Error
  • JUser: :_load: Unable to load user with ID: 62
Saturday, 04 February 2012 11:57

የኮ.ል መንግስቱ መፅሃፍ - በሰበቦችና በማመካኛዎች የተሞላ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

ኮ.ል አጥናፉ አባተ ይቅርታ አልጠየቀም። “ከዚያ በኋላ አላየሁትም”

“ጄነራል አማን አምዶም ለ60 ባለስልጣናት መገደል ምክንያት ሆነዋል”

በኢትዮጵያ ረዥም ታሪክ ውስጥ፤ ስልጣን የሚመነጨው ከህዝብ ሳይሆን ከጠመንጃ ወይም ከሃይል እንደነበረ በመጥቀስ የአፄ ሃይለስላሴን መንግስት ይኮንናሉ - ኮ.ል መንግስቱ ሃይለማሪያም (አዲስ ያሳተሙት መፅሃፍ ገፅ 112)። “የትኛው ኮ.ል መንግስቱ?” የሚል ጥያቄ ሊፈጠርባችሁ ይችላል። ስልጣን ለመያዝ ብቻ ሳይሆን፤ በስልጣን ላይ ለመቆየትም ጠመንጃ በመጠቀም የሚታወቁት የደርግ መሪ ኮ.ል መንግስቱ፤ እንዴት እንዲህ ሊፅፉ ይችላሉ? ... ብዙ ባትገረሙ ይሻላል። የአገራችን የፖለቲካ ባህል እንደዚሁ ነው። በጠላትነት የተፈረጀውን ተቀናቃኝ ለማውገዝ እስከጠቀመ ድረስ፤ ማንኛውንም ነገር መጠቀምና መናገር ይቻላል - መዋሸትና ማጋነን ጭምር።

ኮ.ል መንግስቱ፤ “ግንኮ የእርስዎ ስልጣንም ከጠመንጃ የመነጨ ነበር” የሚል ምላሽ ቢሰነዘርባቸው፤ ከቁም ነገር እንዲቆጠር አይፈልጉም። “የኔ ስልጣንማ፤ የህዝቡን አብዮት ለመምራት፤ የአገርን አንድነት ለማስከበር፤ የድሆችን ኑሮ ለማሻሻል ሲባል የተደረገ ነው” በማለት ሰበብ እንደሚደረደሩ አያጠራጥርም። እንደተለመደው፤ “ህዝብ፤ አገር፤ ድሆች” በሚሉ ቃላት፤ ማመካኛና ሰበብ እየሰበሰቡ፤ ተቀናቃኝን ለመወንጀልና በልጦ ለመገኘት ሲባል፤ “እውነታን እየካዱ መዋሸትና ማጋነን” ከአገሪቱ ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ጋር የተቆራኘ ነው። በ500 ገደማ ገፅ በቀረበው የኮ.ል መንግስቱ መፅሃፍ ውስጥም፤ ያህንን ኋላቀር ባህል በህይወት እናየዋለን።

ኮ.ል መንግስቱ እና ጠ/ሚ እንዳልካቸው

በአፄ ሃይለስላሴ የመጨረሻ አመት፤ ጥቂት ወራት ሲቀራቸው ነው፤ ልጅ እንዳልካቸው በጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሾሙት። እናም የደርግ ጥርስ ውስጥ የገቡት - በተለይ ደግሞ ኮ.ል መንግስቱ ጥርስ ውስጥ።

ጠ/ሚ ልጅ እንዳልካቸው፤ አብዮቱን የሚቀለብሱ ሁለት ወታደራዊ ተቋማትን እንደመሰረቱ የሚጠቅሱት ኮ.ል መንግስቱ፤  ተቋማቱ ከሚያሳድዷቸው ወገኖች መካከል በቅድሚያ የተጠቀሱት የአየር ሃይል አባላት እንደሆኑ ይገልፃሉ። የልጅ እንዳልካቸው መንግስት፤ የአየር ሃይል አባላትን በከሃዲነት እየፈረጁ ስም የማጥፋት ዘመቻ አካሂደዋል የሚሉት ኮ.ል መንግስቱ፤ በአየር ሃይሉ ውስጥ እውቅ አብራሪ መኮንኖችን፤ እንዲሁም ቁልፍ የቴክኒክ ብቃት ያላቸው የአየር ሃይል አባላትን እያሳፈኑ በወታደራዊ ወህኒ ቤት ውስጥ ያጉሯቸው ነበር ይላሉ።

