Saturday, 10 March 2012 09:19

“ትኩሳት” - አልጋ ውስጥ የቀረ የስለላ ድርሰት

Written by  ከድር አየለ
Rate this item
(3 votes)

አርባ አመት አጭር ጊዜ ባይሆን፤ ስብሃት ገብረእግዚአብሄር፤ ከ”ትኩሳት” በኋላ ረዥም ልብወለድ ባይፅፍ አይገርመኝም። ተጨማሪ ድርሰት ለመፃፍ ያልፈለገው ወይም ያልቻለው፤ በትኩሳት ምክንያት ይመስለኛል። ድርሰቱን እንደአጀማመሩ ከ80 ገፆች በላይ አልዘለቀለትም። ወዳልተለመዱ የወሲብ ትእይንቶች ተንሸራተተ።(የዛሬው ፅሁፍ አንዱ ነጥብ፤ “የድርሰቱ ውጥን በጅምር ቀርቷል” የሚለውን ሃሳብ በመረጃዎች ማረጋገጥ ይሆናል።) የስብሃት ድርሰት፤ ታሪኩን የሚጀምረው ጥያቄ በሚያጭር መንገድ፤ አንዳች ድብቅ ሴራ ወይም ሚስጥራዊ ጉድ እንደሚተርክልን ብልጭ - ጠቆም በማድረግ ነው። ምን ዋጋ አለው? የታሪኩን ጫፍ አስይዞ፤ ጀግንነት የጎላበት አዲስ ወጣትነት አለም ለማሳየት የተወጠነው የስለላና የምርመራ ድርሰት፤ ብዙም ሳይራመድ መሄጃው ጠፋበት። (የዛሬው ፅሁፍ ዋና ነጥብም ይሄው ነው - የድርሰቱ ውጥን ወጣት ጀግኖች የሚያሾሩት የስለላና የምርመራ ታሪክ እንደነበረ በመረጃ አስደግፎ ማብራራት ይጠበቅብኛል።)

አሳዛኙ ነገር፤ ትኩሳትን ያነበቡ ብዙ ሰዎች፤ የስለላና የምርመራ ድርሰት እንደሆነ አያውቁም። ማለቴ... የስለላና የምርመራ ድርሰት እንዲሆን ተወጥኖ የተሞከረ ስለመሆኑ አያውቁም። ብዙዎቹ የስብሃት የቅርብ አድናቂዎች ሳይቀሩ፤ የስብሃትን ጥረትና ፍላጎት አላወቁለትም ብዬ እገምታለሁ። “ስለ ትኩሳት ነው የምታወራው?” የሚል ጥያቄ ከየአቅጣጫ ሊያነሳ እንደሚችል ይገባኛል። “ትኩሳት ... ያ የምናውቀው ትኩሳት፤ የስለላና የምርመራ ልብወለድ ነው?” የሚል አግራሞትን ያዘለ ጥያቄ ይኖራቸዋል። በእርግጥ፤ “ነው” አላልኩም።

ጠቅላላ ድርሰቱ ሲታይ፤ “የስለላና የምርመራ ልብወለድ” አይደለም።  የድርሰቱ አጀማመርና ውጥን፤ የስብሃት ፍላጎትና ጥረት ግን፤ “የስለላና የምርመራ ልብወለድ” ላይ ያነጣጠረ እንደነበር የመፅሃፉ ይዘት ይናገራል። በእዚህ አባባል ላይም፤ ጥያቄዎችና ቅሬታዎች መነሳታቸው አይቀርም። በተለይ፤ “ስብሃት ነውር ይፅፋል” የሚል ቅሬታ ለያዙ አንባቢዎች፤ የሚዋጥላቸው አይመስለኝም። “የወሲብ አይነት ለመዘርዘርና የወሲብ ትእይንት ለመተረክ የሚንደፋደፍ መፅሃፍ አይደለም እንዴ?” እንደሚሉ እገምታለሁ። ለነገሩማ በርካታ አድናቂዎቹ ሳይቀሩ፤ “የስብሃት ድርሰት፤ የወጣቶችን የወሲብ ትኩሳት የሚዳስስ ነው” በማለት ያሞግሱት የለ?

