Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 11 February 2012 10:00

የነፃ ገበያ በረከት - በሲሚንቶና በቢራ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የነጋዴ ስራ፤ የተወደዱ ነገሮችን እየፈለገ ዋጋቸው እንዲቀንስ ማድረግ ነው

“የነጋዴ ስራ፤ የተወደዱ ነገሮችን እያፈላለፈገና እያሰሰ ዋጋቸው እንዲቀንስ ማድረግ ነው” ብሎ መናገር ለፈተና ያጋልጣል። ለምን እንደሆነ የምታውቁ ይመስለኛል። ሰዎች ብዙ፤ እንዲህ አይነትቱ አባባል፤ “ጨርሶ የማይታመን  ቅዠት ነው” ብለው ያስባሉ። “ያስባሉ” ከማለት ይልቅ፤ ...ለአፍታ ለሴኮንድ ሊያስቡበት አይፈልጉም ቢባል ይሻላል። በቸልታ ስሜት ያልፉታል። አንዳንዶቹን ደግሞ፤ በቁጣና በቁጭት ስሜት ያንጨረጭራቸዋል። “የነጋዴ ስራ፤ ዋጋ መቀነስ ነው? ከየት አገር የመጣ ነጋዴ ነው ባክህ?”... በእልህ ይንተከተካሉ። ወደው አይደለም። ይህን ስሜት አእምሯችን ውስጥ የሚጠቀጥቅ ባህል ውስጥ ያደገ ሰው፤ ደረጃው ይለያይ እንጂ ንግድንና ቢዝነስን እንደጠላት የሚያይ ጨለማ መንፈስ ይጫጫነዋል። ከጨለማው መንፈስ ለመላቀቅ በትጋት መጣር ያስፈልጋል - ወደው የሚገቡበት ጥረት።

የአገራችን ባህል እጅግ ኋላቀር እንደሆነ ከሚመሰክሩ ስሜቶች መካከል አንዱ፤ በንግድና በቢዝነስ ላይ የምናወርደው የጥላቻና የእርግማን ስሜት ነው። “አተረፈብን” ብለን የምንናገረው በምሬት አይደል? የነጋዴ ስራ፤ ሌሎች ሰዎችን ማታለል፣ ማጭበርበር፣ ማራቆት እንደሆነ ያምናሉ ብዙ ሰዎች። እዚህ ላይ፤... “እና አያተርፉብንም፤ አያጭበረብሩንም ልትል ነው?” ...የሚል ስሜት ውስጣቸውን ወጥሮ ቢተናነቃቸው አይገርምም።

የጥላቻው ስሜት፤ ለምእተአመታት የተተከለና በአገር ምድሩ የተንሰራፋ ከመሆኑ የተነሳ፤ የነጋዴ መሰሪነት ጨርሶ ጥያቄ የምናነሳበትና የምንነጋገርበት ጉዳይ ሊሆን እንደማይችል ይሰማቸዋል። በቃ፤ የነጋዴ መሰሪ ክፋትና ሃጥያት... ገና ድሮ ተመስክሮበት የተረጋገጠና ያለቀለት ጉዳይ ሆኖ ይታያቸዋል። የጥላቻው ስሜት እጅግ የመረረ በመሆኑም፤ ስለ ነጋዴ ሲናገሩ ስለ ሰው የሚናገሩ አይመስሉም። ነጋዴን እንደሰው ሳይሆን፤ ከሌላ አለም፤ ከሌላ ፕላኔት የመጣ ልዩ ፍጡር የሆነ ያህል፤ ጭራቅ አድርገው ይቀርፁታል።

ታዲያ፤ በዚህ መሃል፤ “የነጋዴ ስራ፤ የጠፉ ምርቶችን ፈልጎ ማበራከት፤ የተወደዱ ሸቀጦችን ዋጋቸው እንዲረክሱ ማድረግ ነው” የሚል አባባል ሲመጣ ይታያችሁ። አድማጭ የሚኖረው አባባል አይመስልም። “ቦዳ ቲዎሪ” ከሚል ዘመነኛ ማጣጣያ ጀምሮ፤ “የንዋይ ፍቅርን፤ የሃብት ሴሰኝነትን የሚያስተምር ነው” የሚል ጥንታዊ የሃይማኖት ውግዘት ድረስ ሲጨንበት ጭጭ ሊል ይችላል። በዚያ ላይ፤ “የበዝባዦች ጠበቃ፤ የኒዮሊበራሎች ልሳን” የሚል የሶሻሊስቶች ፍረጃ ሲታከልበት አስቡት።