የአየር ሃይል መኮንኖች የእስር አፈናውን በመስጋት እየጠፉ ነው የሚል መረጃ እንደደረሳቸው የሚገልፁት ኮ.ል መንግሰቱ፤ ይህንንም “ደብረዘይት ድረስ ሄደን ማረጋገጥ ቻልን” ብለዋል - ገፅ 131። “በአየር ሃይል ሰራዊታችን ላይ የተጀመረውን አደገኛ የማፍረስ ተግባር” በተመለከተ ለህቡዕ ኮሚቴ ሪፖርት እንዳቀረቡና ተወያይተው እንደተማመኑ የሚገልፁት ኮ.ል መንግስቱ፤ የኮሚቴው ሃሳቦች ትክክለኛ እንደነበሩ የኋላ ኋላ በተግባር እንደታየ ያወሳሉ።

በ158 ገፅ ግን፤ ይህንን ያፈርሱታል። ደርግ ሰኔ 1966 አ.ም በይፋ ከተመሰረተ በኋላ፤ ከሁሉም አስቀድሞ ምን እንዳደረገ ኮ.ል መንግስቱ ሲተርኩ፤ በወታደራዊ እስር ቤት ውስጥ ለታሰሩ የአየር ሃይል አባላት ቅድሚያ እንደተሰጠ ይገልፃሉ። የልጅ እንዳልካቸው መንግስት፤ አየር ሃይልን ለማፍረስ እውቅ አብራሪዎችንና ቁልፍ የቴክኒክ ባለሙያዎችን በወታደራዊ ወህኒ ቤት እያጎሩ እንደነበር የነገሩን ኮ.ል መንግስቱ፤ በመቶዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን ለማየት የጠበቁ ይመስላል። በወታደራዊው እስር ቤት የነበሩ ታሳሪዎች ግን ከ30 አይበልጡም፤ የልጅ እንዳልካቸው መንግስት አየር ሃይሉን እያፈረሰ ነው ተብሎ የተወራውም በጣም የተጋነነ እንደሆነ ተገነዘብን ይላሉ ኮ.ል መንግስቱ።

እንዴ? ...ከጥቂት ገፆች በፊትኮ፤ አየር ሃይሉ እየፈረሰ ነበር፤ በቦታው ተገኝቼም አረጋግጫለሁ በማለት የልጅ እንዳልካቸውን መንግስት ሲያወግዙ ነበር። ያው... ተቀናቃኛቸውን ለማውገዝ እስከጠቀማቸው ድረስ፤ ነገርዬው እውነትም ቢሆን ሃሰት ችግር የለውም። የአገራችን ኋላቀር የፖለቲካ ባህል፤ ዋነኛ መለያ ባህርይው ምን መሰላችሁ? ለእውነታ ክብር አለመስጠት! ተቀናቃኞችን ለማጥላላትና ለማውገዝ እስከጠቀመ ድረስ ማንኛውንም ነገር መጠቀም፤ በሃሰት መወንጀልም ጭምር ይቻላል። ከተቀናቃኝ በልጦ ለመገኘትም እንዲሁ፤ ነገሮችን ማጋነንና መዋሸት ይቻላል - በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባህል ውስጥ። እንዲያውም እንደ ትልቅ መሳሪያ ይቆጠራል።

