ይልቃል። በከተማ፤ ከአንድ ሺ ሴቶች መካከል 52ቱ፤ ከአንድ ሺ ከተሜ ወንዶች ደግሞ 29 ያህሉ ኤችአይቪ ፖዘቲቭ እንደሆኑ ጥናቱ አመልክቷል። በጋምቤላ ግን፤ የኤችአይቪ ስርጭት ከአዲስ አበባም ይበልጣል። በተለይ ከ15 እስከ 24 አመት እድሜ ባላቸው ወጣቶች ዘንድ፤ በሌሎች ከተሞችና ክልሎች የኤችአይቪ ስርጭት ከሁለት በመቶ በታች ቢሆንም በጋምቤላ ግን ዘጠኝ በመቶ ነው (ገፅ 259)። በነገራችን ላይ ከወንዶች መካከል 37 በመቶ እንዲሁም ከሴቶች 36 በመቶ፤ ከጥናቱ በፊት ቢያንስ አንዴ የኤችአይቪ ምርመራ አድርገዋል።

ለዚሁ ጥናት ሲባል የኤችአይቪ ምርመራ እንዲያደረጉ ከተጠየቁ በርካታ ሺ ሰዎች መካከል፤ ወንዶች 82 በመቶ፤ ሴቶች 89 በመቶ ፈቃደኛ ሆነዋል። ይበልጥ ፍቃደኝነት በማሳየት ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዘው አዲስ አበባ ሊሆን ይችላል ብለን እንገምት ይሆናል። ነገር ግን፤ በዚህ በኩል አዲስ አበባ ዝቅተኛ ሆኗል፤ ከሶማሌ ክልል ጋር። ከፍተኛ የምርመራ ፈቃደኝነት የሚታየው በኦሮሚያና በትግራይ ነው (በአጠቃላይ ከከተማ ይልቅ በገጠር)። ከተማሩት ይልቅም ባልተማሩት ዘንድ የምርመራ ፈቃደኝነት ከፍ ይላል። ምናልባት፤ የኤችአይቪ ምርመራውን እንደመንግስት ትእዛዝ ስለቆጠሩት ይሆን? የተማሩና ከተሜ ሰዎች ላይ፤ “እምቢ” የማለት ነፃነትና ድፍረት በመጠኑ ሰፋ ስለሚል ሊሆን ይችላል።

ከመቶ ወንዶች መካከል 92ቱ የተገረዙ እንደሆኑ ጥናቱ ገልፆ፤ 61 በመቶ ያህሉ አምስት አመታቸው ሳይሞላ የተገረዙ እንደሆኑ ይጠቅሳል። ግርዘት የሚካሄደው በአብዛኛው በልምድ ሰዎች ነው ተብሏል። ግርዘት ለኤችአይቪ ከመጋለጥ ጋር ያለው ግንኙነት ግልፅ ባይሆንም፤ በጎልማሶች ዘንድ ግን ልዩነት የሚያመጣ ይመስላል - የኤችአይቪ ስርጭት፤ ባልተገረዙ ወንዶች ዘንድ ከፍ ይላልና (ገፅ 262)።

 

ከሴተኛ አዳሪ ጋር

ከመቶ ወንዶች መካከል ስድስቱ በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንዴ ከሴተኛ አዳሪ ጋር መተኛታቸውን እንደተናገሩ የሚገልፀው ይሄው ጥናት፤ ጋምቤላ፤ ትግራይ፤ አዲስ አበባና ድሬዳዋ ላይ በርከት እንደሚል ያስረዳል። ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በጋምቤላ ነው፤ መቶ ወንዶች መካከል 15ቱ ከሆነ ጊዜ ከሴተኛ አዳሪ ጋር ተኝተዋል። ዝቅተኛ ቁጥር የተመዘገበው፤ በሶማሌ፣ በሃረር፣ በአፋርና በኦሮሚያ ነው። በከተሜና በገጠሬ ወንዶች መካከል ልዩነት አለ። በከተማ ከመቶ ወንዶ አስሩ፤ በገጠር ደግሞ ከመቶ ሰዎች አራቱ፤ ከሴተኛ አዳሪ ጋር የወሲብ ገጠመኝ አላቸው።

 