በዚህ ሁሉ ማጣጣያና ፍረጃ አማካኝነት፤ “የነጋዴ ስራ፤ የሸቀጦችን ዋጋ መቀነስ ነው” የሚል አባባል ድምፁ ቢጠፋ ምኑ ይገርማል! ግን፤ እውነት ቢሆንስ? እውነትም የነጋዴ ስራ፤ የጎደለውን ነገር መሙላት፤ የናረውን ዋጋ መቀነስ፤ የተበላሸውን ማስተካከል ቢሆንስ? በአጭሩ፤ የነጋዴ ስራ፤ “አንዳች ተጨማሪ ጥቅም መፍጠርና ማቅረብ (እሴት መፍጠር)” ሆኖ ቢገኝስ?

ይሄ እውነት ከሆነ፤ በማጣጣያ፣ በውግዘትና በፍረጃ ክምር፤ ያንን አባባል ማዳፈንና ጭጭ እንዲል ማድረግ አይቻልም። ከእውነታ ጋር እንደመጣላት ይሆናላ። ብዙ ሰዎችም፤ የነጋዴ ስራ፤ ተጨማሪ ጥቅም መፍጠርና ማቅረብ እንደሆነ በማየት ውለው አድረው እውነታውን መገንዘባቸው አይቀርም። በቅድሚያ ግን እውነት መሆኑን አለመሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

እንግዳና ያልተለመደ ነገር ይመስለኛል እንጂ፤ ጥያቄው ያን ያህልም ከባድ አይደለም። የሃኪም ስራ ምንድነው? ህመምን መርምሮና ለይቶ ማከም፤ ህመምን መቀነስ ወይም መፈወስ፤ የተጓደለ ጤንነትን ማሟላት፤ እና በቁሳቁስም ሆነ በምክር መልክ ለጤንነት የሚጠቅሙ ነገሮችን ማቅረብ ነው የሃኪም ስራ። የመሃንዲስ ስራስ? ለአያያዝና ለአሰራር ያስቸገሩ ነገሮችን መርምሮ፤ ችግሩን የሚያቃልል፤ ስራን የሚያቀላልና ኑሮን የሚያመቻች ነገር መፍጠር፤ መገንባት፤ መገጣጠም፤ መቀመም፤ ማቅረብ የመሃንዲስ ስራ ነው። ነገርዬው ህንፃ ወይም ድልድይ፤ ብረት መቁረጫ ወይም ዶዘር፤ የኤሌክትሪክ ሶኬት ወይም የሞባይል ኔትዎርክ፤ ቫርኒሽ ወይም ሳሙና ሊሆን ይችላል።

የጠበቃ፤ የታክሲ ሾፌር፤ የጥበቃ ሰራተኛ፤ የአስተማሪ ስራዎችንም መዘርዘር እንችላለን። የእያንዳንዳቸው ስራ በመልክ ቢለያይም፤ ችግርን ለማቃለልና ተጨማሪ ጥቅም ለመስጠት የሚችል ነገር መሆን አለበት - በማንኛውም የሙያ መስክ። የስኬቱ መጠንም በዚያው ልክ ይሆናል።

እንዲህ ሲባል፤ የሚያጭበረብር ሃኪም፤ ኪስ የሚያራቁት መሃንዲስ፤ መሰሪ ጠበቃ፤ ዘራፊ የታክሲ ሾፌር፤ የሚያታልል አስተማሪ የለም ማለት አይደለም። ሞልተዋል። አጭበርባሪ፣ ዘራፊ፣ አታላይ የሚል ቃል ትርጉም የሚኖረውም፤ ከትክክለኛው ስራቸው ውጭ መጥፎ ተግባር መፈፀማቸውን ለመግለፅ ስንጠቀምበት ነው።