ብዙ አንባቢዎች፤ የስብሃትን ፍላጎትና ጥረት በግልፅ ባያውቁ... እሺ ይሁን። አድናቂዎቹም ሳያውቁለት ሲቀሩ ግን ያሳዝናል። ለደራሲ፤ ትልቅ የልብ ስብራት አይመስላችሁም? ደራሲው፤ ልብ አንጠልጣይ የጀግንነት ታሪክ በአስደናቂ የስለላና የምርመራ ልብወለድ ለማቅረብ አስቦ ፃፈ እንበል። ምን ምላሽ አገኘ? አንባቢዎቹ፤ በተለይ ደግሞ አድናቂዎቹ፤ “ስለወጣቶች የወሲብ ትኩሳት ፅፈሃል” ብለው ደራሲውን ሲያወድሱት ይታያችሁ።

ምናልባት፤ ስብሃት እጅግ ጠንካራ ስለሆነ፤ በዚህ “ቀሽም አድናቆት” ልቡ አልተሰበረ ይሆናል። በእርግጥም፤ ድርሰቱ ከታተመ ወዲህ፤ ብዙ የጋዜጣ ወጎችን መፃፉ ጠንካራነቱን ይመሰክራል። ለነገሩ፤ የአንባቢዎችና የአድናቂዎች አስተያየት ብዙም ላያስጨንቀው ይችላል። ከሁሉም በላይ፤ ራሱ ስብሃት ስለ ራሱ ድርሰት ይበልጥ ማወቁ አይቀርም - እንደአጀማመሩ እንዳልዘለቀለትም ጭምር። ካስጨነቀውም፤ ይሄ ነው ይበልጥ የሚያስጨንቀው። እዚህ ላይ፤ በተራ አነጋገር፤ “እና ምን ይጠበስ?” ሊባል ይችላል።

እንደአጀመማመሩ ያልዘለቀለት ደራሲ ስብሃት ብቻ አይደለም። ስንትና ስንት ድርሰት በጅምር ቀርቷል። ብዙ ሰው ወዲህና ወዲያ ሲባዝን በጅምር ባክኗል። የስብሃት በምን ይለያል? ባለፈው ሳምንት ፅሁፍ እንደጠቀስኩት፤ ብዙዎች እንደሚመሰክሩት፤ ስብሃት ከፍተኛ የአእምሮ አቅም ወይም ብቃት ነበረው። የአእምሮ አቅምና ብቃት፤ የቅዱስ ስብእና አካል እንደሆነ ደግሞ አምናለሁ። እንደኔ እንደኔማ፤ በስብሃት ውስጥ፤ ከሁሉም በላይ ጎልቶ የሚታየኝ፤ የጀግንነት ጥማትና ጀግናን የማድነቅ ቅዱስ ስሜት ነው። የአእምሮ ብቃት እንዲሁም ጀግንነትን የማድነቅ ስሜት... ለማንኛውም ሰው እጅግ አስፈላጊ ቢሆኑም፤ ለደራሲ ግን ህይወቱ ናቸው ማለት ይቻላል። ይሄ ባክኖ ሲቀር ያስቆጫል። ከ1960ዎቹ የሶሻሊዝም ትኩሳት ጋር ተያይዘው ከተከሰቱት ብዙ የሚያስቆጩ ብክነቶች አንዱ ነው።

ትኩሳት - የስለላና የምርመራ ድርሰት

ባህራም የተሰኘው ኢራናዊ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ፤ ጭር ባለ ጎዳና፤ በውድቅት ሌሊት፤ ሶስት ግዙፍ ሰዎች ሲደበድቡት ነው ታሪኩ የሚጀምረው። ለነገሩ ብዙ አልደበደቡትም። ይህን የሚነግረን አንድ ሌላ ገፀባህርይ ነው። ጠቅላላውን ታሪክ የሚተርክልን ይሄው ገፀባህርይ፤ ደራሲ ለመሆን የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ የዩኒቨሪሲቲ ተማሪ ነው።  “ተራኪው” ገፀባህርይ፤ ድንጋይ ወርውሮ ባህራምን ከደብዳቢዎቹ ያስጥለዋል። በዚህም ሁለቱ ወጣቶች ትውውቅና ጓደኝነት ይፈጥራሉ። ባህራም፤ ካፒታሊዝምንና አሜሪካን የሚጠላ የኮሙኒዝምና የነማኦ አድናቂ ሲሆን፤ ተራኪው በከፊል ይደግፋል - በሃሳብ ደረጃ ይደግፋል፤ በተግባር ግን ጥርጣሬ አለው።