የጋብቻ እድሜ ዛሬና ድሮ

ከ30 አመት በፊት፤ ከመቶ ሴቶች መካከል አርባ ያህሉ በ15 አመት እድሜያቸው ያገቡ ነበር። እንዲህ አይነቱ ልምድ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ ጥናት የሚገልፅ ሲሆን፤ ዛሬ በ15 አመት እድሜያቸው የሚያገቡ ሴቶች ከመቶ አስር አይሞሉም። ቢሆንም ግን፤ 25 አመት ከሞላቸው ሴቶች መካከል ስድሳ በመቶ ያህሉ አግብተዋል። ተመሳሳይ እድሜ ላይ ከደረሱት ወንዶች መካከል ግን 14 በመቶ ያህሉ ናቸው ያገቡት።

ያለ እድሜ ጋብቻ እየቀነሰ እንደመጣው ሁሉ፤ ያለ እድሜ ወሲብም ቀንሷል ይላል ጥናቱ።  ከሰላሳ አመት በፊት ከመቶ ሴቶች አርባዎቹ በ15 አመት እድሜያቸው ወሲብ ይጀምሩ የነበረ ቢሆንም፤ ዛሬ ሰባቱ ብቻ ናቸው በዚያ እድሜ ከወሲብ ጋር የሚተዋወቁት። ያለ እድሜ ወሲብ የሚጀምሩት ሴቶች በአብዛኛው ያለ እድሜ ጋብቻ ለመፈፀም የሚገደዱ ሴቶች ናቸው። ጋብቻ ሳይፈፅሙ በ15 አመት እድሜያቸው ወሲብ የምትጀምር ሴት ከመቶ አንድ ቢሆን ነው።

በ18 አመት እድሜ ከወሲብ ጋር የሚተዋወቁ ወጣቶች ግን በርካታ ናቸው፤ ከመቶ ወጣት ሴቶች መካከል 32ቱ። የብዙዎቹም ከጋብቻ ጋር ነው። ያላገቡ ወጣት ሴቶች ግን፤ ከመቶ መካከል ሶስቱ ብቻ በ18 አመት እድሜያቸው ወሲብ ይጀምራሉ፤ ከወንዶች ደግሞ ዘጠኙ። እድሜያቸው 24 አመት ሲደርስ ግን፤ ከወሲብ ጋር የሚተዋወቁ ወጣቶች ቁጥር ይጨምራል። በዚህ እድሜ ክልል ከሚገኙ ያላገቡ ሴቶች መካከል 19 በመቶ፤ ከወንዶች ደግሞ 35 በመቶ ያህሉ ወሲብ ፈፅመዋል። ከሴቶቹ 12 በመቶ ከወንዶቹ 23 በመቶ፤ ቢያንስ በአመት ውስጥ አንዴ ወሲብ ፈፅመዋል። የወንዶቹ ቁጥር እስከ ሃያ በመቶ ይደርሳል። (ገፅ 236-40)

 

አባወራ፤ እማወራ

ኢትዮጵያ ውስጥ ጋብቻ ከመሰረቱት መቶ ሴቶች መካከል፤ 11 ያህሉ በቤተሰቡ ውስጥ ብቸኛ ሚስት አይደሉም። ተደራቢ ሚስት ናቸው። ለምን ቢባል፤ አንድ ወንድ በርካታ ሚስቶችን ያገባልና ነው።

አባወራ የሌላቸው ቤተሰቦች ጥቂት አይደሉም። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው። ከመቶ ቤተሰቦች መካከል 25ቱ በእማወራ የሚተዳደሩ ናቸው ይላል ጥናቱ። የከተማው ብቻ ከታየ ደግሞ፤ ከመቶ ቤተሰቦች መካከል 36ቱ በሴት ይተዳደራሉ። (ገፅ 42)

 

ልጆችና ቤተሰቦች

በመላ አገሪቱ ከሚገኙ ቤተሰቦች መካከል፤ 19 በመቶ ያህሉ ውስጠ ቢያንስ አንድ የማደጎ ልጅ እንዳለ ጥናቱ ይጠቅሳል።  3.5 ሚ. የሚሆኑ ቤተሰቦች ውስጥ የማደጎ ልጆች ይኖራሉ ማለት ነው።

ጥናቱ እንደሚገልፀው፤ በአዲስ አበባ ከአባትና ከእናት ጋር የሚኖሩ ልጆች፤ 52 በመቶ ያህል ናቸው። ከጠቅላላ የአገሪቱ ልጆች መካከል፤ 72 በመቶ ከአባትና ከእናት ጋር ይኖራሉ። 14 በመቶ ከእናት ጋር፣ 3 በመቶ ከአባት ጋር፣ 11 በመቶ ደግሞ ከሌላ ሰው ጋር ይኖራሉ። 11 በመቶ ማለት፤ ከ4 ሚ. በላይ ልጆች ማለት ነው - ከወላጆቻቸው ጋር የማይኖሩ። ከእነዚህ ውስጥ ከ300ሺ በላይ የሚሆኑት ልጆች፤ እናትና አባታቸውን በሞት ያጡ ናቸው (ገፅ 41 -48)።