ስራቸው ተጨማሪ ጥቅም መፍጠርና ማቅረብ ሆኖ ሳለ፤ የሚጎዳና የሚያበላሽ ድርጊት ሲፈፅሙ፤ መሰሪ ወይም አጭበርባሪ፤ ሰነፍ ወይም ዘራፊ ይባላሉ። የሃኪም ስራ ግን ማጭበርበር አይደለም። የጠበቃ ስራም መሰሪነት አይደለም። ሌሎች ሙያዎች ላይ ስንነገጋር እንዲህ ከተግባባን፤ ነጋዴ ላይ ወይም የቢዝነስ ሰው ላይ ስንደርስ እንዴት ነገሩ የተለየ ይሆንብናል። በማንኛውም የስራ መስክ፤ ከተገቢው ስራ ውጭ ጥፋት የሚፈፅም አጭበርባሪና ዘራፊ ሰው ሊኖር የመቻሉን ያህል፤ በንግድና በቢዝነስ መስክም እንዲሁ ይኖራል። በዚያው ልክ፤ የነጋዴ ስራ፤ እንደማንኛውም የስራ መስክ፤ ተጨማሪ ጥቅም መፍጠርና ማቅረብ ነው - ማለትም የጎደሉትን ምርቶችን መፍጠር፤ የናረውን ዋጋ ማውረድ።

ይህን ደግሞ ራሳችሁ ልታስቡት ትችላላችሁ። የሆነ ንግድ ወይም የቢዝነስ ስራ ለመጀመር አስቡ፤ የሰፈር ሱቅ ከመክፈት ጀምሮ የቢሊዮን ብር ፋብሪካና ኩባንያ እስከማቋቋም ሊሆን ይችላል። ምን ያህል ገበያተኛ እንደምታገኙ ማሰላሰላችሁ አይቀርም። ገበያተኛ የምታገኙበት ምክንያት መኖር አለበት።

በሰፈሩ ውስጥ በቅርበት የሚገኝ ሱቅ ስለሌለ፤ ወይም ያሉት ሱቆች ሸቀጦችን አሟልተው ስለማያቀርቡ፤ መስተንግዷቸው ቀልጣፋ ስላልሆነ፤ አልያም በጥራትና በዋጋ ተመራጭ መሆን ስለሚቻል፤ ... እልፍ ምክንያት ሊኖር ይችላል። ነገር ግን፤ አንዳች ተጨማሪ ጥቅም በመፍጠር ለማቅረብ መነሻ የሚሆኑ ምክንያቶች ናቸው።

እንደ ሲሚንቶ ወይም እንደ ስኳር፤ ከፍተኛ የአቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት እንዳለ በመገንዘብም፤ መስኩን ለኢንቨስትመንትና ለቢዝነስ ትመርጡት ይሆናል - በሌላ አነጋገር የቢዝነሳችሁ ወይም የንግድ ስራችሁ መሰረት፤ የተጓደለውን ሸቀጥ ማሟላትና የናረውን ዋጋ ማውረድ ላይ የተመሰረተ ነው።

የቢራ ገበያውን ተመልከቱ። ድሮ በኮታ፤ በዝምድናና በአድልዎ ነበር ቢራ የሚከፋፈለው። ለዚያውም ከጊዜ ወደ ጊዜ የማይሻሻልና አዳዲስ አማራጮችን የማያቀርብ የደነዘዘ መስክ ነበር - የመንግስት ቢራ። ወደ ንግድና ወደ ቢዝነስ ሲለወጥስ? እያያችሁት ነው። ከሌላው ምርት ተለይቶ፤ ከባድ ታክስና ግብር እየተጫነበትም ቢሆን፤ የተጓደለውን እያሟላ ነው - እጥረትን በማስወገድና አማራጮችን በማቅረብ።

አሁን ደግሞ ይሄውና እንምታዩት የሲሚንቶ ዋጋ፤ አንድ አመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ከግማሽ በላይ ቀንሷል። በምርት ወይም በአቅርቦት እጥረት ሳቢያ በኩንታል ከ500 ብር በላይ ደርሶ የነበረው ሲሚንቶ፤ መጀመሪያ ወደ 270 ብር ወረደ። አሁን ደግሞ ከ200 ብር በታች ሆኗል።

ችግሩ የዋጋ ንረት ብቻ አልነበረም። አንድ ሺ ኩንታል ስሚንቶ ለመግዛት የጠየቀ ሰው፤ መቶ ኩንታል ይበቃሃል ተብሎ ይወሰንበታል። በዚያ ላይ የስድስት ወር ቀጠሮ ይሰጠዋል። ቀጠሮው ደርሶ ሲሚንቶውን ለመረከብ፤ መኪኖችን ተከራይቶ ወደ ፋብሪካው ሲሄድ፤ ወዲያው አስጭኖ ይመለሳል ማለት አይደለም። እዚያ በወረፋ እስከሁለት ሳምንት ድረስ እንዲጠብቁ የሚገደዱ ገበያተኞች፤ ለመኪና ኪራይ ምን ያህል እንደሚከስሩ አስቡት።