እንግዲህ፤ ታሪኩ ወደፊት እንዲራመድ አሳማኝና ሁነኛ ምክንያት ያስፈልጋል። ተራኪው ወጣት፤ ደራሲ ለመሆን ስለሚፈልግ የባህራምን ማንነትና ባህርይ በቅርበት ማወቅ አለብኝ ብሎ ያስባል። ደካማ ምክንያት ነው። ቢሆንም ግን፤ መነሻ ስለሆነ ችግር የለውም። ልብወለዱ በባህራምና በተራኪው ዙሪያ የሚያጠነጥን ነው ብንል፤ ሁለቱ ወጣቶች የተዋወቁበት መነሻ ምክንያት ደካማ ቢሆን እንኳ፤ በየደረጃው እየጠነከረና እየሰፋ ከሄደ ስኬታማ ከመሆን አያግደውም። ስለዚህ፤ “ባህራም ማን ነው?” የሚል የተራኪው የማወቅ ጉጉት ለጊዜው በቂ ሊሆን ይችላል።

በዚህ ጉጉት የተነሳ፤ ስለ ባህራም ለማወቅ በሚያደርገው ሙከራና ጥረት፤ የድብቅ ሴራና የሚስጥራዊ ማንነት ፍንጮችን ሲያገኝስ? የወጣትነትና የጉጉት ነገር! ሚስጥር ለማወቅ ሲጎለጉል፤ ጓደኝነትና ፍቅር ለመፍጠር የሚያስችሉ ምክንያቶች፤ በዚያው መጠን ደግሞ ህይወትን ከባድ አደጋ ላይ የሚጥሉ መዘዞች እየሰፉ ይሄዳሉ። በስለላ እና በምርመራ ላይ ያተኮሩ ድርሰቶች ውስጥ የምናገኘው ታሪክ፤ እንዲህ እየከረረና እየጦዘ ልብን አንጠልጥሎ የሚያስጋልብ ነው። ትኩሳት ውስጥ የምናገኘው ጉዳይም ቀላል አይደለም።

“ጄምስ ቦንድ” “ሼርሎክ ሆምስ”

በእርግጥ፤ ታሪኩ የወጣት ተማሪዎች ነው፤ ለዚያውም በአነስተኛ ከተማ ውስጥ የሚፈፀም ታሪክ። ግን የትና የት የሚደርስ ታሪክ እንደሆነ ብታውቁ ጉድ ትላላችሁ። ይህን ጉድ ፈልፍሎ ሊነግረን የሚችል፤ ብቁ አእምሮና ድፍረት የያዘ ጀግና ተራኪ አለ። በዚህ በዚህ ስራው፤ ከሼርሎክ ሆምስ ወይም ከጄምስ ቦንድ ጋር ይመሳሰላል ብላችሁ አስቡት። አዎ፤ ባለታሪኮቹ፤ ገና የዩኒቨርሲቱ ተማሪዎች ናቸው። ነገር ግን ላይ ላዩን ተራ ተማሪ ቢመስሉም፤ አንዳንዶቹ ከዚያም በላይ ናቸው። ብዙ ሚስጥር አለው።

ባህራም፤ የኢራን ኮሙኒስት ፓርቲ ቁልፍ ሰው ነው። አሜሪካን ከኢራን ለማስወጣትና መንግስት ለመገልበጥ፤  ሴራ ሲሸርብ፤ ደርጅት ሲያዋቅር፤ አባላትን ሲመለምልና ሲያሰለጥን የነበረው ባህራም፤ እውነተኛ ስሙንና ማንነቱን መደበቅ ነበረበት። ከኢራን መንግስትና ከሲአይኤ ጥቃት ያመለጠው ለትንሽ ነው። ከነህይወቱ መያዝ አልያም ሞቱን ይፈልጋሉ። የባህራም ጓደኞችም ቀላል አይደሉም። በራሺያና በኮሙኒስት የአውሮፓ አገራት፤ በቻይናና በሰሜን ኮሪያ፤ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላርና በሺዎች የሚቆጠር የመትረየስ ትጥቅ አሰባስበው፤ ከባህራም ጋር በመሆን መንግስት ለመገልበጥ ተዘጋጅተዋል። እሱም ወደ ጦርነት የሚሄድበትን ቀን እየተጠባበቀ ነው።

