Wednesday, 04 April 2012 07:23

ከመምህራን “የደመወዝ ጭማሪ” ጀርባ፣ “ሌላ ወግ”

Written by  ናርዶስ ጂ.
Rate this item
(1 Vote)

ወዳጄ መምህሩ ሰሞኑን ካለወትሮህ ብስጭትጭት ማለትህን ሣይ ኑሮህን በመራራ ጽሑፍ ላጠለሸው አልደፈርኩም፤ የየዕለት እውነትህ ደግሜ በደረቁ፣ በወረቀት ሁዳዴ ላይ ልዘራው አልፈለግኩም፤ ወይም፣ አንተ ሆድ ብሶህ በየአስኳላ ቤትህ እያለቃቀስክ እያየሁ ከነጭራሹ ዝም ልለም አልችልም፤ እቺን ወግ የመከትክበትን ፊደላት እንኳ የቆጠርኩት በአንተ ነውና፣ የአንተ ነገር ጆሮ ዳባ ልበስ ብዬ በዝምታዬ አሸምቅብህ ዘንድ አንተ የፈጠርክብኝ የሕሊና ዳኝነት አልፈቀደልኝም…ከሁሉም በላይ ግን የአንተን ቃል ቃሌ፣ የአንተን ግብር ግብሬ ብዬ የአንተን ጐዳና መርጬ ነበርና የብስጭትህና የቁጣህ ጦር፣ ውስጤን በጨረፍታ ሳይሆን፣ መሀል ለመሀል ነው የሰነጠቀው፡፡ በአጭሩ እኔም፣ የትላንት ተማሪህ፣ የዛሬ “የሙያ” ተጋሪህ ነኝና ውስጥህን እረዳዋለሁ - ወድጄ መሰለህ ተገድጄ!

እናም፣ ወዳጄ መምህሩ የምር ጥያቄህን በደረቁ አስተጋብቼ አዙሬ ከማበሳጭህ፣ በአብዛኛው አንተው በፈጠርከው መራራ ቀልዶች አዋዝቼና አለዝቤ የችግርህ ተካፋይ፣ መሆኔን ባሳውቅህ ምን ይልኻል? ምንም! እናም ወዳጄ መምህሩ አሁን ይህን እየፃፍኩልህ ያለሁት “ወገኛ” መምህር ነኝ፤ አቶ በረከት ስምኦን ቢሆኑ ኖሮ፣ “ወሬኛ” መምህር ሊሉኝ ይችላሉ፤ የክቡር ሚኒስትሩን ስም ያነሳሁት ዝም ብዬ እንዳይመስልህ - ያለማስረጃ፡፡ የታዋቂውን ባለሀብት የሼህ መሀመድን ጨዋታ አዋቂነት፣ ወግ ነጣቂነት ለመግለጽ አስበው ይመስላል፣ “መሃመድ ወሬኛ ነው” ማለታቸውን ሰምተህ የለ…ወሬ አይደበቅ! ግን ለወግ ያህል ነው ማጣቀሳችን!

በል እንደተባባልነው…የቆዩት የሥራ ባልደረቦች ከህይወት ልምዳቸው ቀምረው ያወሩንን “ቀልድ” ላስታውስህ፤ ሰምተኸው ይሆናል…በሃገሪቱ ታሪክ መምህራን በሙሉ በአንድ ጊዜ ለሁለት ወራት በተሰባሰቡበት የሀምሌ፣ 1994 ሃገር አቀፍ ጉባኤ ላይ ምን ያልተወራ ነገር ነበር፤ አዲስ ምልምል ሰሞንኛ “መምህር” ካልሆንክ አንተም በተሰበሰብክበት ወረዳ ብዙ መራር መምህር ተኮር ቀልዶችን ሰምተኻል ብዬ እገምታለሁ፡፡

ሰሞኑን የተደረገልህ የአንድ እርከን የደመወዝ ጭማሪ፣ በየቤቱ ምን ጉድ እንደፈጠረብህና የዛሬው የኑሮ እውነትህ፣ ለነገ መምህር ተኮር ቀልድህ መነሻ ብቻ ሳይሆን ቀጥተኛ “ግብአት” መሆኑን ላስተነትንልህ ፈልጌ ነው (በነገራችን ላይ፣ እቺ “ግብዐት” የምትል ሥረ - ግዕዝ ቃል፣ “Input” ለሚለው ለፈረንጅ አፉ ቃል ምትክ ትርጓሜ ስትሆን፣ ይህቺን ቃል አስማምተው ለመጀመያ ጊዜ የተጠቀሙበት ፀሐፊ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ መምህር የሆኑት አቶ ደረጄ ገብሬ (ረዳት ፕሮፌሰር) እንደሆኑ አንድ አንብቦ አደር ባልንጀራዬ ለአጠቃላይ እውቀት አጫውቶኛል፡፡)