ይሄን ሁሉ ወጪና እንግልትን የሚያስቀር ጠቃሚ ነገር መፍጠርና ማቅረብ ነው የነጋዴ ስራ። ምን ያህል ቅዱስ ስራ እንደሆነ መመልከት ትችላላችሁ። ያን ያህልም ሚስጥር አይደለም። የተጓደለ (ተፈላጊ የሆነ) ነገር መኖሩን መርምሮ ማወቅ፤ ዋጋው የናረ እና በቅናሽ ማቅረብ የሚቻል ሸቀጥ ምን እንደሆነ ፈትሾ ማወቅ፤ ከዚያም የተጓደለውን አሟልቶ ገበያተኞችን በሚስብ ዋጋ ማቅረብ ነው ቁልፉ ጉዳይ።

ቀላል ስራ አይደለም። ከባድ ስራ ነው። ነገር ግን፤ የዚያኑ ያህል ሽልማቱም ትልቅ ነው። ተጨማሪ ጥቅም በመፍጠር ማቅረብ የቻለ ሰው፤ በዚያው መጠን በትርፋማነት ይበለፅጋል። ሃብትና ብልፅግና የቅዱስነት ምልክት ናቸው - ከቅዱስ ስራ የሚገኙ ስኬቶች ስለሆኑ።

“እና ሃብታም ሰዎች ሁሉ በቅዱስ ስራ ነው የበለፀጉት?” የሚል በእልህ የተሞላ የማፋጠጥ ጥያቄ እንደሚነሳ አውቃለሁ። ጥያቄዎቹ፤ በአብዛኛው የባህላችን ውርስ ናቸው። የንግድ፤ የቢዝነስ፣ የሃብት እና የብልፅግና ጉዳይ ሲነሳ፤ እንዲህ አይነት ጥያቄዎች በብዛት አእምሯችን ውስጥ ቢጨፍሩ አይገርምም። ከህፃንነታችን አንስቶ ያደግንበት፤ የኖርንበትና የዋኘንበት ባህል ውስጥ፤ እንደዚህ አይነት ጥያቄዎችን ሳንሸከም ልንወጣ አንችልም። እንደዚያ ባይሆን ኖሮማ፤ ሃብትና ብልፅግና ላይ የእልህ ጣቶቻችን እንደጦር አይቀሰሩም ነበር። ምሳሌ እናንሳ።

ዲግሪ የእውቀት ምልክት ነው አይደል? የወርቅ ሜዳሊያም የብቃት ምልክት ነው። ፓተንት የፈጠራ ብቃት ምልክት ነው። ማእረግ፤ የጄነራልነትም ይሁን የፕሮፌሰርነት ማእረግም እንዲሁ የእውቀትና የችሎታ ምልክት ነው። በአጠቃላይ፤ ዲግሪና ሜዳሊያ፤ ፓተንትና ማእረግ፤ ዝነኛነትም ሳይቀር፤ የቅዱስ ስራ ምልክቶች ናቸው - በቅዱስ ስራ የሚገኙ ስኬቶች።

በማጭበርበር የተገኘ ዲግሪ ወይም ፓተንት የለም? ይኖራል። ግን ስለዲግሪና ስለፓተንት ቅዱስነት ሲነሳ፤ “በዝምድና የተገኘ ዲግሪ የለም እንዴ!” በሚል አንንጨረጨርም፤ ዲግሪንና የፈጠራ ስራዎችን እንደጠላት አንጠምዳቸውም። “በአድልዎ የተሰጠ ማእረግና ሜዳሊያ የለም እንዴ!” እያልን በእልህ እርር አንልም። ባለሜዳሊያዎችን በጠላትነት አናያቸውም። አጭበርባሪዎች ሊኖሩ ቢችሉም፤ እውነተኛዎቹ ፓተንትና ዲግሪ፤ ሜዳሊያና ማእረግ የቅዱስ ስራ ውጤት ናቸው። ሃብትና ብልፅግናም እንደነዚሁ የቅዱስ ስራ ውጤት ነው።

 

 

Read 4557 times Last modified on Saturday, 11 February 2012 10:04