Saturday, 21 January 2012 09:55

የኢህአዴግ ችግሩ “ከእኔ በቀር ሌሎች አይኑሩ” ማለቱ ነው!

Written by  አላዛር ኬ.
Rate this item
(0 votes)

ተቃዋሚዎች “ደካማ” ናቸው ቢባልም ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ሊከበር ይገባል

ከሁለት ሳምንት በፊት የአቶ በረከት ስምኦን መጽሐፍ በሆነው “የሁለት ምርጫ ወጐች” ላይ ያቀረብኩትን አስተያየታዊ ጽሑፍ አንብቤዋለሁ ያሉት አብዲ.መ የተባሉ ግለሰብ ባለፈው ቅዳሜ “ቻይናው ኢህአዴግ ስንት ዓመት ይኖራል?” የሚል ምላሽ አስነብበውናል፡፡ “የአላዛር ኬ. ጽሑፍ የዋህ ይመስላል” ሲሉም በነገር ወጋ ሊያደርጉኝ ሞክረዋል፡፡ ሃቁን ለመናገር እኔ በመጽሐፉ ላይ ከሰነዘርኩት አስተያየት ይልቅ አብዲ.መ የሰጡት ምላሽ ልቤን በሃሴት ሞልቶታል፡፡ በፖለቲካ ሃሳብ ልዩነት በጠላትነት ከመፈራረጅና ጦር ከመማዘዝ ወጥተን ብዕር ወደመማዘዝ ላደረሰን ዓምላክ ክብር ምስጋና ይድረሰው፡፡ ለህገመንግስታችንም እንዲሁ፡፡

የአብዲ መ. ጽሁፍ እውቁ እንግሊዛዊ ፈላስፋ በርትራንድ ረስል ፖለቲከኞችን በተመለከተ የተናገረውን እድሜ ጠገብ ንግግር እንዳስታውስ አድርጐኛል፡፡ በርትራንድ ረስል “ፖለቲከኞች ንግግር በማድረግ ከመጠን በላይ ከመጠመዳቸው የተነሳ ለማሠብ ጊዜ የላቸውም” ብሎ ነበር፡፡ ባለፈው ሳምንት የቀረበው የአቶ አብዲ ፅሁፍም ለማሰብ ጊዜ አጥተው በጥድፊያ የፃፉት ሳይሆን የተናገሩት ይመስላል፡፡ ይህን ያልኩት በሁለት ምክንያቶች ነው፡፡ የመጀመሪያው በጽሁፋቸው ያነሷቸው ሀሳቦች እርስ በርሳቸው የሚጋጩና ግልብ ትንታኔ የሚስተዋልባቸው መሆኑን በማጤን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፀሃፊው እኔ ባነሳኋቸው ጉዳዮች ዙሪያ የመልስ ምት ከመስጠት ይልቅ አጥር ላጥር (around the bush እንዲሉ) በመዞር የባዘኑ መሆናቸው ነው፡፡ ሁለቱም ምክንያቶች የሚያመላክቱት ፍሬ ነገር ግን አንድ ነው፤ ፀሀፊው ለማሠብ ጊዜ አጥሯቸዋል፡፡ እኔ ካለፈው ሳምንት ቀደም ብሎ ባቀረብኩት አስተያየት ደጋግሜ እንደጠቆምኩት ዋናው ጉዳይ አቶ በረከት በመጽሀፋቸው “ትክክለኛዋ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያደርስ የፖለቲካ ኢኮኖሚ የሚከተለው ፓርቲዬ ኢህአዴግ ነው” ማለታቸው ፈፅሞ እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ብቻ ቢሆን ኖሮማ አሪፍ ነበር፡፡ ዋናውና አሳሳቢው ችግር ግን ኢህአዴግ ከእኔ በቀር ሌሎች አይኑሩ ማለቱና እንዳይኖሩም አልሞ በተግባር መንቀሳቀሱ ነው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ጉዳይ ለማስረዳትና በተለይ ደግሞ የአቶ በረከትን ትንተና ሳይንሳዊ ድባብ ለመስጠት በሚመስል መልኩ በፀሃፊው የተጠቀሱት የዛምቢያው ኢኮኖሚስት፣ ከወደ ካናዳ ተገኘ የተባለው የተቃዋሚ ፓርቲነት ፍች፣ የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ዘገባ ወዘተ... አቶ አብዲ ሊያስረዱት የፈለጉትን ጉዳይ ከማስረዳት ይልቅ ሀሳባቸው እዚያና እዚህ እንዲረግጥና የመልእክታቸው ፍሬ ነገር በጊዜ እንዲሟሟ አድርጐባቸዋል፡፡ ማሳመን ካቃተህ አደናግር የሚለውን የፖለቲከኞች መርህ ተከትለው ይሆን?