በኮ.ል መንግስቱ የሚመራው ደርግ፤ በመጀመሪያዎቹ አመታት በጄነራል አማን አንዶም ዝና ተጠቃሚ ሆኖ የለ? ኮ.ል መንግስቱ ይህንን ራሳቸው ይናገሩታል። ጭራሽ፤ የጄነራሉን ዝና የፈጠርነው እኛ ነን በማለት ኮ.ል መንግስቱ ሲተርኩ፤  የጄነራሉን ጀግነነት እያጋነኑ በመፃፍና በማውራት ዝነኛ እንዳደረጓቸው ይጠቅሳሉ። መዋሸትና ማጋነን እንደ አሳፋሪ ነገር ሳይሆን፤ እንደ ፖለቲካ ብልህነት የሚቆጥሩት ይመስላል። ብዙዎቹ የአገራችን ፖርቲዎችና ፖለቲከኞችም ተመሳሳይ አስተሳሰብ አላቸው። ደህና የሰለጠነ ፖለቲካ በሚታይባቸው አገራት ውስጥ፤ የውሸትና የማጋነን ጨዋታ የለም እያልኩ አይደለም። ሞልቷቸዋል። በኢትዮጵያ ግን፤ ዋነኛ የፖለቲካ ባህላችን ባህርይ ነው። ተቀናቃኝን በጭፍን እያወገዙ በልጦ ለመገኘት... በውሸት ማጥላላትና መወንጀል፤ በውሸት ማግዘፍና ማወደስ።

በ69 አ.ም በጋንዲ ሆስፒታል ከስቴዲዮም ጎን ወደ መሻሎኪያ በሚወስደው መንገድ የግድያ ሙከራ እንደተካሄደባቸው በማስታወስ፤ ለጥቃቱም ተቀናቃኝ የደርግ መሪዎች ተጠያቂ እንደሆኑ ይገልፃሉ - ኮ.ል መንግስቱ። በተለይ ደግሞ፤ ምክትላቸው የነበሩን ኮ.ል አጥናፉ አባተ፤ እንዲሁም በመሪነት ተሹመው የነበሩትን ብ. ጄ ተፈሪ ባንቲ፤ በሴራው ውስጥ እጃቸው እንዳለበት የሚገልፁት ኮ.ል መንግስቱ፤ ብዙም ሳይቆዩ ይህንን የሚያፈርስ ሌላ ውንጀላ ይሰነዝራሉ። የግድያ ሙከራውን የፈፀሙት ሻእቢያና ኢህአፓ እንደሆኑ በደህንነት መስሪያ ቤት በኩል የተገኙ መረጃዎች አረጋግጠዋል ይላሉ ኮ.ል መንግስቱ። (ገፅ 250)

 

“ህዝባዊ የግድያ ውሳኔ”

በኮ.ል መንግስቱ መፅሃፍ ውስጥ፤ በጣም ዘግናኝ ሆኖ ያገኘሁት፤ 60 የሃይለስላሴ ባለስልጣናት፤ ሌ.ጄ አማን አንዶም እንዲሁም ኮ.ል አጥናፉ አባተ የተገደሉበት ሁኔታ ነው። አንደኛ፤ የግድያዎቹን ትክክለኛነት ለማሳመን ያደረጉት ሙከራ፤ ሁለተኛ፤ በግድያዎቹ ላይ “እኔ የለሁበትም” በማለት ከህሊና ተጠያቂነት ለማምለጥ ያቀረቡት ሰበብና ማመካኛ ያሳፍራል።

ያው፤ ማሳበብና ማመካኘትኮ፤ ሌላ ትርጉም የለውም - የፖለቲካው ባህል ሌላ ተቀጥላና ገፅታ ነው። ኮ.ል መንግስቱ፤ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ጄ. አማን አንዶም ብዙ ውለታ እንደዋሉላቸው ይገልፃሉ። የውጭ ትምህርት እድል ሰጥተዋቸዋል። ከቅጣት አድነዋቸዋል። የዩኒቨርሲቲ መማሪያ ወጪ በመንግስት እንዲሸፈንላው አድርገዋል። ጄ. አማን ባለውላታዬ ናቸው በማለት የተናገሩት ኮ.ል መንግስቱ፤ የጄነራሉን ጀግንነት አጋንነው እንደፃፉና በጋዜጣ ታትሞ እንደወጣ ያወሳሉ።