ወደ መራር ቀልዶቻችን በቀጥታ እንግባ …ድሮ በአብዮታዊው መንግስት ዘመን (ውይ…ለካ “አብዮት” ለአሁኑ መንግስታችንም፣ የዲሞክራሲ ማጥመቂያ መሣሪያ፣ የግራ ክንፍ ቅጂ አስኳልም አይደል?) ይቅርታ በደርግ ዘመን፣ በአንድ የገጠር ትምህርት ቤት ያለ የአንደኛ ደረጃ መምህር “Girl” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል “ጀርል” እያለ ያስተምራል (“ስቱደንት ጀርል” “ጀርል”…”ሴይ አጌን” “ጀርል”) ለቁጥጥር የመጡት የትምህርት ባለሙያ፣ “ኢንስፔክተር ግዛቸው” የመምህሩን “ጀርል” ሰሙና ተደናገሩ፡፡ ወዲያው መምህሩን አስጠርተው፣ “ጓድ፤ ምን እያልክ ነበር የምታስተምረው?” አሉት፡፡ ብሶት ያለበት መምህር፣ “ታድያ በዘጠና ብር “ጀርል” እንጂ “ገርል” ብዬ ላስተምርልህ ፈለግክ” ኮስተር ብሎ መለሰ አሉ…በመምህራኑ ጉባኤ ላይ መሪር ሣቅ ተስተጋባ…ንግግር አድራጊው መምህር ግን ቀልዱን እንደማነቃቂያ ተጠቅመው፣ የመምህሩን ብሶት ማስተንተን ቀጥለው ነበር፤ ያኔ፣ በ1994 ዓ.ም፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ300 ብር በማይበልጥበት ጊዜ ነው እያልኩህ ያለሁት፡፡ ዛሬ ኩንታል ጤፍ 1500 ብር በሚገዛበት ጊዜ የአንተ የመምህሩ “ቀልድ” ምን እንደሆነ ትነግረኛለህ…ወይም እነግርሃለሁ፡፡

አሁንም የሀምሌ 1994 ዓ.ም ስብሰባ ላይ ባልደረባህ እንባ እየናነቀው የቀለደውን ነው የማወጋህ…“አቤት ጉድ እውነትም ቀልድ እቴ” እንዳትለኝ፡፡ በተጠቀሰው ጊዜ እንደምታስታውሰው ወይም እንደሰማኸው የኢትዮጵያ መምህር ሁሉ በሚሰራበት ወረዳ ለሁለት ወር ተሰብስቦ ነበር፤ የአንተን ባላውቅም እኔ ግን ተሰብስቤያለሁ፤ “በእረፍት ጊዜዬ ላይ ከሰበሰብከኝ የውሎ አበል ይከፈለኝ” ብለህ፣ እንደ አሁኑ መረር ብለህ ጠይቀህ ነበር፤ እናም የተሰጠህን ፈጣን ምላሽ እስከ መቃብር የምትረሳው አይመስለኝም፤ በቀን 7 ብር ነበር የተፈቀደልህ…

ይህን አስመልክቶ ነው፣ ባልደረባህ ከስብሰባው አጋማሽ ቀናት ላይ እያነቡ ቀልደው ያሳቁን፤ አንዲት እናት፣ ገበያ ውስጥ እህል ገዝተው የሚሸከምላቸውን፣ “ሰራተኛ…ሠራተኛ” ብለው ይጠራሉ፡፡ አንድ ደበሎ ለባሽ ተሸካሚ እየሮጠ መጥቶ፣ ግማሽ ኩንታሉን እህል ብድግ አደርጐ እያስቀመጠ፣ “የት ነው የሚሄደው?” አለ፡፡ ሴትየዋም፣ “አገር ግዛት፣ ኪዳነምህረት አጠገብ…” ብለው ነገሩት፣ “ከሰኞ ገበያ እስከ ኪዳነምህረት ሩቅ ነው፣ ደሞ ጭቃው! እሺ በቃ 10 ብር ይሰጡኛል” ሲል ሴትየዋ በፍጥነት፣ “ምን አልክ? ደፋር ነህ!…ለአንድ መሀይም አስር ብር ከምከፍል…ለተማረ ተሸካሚ መምህር በ7 ብር አሸክመዋለሁ” ብለው አረፉት፣ ሲል መምህሩ፣ አዳራሹ በሳቅና በጩኸት ተናወጠ፡፡ በዚህ ጊዜ በጠቀስኩልህ ከተማ ላይ የህግ ባለሙያዎች በቀን 100 ብር አበል ተሰብስበው ነበር፤ ፀባይ ካለህ እነሱ ሻይ ይጋብዙሃል ግን ብሶት እንድታሰማ አይፈቅዱልህም፤ እነሱንም እንዳንተ በ7 ብር ለምን አልተሰበሰቡም አይነት ቅናት ያደረብህ ይመስላቸዋልና…