በእርግጥ ታሪኩ የሚጀምረው በአነስተኛ የፈረንሳይ ከተማ ነው። ነገር ግን፤ ከፈረንሳይ እስከ ሊባኖስ፤ ከአሜሪካ እስከ ራሺያ፤ ከኢትዮጵያ እስከ ኢራን፤ የአለምን ፖለቲካና መንግስታትን የሚያነካካ፤ የሲአይኤና የንጉስ ሰላዮች ያቆበቆቡበት ታሪክ ነው። ሊባኖስ ውስጥ ባህራምን ማሳደድ የጀመሩ የሲአይኤ ወኪሎች ተከትለውት ቢመጡስ? ኢራን ውስጥ ባህራምን ማሳደድ የጀመሩ የገዢው ሰላዮችም የገባበት ገብተው ሊያጠምዱ ይሞክራሉ (ለምሳሌ የባህራም ጓደኛ ሆኖ የሚታየው ጀምሺድ አለ። ቁማርና ቀልዶችን ያዘወትራል - ቀልዶቹ አስቂኝ ሆነው ባይቀርቡም። እና ደግሞ ከባህራም ፍቅረኛ ጋር ድብቅ ግንኙነት ፈጥሯል። ባህራምና ተራኪው ይህን ወጥመድ አያውቁም)። በዚያ ላይ፤ ፈረንሳይ ውስጥ የተደራጁ የፋሽሽት ቡድኖች አሉ - ባህራምን መግደል የሚፈልጉ...

ታዲያ ይሄ ሁሉ፤ ልብን አንጠልጥሎ የሚይዝ፤ ጀግንነትን አጉልቶ የሚያሳይ ምርጥ የስለላና የምርመራ ታሪክ (Mystery Story) አይወጣውም? ያ ሁሉ ሚስጥር ከነመረቡ ቀስ በቀስ እየተገለጠ፤ እየከረረና እየባሰበት፤ ከነውጥረቱና ከነውስብስብነቱ፤ ይህንን ከሚመጥን የገፀባህርያት ስብእናና እድገት ጋር፤ ከነውድቀትና ስኬታቸው ጋር ሲተረክ ለማየት አትናፍቁም? ስብሃት ይህን የጀግንነት ታሪክ ለመተረክ የፈለገ ይመስላል። ምክንያቱም፤ እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው “ሚስጥሮችና ድብቅ ሴራዎች” መፅሃፉ ውስጥ አሉ። ትልልቅ የድርሰት ቁምነገሮች ናቸው።

ስብሃት ድርሰቱን ለመፃፍ ሲያስብ ወይም ሲፅፍ፤ ዋና አላማው እነዚህ ትልልቅ ቁም ነገሮችን እግረመንገድ ጠቃቅሶ እንደዘበት ለማለፍ፤ እናም ስለሌሎች ተራ ነገሮች ለመፃፍ ሊሆን ይችላል? ሊሆን አይችልም። አለበለዚያኮ፤ ትልልቅ ቁምነገሮችንና ትናንሽ ተራ ነገሮችን ለይቶ የማወቅ የአእምሮ አቅም አልነበረውም እንደማለት ይሆናል። ስብሃት ከፍተኛ የአእምሮ አቅም እንደነበረው የምንስማማ ከሆነ ግን፤ የድርሰቱ ውጥን ከላይ በዘረዘርኳቸው ቁምነገሮች ዙሪያ ያጠነጠነ የስለላና የምርመራ ድርሰት ለመፃፍ እንደነበረ አያጠራጥርም። በዚህም አድናቆት ይገባዋል እላለሁ። የአእምሮ አቅምንና ጀግንነት የማድነቅ ስሜትን የሚያሳይ መልካም የድርሰት ውጥንና ጥረት ነበረውና። በእርግጥ አልዘለቀለትም። ደራሲው፤ የያዘውን ውጥን፤ ልብ ወደሚያንጠለጥል የግጭትና የውጥረት ታሪክ ማድረስ አልተቻለውም። ጀግኖቹንና ታሪካቸውን ተመልከቷቸው

ሟሙተው የጠፉ ጅምር ጀግኖች

“መንግስታትን የሚያናውጥ ጀግንነት በውስጡ ደብቆ ይዟል” የሚባለው ሚስጥረኛው ባህራም፤ ፈታኝ ነገሮች ሲገጥሙት ቀስ በቀስ ጀግንነቱ እየጎላ ቢወጣ ታሪኩ ወደ ፊት የመራመድ እድል ያገኝ ነበር። ለባህራም የገጠመው ፈተና ግን፤ ታሪኩን ለማራመድ ምንም አልጠቀመም።ሲላክለት የነበረ ገንዘብ ተቋርጦበት በብድር የተዘፈቀው ባህራም፤ የሚላስ የሚቀመስ እስከማጣት ደርሷል።