ወላጆችን በሞት ማጣት ከባድ ፈተና ቢሆንም፤ አብዛኞቹ ከትምህርት ቤት አልቀሩም 70 በመቶ ያህሎቹ እንደሚማሩ ጥናቱ ይጠቁማል። ሌሎች ህፃናት 76 በመቶ ያህል ይማራሉ። (በተለይ በከተማ ደግሞ፤ 93 በመቶዎቹ ያህል ይማራሉ። ከሌሎች ህፃናት ጋር ብዙም አይራራቅም - 94 በመቶ ነውና)።

ተማር ልጄ

ትምህርት... አስቸጋሪ ነገር ነው። ልጆች፤ ከ7 አመት እስከ እስከ 14 አመት እድሜያቸው ድረስ፤ የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ መገኘት አለባቸው አይደል? ግን ሁሉም ት/ቤት ውስጥ አልገቡም። ሌላው ቀርቶ በአዲስ አበባ እንኳ፤ 84 በመቶዎቹ ያህል ናቸው ት/ቤት የገቡት። ከዚያ በመቀጠል ከፍተኛው ቁጥር የተመዘገበው በጋምቤላ ነው - 81 በመቶ። በገጠር አካባቢዎች ደግሞ ስድሳ በመቶ። ዝቅተኛ ደረጃ የሚታየው በአፋር ክልል ነው 52 በመቶ። አንድ ጥሩ ምልክት ግን፤ እንደድሮው በሴቶችና በወንዶች ህፃናት መካከል ብዙም ልዩነት አለመኖሩ ነው። እንዲያውም በብዙ ቦታዎች የሴት ተማሪዎች ቁጥር ይበልጣል።

ከስምንተኛ ክፍል በኋላስ?  ከ14 እስከ 18  አመት እድሜ ያላቸው ታዳጊዎች፤ በሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት መገኘት የለባቸውም? ግን በዚህ እድሜያቸው የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ ገብተው የሚገኙት ከመቶ ታዳጊዎች 14ቱ ብቻ ናቸው። በጣም የተሻለ ሆኖ በሚታየው በአዲስ አበባ እንኳ፤ ከመቶ ታዳጊዎች ውስጥ 35ቱን ብቻ በሃይስኩል ውስጥ እንደምናገኛቸው ጥናቱ ያሳያል (50)። በእርግጥ ጥናቱ ከዚህ ጋር የሚጋጭ የሚመስል መረጃ በዚያው ገፅ አስፍሯል።

ከአዲስ አበባ በሚበልጥ ሁኔታ ትምህርት የተስፋፋበት አካባቢ በጥናቱ ላይ አልተጠቀሰም። ነገር ግን፤ የከተሞችን መረጃ በጥቅሉ ሲያሰፍር፤ ከመቶ ከተሜ ታዳጊዎች መካከል 39 ያህሉ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ውስጥ እንደሚገኙ ይገልፃል። ስህተት መሆን አለበት። ከተማ ውስጥ በጣም የተሻለ ኑሮ መስርተዋል በሚባሉት ቤተሰቦች ውስጥ እንኳ፤ የዚህን ያህል ውጤት እንዳልተመዘገበ የጥናቱ መረጃ ያመለክታል።

በአማካይ በቀን ለአራት ሰአታት ቤት ውስጥ በስራ የሚጠመዱ ወይም በክፍያም ሆነ ያለክፍያ በቤተሰብ ውጭ የሚሰሩ ህፃናት በርካታ ናቸው (ከመቶ 27ቱ)። ስራው የሚያመዝነው በወንድ ህፃናት ላይ እንደሆነ የሚገልፀው ጥናት፤ ከከተሜዎች ይልቅም በገጠሬዎች ላይ በስፋት ይታያል። ለህፃናት ብዙ የስራ ሸክም የማይታየው በአዲስ አበባ ነው። ከመቶ ህፃናት መካከል ሰባቱ ብቻ ናቸው የስራ ጫና የሚበረታባቸው። ሃረርና ድሬዳዋ ደህና ነውጫናው የሚከብደው ደግሞ በትግራይ ነው - ከመቶ ህፃናት መካከል 42ቱ ከባድ የስራ ጫና አለባቸው።

 

 

Read 3946 times Last modified on Saturday, 07 April 2012 09:04