“እውቀት ጢቁ” ወዳጄ…ወደ ሰሞኑ ብሶታችን እንመለስ፤ ከዚያ በፊት ግን “እውቀት ጢቅ” ስልህ ላሸሙርህ ፈልጌ እንዳይመስልህ፤ ወይም፣ የመንግስት ባለስልጣናቱ የተደረገልህን የደመወዝ ጭማሪ፣ በመላው ሀገር እያወጁ፣ ለሙያህ ክብር የተደረገ ታላቅ በረከት እንደሆነ ካሳበቁብህ ጋር አያይዘህ፣ እኔም እያፌዝኩብህ እንዳይመስልህ፤ ከሆነም በራሴ ላይ እያፌዝኩ መሆኑን አንጥረህ፣ የብሶታችን ልኬት ገደብ አልባ መሆኑን በትይዩ ልታመሳክርበት ትችላለህ እልሃለሁ “እውቀት ጢቅ” የሚለውን አባባል ያገኘሁት የት መሰለህ? ብዙ ግንባር ቀደም አብዮተኛ ተማሪዎች ካፈራው ከወይዘሮ ስኅን ትምህርት ቤት ጀርባ በፊት ለፊት ለሚታይ ለአንድ ሠፈር የተሰጠ ስያሜ ነው፡፡ ምን መሠለህ ባልደረባዬ…በደሴ ከተማ፣ ከጦሣ ተራራ በትይዩ ከዓመታት በፊት፣ ኩንታል ጤፍ ከ250 ብር ሳይበልጥ፣ ባልደረቦችህ ቦታ ተመርተው ቤት ሰርተው ነበር፤ ታዲያ በዚያ ሠፈር የተመራው አብዛኛው እንዳንተ መምህር ስለነበር፣ ሠፈሩ “እውቀት ጢቅ” ተባለ፡፡ እኔም ይህንን ነው ለአጠቃላይ እውቀት የነገርኩህ፤ በነገራችን ላይ ብር ይጠርህ እንጂ በአንፃራዊነት፣ ከሌሎች የሀገሪቱ ሠራተኞች ሁሉ የተሻለ የእውቀት እጥረት እንደሌለብህ አንተም፣ ፈጣሪህም፣ ወይም “ዲሞክራሲን” በአብዮት ሊግትህ የተነሳው “ልማታዊ መንግስትህም” ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡

አንድ እርከን (በአብዛኛው ከመቶ ብር በታች) ደመወዝ ጨምሮም ቢሆን፣ “ሙያውን የሚያስከብር ጭማሪ” እያለ መንግስታችን የለፈፈው፣ በአንድ በኩል ተቸግሮም ጭምር እንደሆነ ጠርጥር፤ እውቀት የማካፈል ሙያህ፣ መተኪያ የሌለው የሚያስከብር ሙያ እንደሆነ ጠንቅቆ ስለሚያውቀው ነው፡፡ ግን… “አበሻ ግን ሲል ችግር ነው” ያለውን አንድ ባልንጀራዬ ትዝ አስባልከኝ… “ግን” ማ፣ ይሄ እያስወጋን ያለ ጉዳዩ ነው!

ይልቅ መምህር…የአሁኑ “የደመወዝ ጭማሪ” ግብር በምትከፍልበት ቴሌቪዥንህ ላይ (“ወይ ጉድ! አንተ ትቀልዳለህ…ቴሌቪዥን እንዴት ብዬ ነው የምገዛው?”  የምትለው ጀማሪ መምህር ለአብዮታዊ ዲሞክራሲያችን ብለህ ይቅር በለኝ…) ፊታቸው ላይ ወዝ በተዳፋባቸው ቱባ ባለሥልጣናት “ታጥቦና ተቀሽሮ” ሲነገር፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን አንተም ተደናግረህ ነበር፤ “አንድ እርከን ጭማሪ ስንት ብር ነው?” እያልክ ለየባልንጀሮችህ ስልክ ስትመታ ማምሸትህን አስታወስክ? “ወቾ ጉድ! እንዴት ይረሳል ወዳጄ!?” ከሆነ መልስህ ልቀጥል…