ግን፤ የጉልበት ስራ ወይም ሌላ ጊዜያዊ ስራ ላይ ተቀጥሮ ችግሩን በቀላሉ ማስወገድ ይችላል። ያን ያህልም ጀግንነት አያስፈልገውም። ደግሞም አላስፈለገውም። ዘይት ፋብሪካ ሄዶ ተቀጠረ፤ ከዚያም የልጆች ት/ቤት ውስጥ ተቀጠረ። በቃ። ከተቧደኑ ጎረምሶች ጋር የፈጠረውን ፀብ ተከትሎ፤ አንድ ነፍሰ ገዳይ ተልኮብሃል ቢባልም፤ በጥቂት ደቂቃዎች መንገድ ላይ ገድሎ ተገላገለ። ሌላኛው ፈተና፤ “ፍቅረኛው” ማርገዟ ነው። በእርግጥ የሁለቱ ግንኙነት ፍቅር እንዳልሆነ ተገልጿል። ቢሆንም እሷን ትቶ አብዮት ወደሚያቀጣጥል ጦርነት እንዴት ይሄዳል? “ፈተና” ሆነበት። “መፍትሄ” አጣ። ባዘነ። አቅመቢስ ሚስኪን ሆነ። ለዚህ ነው ከለንደን ረዳት የመጣለት። ግን ነገርዮው በቀላሉ መፍትሄ ተገኘለት። ፍቅረኛው ከሌሎች ወንዶች ጋርም ግንኙነት ስለነበራት፤ ያረገዘችው ከባህራም አይደለም ብለው ችግሩን አቃለሉለት። ለምርጥ የስለላና የምርመራ ድርሰት መወጠሪያ ይሆናሉ የሚባሉት እነዚያ ትልልቅ “ሚስጥሮችና ድብቅ ሴራዎች” እንዲህ እንደገለባ በሚንሳፈፉ፤ እንደ ቄጤማ በሚብረከረኩ ገጠመኞች ተቀይረዋል። ባህራም በጥቅሉ ሲታይ፤ ተራ ተደባዳቢና ሚስኪን ሆኖ አረፈው።

በብሩህ አእምሮው፤ የስለላ ሚስጥሮችንና ድብቅ ሴራዎችን እየፈለፈለ፤ በጠንካራ ወኔውም አደጋውን እየተጋፈጠ፤ ያንን የወጣቶች የጀግንነት ታሪክ ይተርክልናል ተብሎ የተጠበቀው “ሸርሎክ ሆምስ”፤ ከአልጋ ጭፈራ የዘለለ ቁምነገር የሚሰራ አልሆነም። የማነፍነፍና የመመርመር ችሎታውን የምናየው፤ ማን ከማን ጋር ተኛች የሚለውን ጥያቄ ለማጣራት ነው። ለዚህም አንድ ሁለቴ የአልጋ ትራስ እያሸተተ ፀጉር ለቅሟል። በምናብ ብልጭ ብለው የነበሩ ጅምር ጀግኖች እንዲሁም ውጥን የጀግንነት ታሪካቸው፤ ብዙም ሳይራመዱ ደብዝዘው ጠፉ፤ ሳይሳኩ ቀሩ። ለምን ሳይሳኩ ቀሩ? ባለፈው ሳምንት ምላሽ የሰጠሁ ይመስለኛል። በተለይ ደግሞ፤ “ራስህን ለሌሎች መስዋእት አድርግ። ሰው ከንቱ ነው” ከሚሉ ጥንታዊና ሶሻሊስታዊ መርሆች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ጠቅሻለሁ። እነዚህ የተሳሳቱና ክፉ የመስዋእት መርሆች፤ ከጀግንነት ጋር አይጣጣሙም። ጀግኖችንና ታሪካቸውን አሟልቶ የመቅረፅ የደራሲ አቅምን ይሸረሽራሉ። “ታሪክ ሰሪው፤ ሰፊው ህዝብ ነው” በማለት የግለሰብን መናኛነትና አቅመቢስነትን የሚሰብክ ሶሻሊስታዊ መርህ ከያዝን፤ ጀግና ግለሰቦችንና ታሪካቸውን በምናባችን ለመቅረፅ የምናደርገው ጥረት ይሰናከላል። የጀግንነት ጥማትና ጀግንነትን የማድነቅ ቅዱስ ስሜትን ከሚያመክን መርህ ስኬት አይጠበቅም። ከዚህ ውጭ በትኩሳት የምናገኘው ሌላው ነገር፤ በድርሰትነት ለመቆጠር አስቸጋሪ የሆነው፤ ወሲብ ተኮር ቁርጥራጭ ትረካ ነው።

 

 

 

 

 

Read 9330 times Last modified on Saturday, 10 March 2012 09:25