ደርግ በጄነራሉ ዝና ለመጠቀም ብሎ ብዙ ነገር አድርጓል። ጄነራሉ የአገር መሪ ተብለው በደርግ ተሹመዋል። በሹመት ላይ ሹመት እንዲሉ፤ የመከላከያ ሚኒስትርነትንም ጨምሮላቸዋል። በዚያ ላይ ኤታማዦር ሹም። ከጥቂት ወራት በኋላ ግን፤ የስልጣን ተቀናቃኝ ሆነዋል። ጄ. አማን የአገር መሪና መከላከያ ሚኒስትር ቢሆኑም፤ የሻለቃ ማእርግ ያላቸው ወታደሮች የሚመሩት ደርግ ነው ለጄነራሉ ትእዛዝ የሚሰጣቸው። ጄ አማን የወሰኑትን፤ ሻለቃ መንግሰቱ ያፈርሳሉ፤ አፍርሰውም ተለዋጭ ትእዛዝ ይሰጣሉ።

በእርግጥ፤ ኮ.ል መንግስቱ በጄ. አማን ላይ የሚዘረዝሩት ድክመትና ጥፋት ብዙ ነው - “ሰነፍ” ከማለት ጀምሮ “አገርን የካደ” እስከሚለው ውንጀላ ድረስ። ያ ሁሉ ውንጀላ ዘርዝረውም ቢሆን፤ ፀቡ ተባብሶ በመጨረሻው እለት ስለተካሄደው ስብሰባ ሲናገሩ፤ ጄነራሉን በክብር ለማሰናበትና ገለል ለማድረግ ነበር የታሰበው ይላሉ - ኮ.ል መንግስቱ። “እንዲገደሉ አልፈለግኩም” ለማለት ነው የፈለጉት። እንዲያም፤ ለጄነራሉ መገደል መነሻ የሆኑት፤ ከየክፍለ ሃገሩ የመጡና ወደ ደርግ ስብሰባ የተቀላቀሰሉ 200 ያህል የደርግ ቅርንጫፍ አባላት ናቸው በማለት ኮ.ል መንግስቱ ሰበብ አቅርበዋል።

ከአዲሶቹ አባላት መካከል በንግግር እሳት የሚተፋ አንድ መቶ አለቃ፤ የስብሰባውን መንፈስ እንደቀየረውም ይተርካሉ - “መቶ አለቃው፤ አንድን ነገር ለማቀጣጠል ከፈለገ፤ ከአፉ እሳት ይተፋል” በማለት። ጄነራሉ ብቻ ሳይሆኑ፤ በእስር ላይ የነበሩ የአፄ ሃይለስላሴ ባለስልጣናት ላይም፤ አሁኑኑ አብዮታዊ ውሳኔ መሰጠት አለበት በሚል ተሰብሳቢው እንደጠየቀ የሚገልፁት ኮ.ል መንግስቱ፤ የባለስልጣናቱ ጉዳይ በፍርድ ቤት ያልቃል የሚል መከራከሪያ ተቀባይነት አላገኘም ብለዋል። እናም፤ ጄነራሉ እና 60 የሃይለስላሴ ባለስልጣናት እንዲገደሉ ተወሰነ።

ኮ.ል መንግስቱ እንደሚሉት፤ አንድ ጭፍን መቶ አለቃ የስሜታዊነት ንግግር መነሻነት፤ በድንገት የግድያ ውሳኔ የሚዥጎደጎድ ከሆነ ... አያስፈራም? አይዘገንንም? ኮ.ል መንግስቱ፤ የግድያ ውሳኔውን ታሪካዊ ውሳኔ ይሉታል። በተጨማሪም፤ ታሪካዊው ውሳኔ፤ “ህዝባዊ ውሳኔ ነው” በማለት ትክክለኛነቱን ለማሳመን ይሞክራሉ - (ገፅ 219)።