አንድ ባልንጀራዬ ያጋጠመውን ልንገርህ፤ እሱም እንዳንተ “እውቀት ጡቅ” ነው፤ “የሙያህን ክብር የሚያስጠብቅ” የደመወዝ ጭማሪህን የሰሙት ቤት አከራዩ አዛውንት ባልተለመደ ሁኔታ ገና በጧት በሩ ላይ ጠበቁት፤ ባልንጀራዬ የወንደላጤ ቤቱን በር ከፍቶ አንድ እግሩን ብቅ ሳያደርግ፣ “መርከሻ…ወይ! ማርከሻ እንዴት አደርክ!...የማታውን ሰማኸው አይደል? አይ…ለካ አንተ ቴሌቪዥንህ ከተበላሸ ቆይቷል…እንኳን ደስ ያለህ ዋናው እሱ ነው፤ ምን አባቱ ቴሌቪዥንህ አሁን ይሠራል መንግስት አንበሻበሻችሁ አይደል? ተመስጌን ነው! እኔማ ማታ አምሽተህብኝ እንጂ ደስታህን ልካፈል ነበር፤ እውነቴን እኮ ነው፣ እንዴት ደስ እንዳለኝ… ቴሌቭዥኑን ብትሰማውኮ ጉድ ነው፤ መምህሩ ከዚህ በኋላ ኮርቶ እንዲሄድ፣ ሱፉን ለብሶ ኮራ ብሎ እንዲንቀሳቀስ ብዙ ብር ተጨምሮለታል …ብሎ ሲናገር” ባልንጀራዬ ተበሳጭቶ አቋረጣቸው፡፡

“አባ ማታ ሌላ ቦታ ሰምቸዋለሁ! እኔ በነበርኩበት ቤት ውስጥ የነበረ ቴሌቪዥን እስዎ ያሉትን ነገር አላለም!” አላስጨረሱትም፤ ቆጣ ብለው “ምን ነካህ የሚያኮራ የብር መሃት ብሏል…የምን ማለባበስ ነው…ለማንኛውም እኔ እስከ ዛሬ ብር ተቸግረሃል ብዬ፣ የጡረታ ብሬን እየገፈገፍኩ፣ የመብራት፣ የውሃ እየከፈልኩ መቀጠል አልቻልኩም፤ ለጊዜው መቶ ብር የቤት ኪሪዩ ላይ ጨምረህ ስጠኝ፤ ለወደፊቱ አንተው አስበህ ትጨምርበታለህ” ብለው በፍጥነት ዘወር አሉ፡፡ ባልንጀራዬ በእልህና በንዴት ልሣኑ ተዘጋጋበት (እሱ እንደነገረኝ…እንደወረደ ነው እየነገርኩህ ያለሁት…)፡፡ ሰውዬው የሚሉት ብለው ወደ ቤታቸው ገቡ፤ ተከትሏቸው ሄደና በር አንኳኳ፤ “ግቡ ማነው?” አሉ አዛውንቱ፡፡ “እኔ ነኝ …አባ ሀይሉ…የተጨመረልን አንድ እርከን ነው…ማለቴ 74 ብር፡፡ ከዚህ ውስጥ ተጣርቶ የሚደርሰኝ 58 ብር ነው…” በማለት እያስረዳቸው ሳያስጨርሱት፣ ሰውዬው ወደ ምኝታ ቤታቸው እየገቡ፣ “እንግዲህ መንግስት ያለውን ሰምተናል…ለማንኛውም የመብራቱን ክፍያ ስላልቻልኩት ያልኩህን አድርግ! ካልቻልክ ያው መልቀቅ ነው …ሆሆ! በጆሮዬ የሰማሁትን ያስተባብላል” ጓደኛዬ እንባ እየተናነቀው ከሰውዬ ቤት ወጣ፤ ጭማሪውን 58 ብር አልተቀበለውም፤ ከሣምንት በኋላ ወሩ ለሚሞላው የቤት ኪራይ ግን፣ ተጨማሪ 100 ብር ጠይቀውታል፡፡

ሣምንት ሌላው አወጋሃለሁ…ግን ተረጋጋ…ብለህ ሁን…መምህር ነህና ሀዘንህም፣ ጥያቄህም ሥርአት የያዘ፣ እንደሚሆን አውቃለሁ፤ ወይም ደግሞ፣ አንድ ለአምስት እንደተደራጀህ ብሦትህን እንዲህ በወግ መልክ እየቀመርክ፣ ልትወያዩበት ትችላለህ…ልማታዊ መንግስታችንም “ተደራጅታችሁ አንኳኩ፤ ይከፈትላችኋል” ሲል ሰምተህ የለ…

 

 

Read 3897 times Last modified on Wednesday, 04 April 2012 07:26