ራሳቸው ኮ.ል መንግስቱ በጠሩትና በመሩት ስብሰባ ላይ፤ ሶስት መቶ ያህል ወታደሮች ተሰብስበው የጅምላ ግድያ ለመፈፀም ስለወሰኑ፤ “የህዝብ ውሳኔ ነው” ይባላል? “የህዝብ ውሳኔ” የሚለው አባባል፤ ፖለቲከኞችና ፓርቲዎች፤ ባለስልጣናትና መንግስታት፤ በክፋት ግድያና አፈና ለመፈፀም የሚያቀርቡት የተለመደ ማሳበቢያ ነው። አንዳንዴም “ለህዝብ ጥቅም ሲባል” የሚል ማመካኛ ያቀርባሉ። ታስረው በነበሩ ሰዎች ላይ፤ ያለ ህጋዊ የፍ/ቤት ስርአት የሚተላለፍ የግድያ ውሳኔ፤ በሚሊዮን ህዝብ ጭብጨባ የታጀበ ቢሆን እንኳ፤ ታላቅ ክፋትና ወንጀል ነው። ኮ.ል መንግስቱ፤ ሰበባሰበቡ አላጠግብ ስላላቸው፤ ሌላ አሳፋሪ ሰበብ ጨምረው አቅርበዋል። ጄ. አማን ለ60ዎቹ ባለስልጣናት መገደል ምክንያት ሆነዋል ይላሉ ኮ.ል መንግስቱ።

የተገደሉት ሰዎች ፃድቅ ይሁኑ ሃጥያተኛ፤ ክፉ ይሁኑ መልካም፤ ወንጀለኛ ይሁኑ ንፁህ፤ ... ለውጥ የለውም። በዘፈቀደ ግድያ የሚፈፀምበት ስርአት መስፈኑ፤ ይህንን የሚፈፅሙ የሰዎች ስብስብ ስልጣን መያዛቸው፤ እንዲሁም ይህንን የሚፈቅድ ወይም የሚያበረታታ ኋላቀር ባህል መኖሩ ነው ዋናው ነጥብ።

በኮ.ል አጥናፉ አባተ ላይም በርካታ ውንጀላዎችን የዘረዘሩት ኮ.ል መንግስቱ፤ አብዮቱን ከድተዋል በማለት ያወግዟቸዋል። ኮ.ል አጥናፉ፤ በደርግ ስብሰባ ላይ፤ ሶሻሊዝም ከኢትዮጵያውያን ባህልና ሃይማኖት ጋር አይሄድም ብለው ባሰሙት ንግግር፤ ህዝቡን ለድህነት አገሪቱን ለወረራ እያጋለጥናት ነን እንዳሉ ኮ.ል መንግስቱ ይጠቅሳሉ። ኮ.ል አጥናፉ በማግስቱ ይቅርታ ቢጠይቁ ኖሮ ነገሩ ይረጋጋ እንደነበር የፃፉት ኮ.ል መንግስቱ፤ ነገር ግን የይቅርታ ጥያቄ አልቀረበም ብለዋል።

እናም፤ በደርግ ውስጣዊ መመሪያ መሰረት፤ አብዮቱን ክደሃል፤ ለደርግ የገባኸውን ቃል አፍርሰሃል በሚል ምክንያት ኮ.ል አጥናፉ እንዲገደሉ ተወሰነ። ኮ.ል አጥናፉን፤ “ከዚህ በኋላ አላየሁትም” ይላሉ ኮ.ል መንግስቱ። የግድያ ውሳኔ አስተላልፈው ሲያበቁ፤ “ከዚህ በኋላ አላየሁትም” ብሎ መፃፍ ምን ይሉታል? ግድያው የተወሰነው በደርግ ውስጣዊ መመሪያ መሰረት እንደሆነ አለም ሊያውቅ ይገባል በማለት የግድያውን ትክክለኛነት ለማሳመን መሞከርስ?

 

 

Read 5452 times Last modified on Saturday, 04 February 2012 12:00