ከዚህ ይልቅ ከጓድ ጆሴፍ ስታሊን ሞት በሁዋላ ሶቪየት ህብረትን የመሩትና በሀገራቸው ባልተለመደ መልኩ የኮሙኒስት ፓርቲያቸዉን፣ “ፖለቲከኞች ወንዝ በሌለበት ድልድይ እንሠራለን ይላሉ” በሚል በመተረብ የሚታወቁትን ኒኪታ ክሩስቼቭን ፍሬ ከናፍር ቢያነቡ ኖሮ ከዚያ ሁሉ የአጥር ላጥር ዙረት የሚገላግልና የዛምቢያን ኢኮኖሚስት ሠፊ ዘገባ በአንድ አረፍተ ነገር የሚያጠቃልል ንግግር ማግኘት በቻሉ ነበር፡፡ ኒኪታ ክሩስቼቭ፤ መሠረታዊ የሆነ የአመራርና የርዕዮተ አለም ተሀድሶ የማድረግን አስፈላጊነትና ይህን አለማድረግ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ በተመለከተ ለፓርቲው የፖሊት ቢሮ ሲናገሩ፤ ፓርቲው ጠንካራና ግዙፍ ፓርቲ መስሎ የሚታየው ውስጡን ለማያውቁት ብቻ እንደሆነ፣ የስታሊን አመራር በበርካታ ስህተቶች የተሞላ ስለነበረ የአባት ሀገራቸውን ኢኮኖሚ እንዳሾቀውና የፓርቲው ግንባር ቀደም ካድሬዎች ህዝብ የመምራት ብቃት በዝቅጠትና በንቅዘት እንዳልነበር ያህል መጥፋቱን ዘርዝረው ካስረዱ በሁዋላ፣ ዛሬም ድረስ የሚጠቀስላቸውን ንግግር እንዲህ ሲሉ አቅርበዋል፡- “እንግዲህ ጓዶች ልብ በሉ፡፡ ለአንድ ሀገር ለሚመራ ፓርቲ ከሾቀ ኢኮኖሚና ከውስጣዊ ድክመቱ የሚበልጥ ብርቱ ጠላት መቼም ቢሆን ሊነሳበት አይችልም”

በተንኮታኮተ ኢኮኖሚ፣ በአቅም ማነስ፣ በዝቅጠትና በንቅዘት ተተብትቦ ህዝቡን በወጉ መምራት ያቃተው ፓርቲ፤ በተቃዋሚዎች መጠንከርና መድከም ብቻ ሳይሆን ከነጭራሹ ባይኖሩም እንኳ መውደቁን ለመረዳት ማስረጃ ፍለጋ ብዙ መድከም አያስፈልግም፡፡

ኢህአዴግም ለሽንፈት የሚዳርግ ናዳ መጣብኝ ያለውም ሌላ ሳይሆን ይህንኑ ነው፡፡ እንግዲህ የተንኮታኮተ ኢኮኖሚና በውስጣዊ ችግሮቹ የተነሳ ህዝብ የመምራት ብቃቱን ያጣ ፓርቲ፤ በራሱ ጊዜም ቢሆን መውደቁ አይቀሬ በመሆኑ እውነት ላይ ከተስማማን የተቃዋሚዎች ጥንካሬና ድክመት ጉዳይ አያጣላንም፡፡

“የሁለት ምርጫዎች ወግ” መጽሀፍም ሆነ የአብዲ መ. ጽሁፍ በማወቅም ሆነ በጊዜ ማጣት ለማብራራት ያልቻሉት፤ ኢህአዴግ “በተቃዋሚዎች ጥንካሬ ሳይሆን በራሴ ድክመት ብወድቅም ከወደቅኩበት አቧራም ላይ ሆኜ ይህችን ታላቅ ሀገር እመራታለሁ እንጂ ስልጣኔን ለሌላ ለማንም ቢሆን አልሠጥም፡፡ እኔ ወድቄ ተቃዋሚዎች ይህቺን ሀገር ሲመሯት ከማይ የእለት ሞቴን ይስጠኝ” ብሎ ምሎ የተገዘተበትን መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

እንደ አሜሪካና አውሮፓ ባሉ ሀገራት ያለውን የዲሞክራሲ አሠራር ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት ከተፈለገ፣ ከገባበት ሀገር ነባራዊ ሁኔታ ጋር ማጣጣም ያስፈልጋል እያሉ ፖለቲከኞች በእለት ተዕለት ንግግሮቻቸው ለበርካታ ዘመናት ሲያስገነዝቡን ኖረዋል፡፡ ከሀገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር ይጣጣም ሲባል ግን የዲሞክራሲ አሠራር ምሠሶና መሠረታዊ መገለጫዎቹ ትርጉማቸውም ሆነ የተግባር አጠቃቀማቸው ገዳዳና ተዛነፍ እንዲሆኑ ማድረግን ጨርሶ አይጨምርም፡፡

ለህፃናት ግንዛቤ እንዲረዱ ተብሎ የተዘጋጁ የስነ ዜጋ መጽሀፎች እንኳ፤ በህግ የተደነገጉ የዜጐችን ሠብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን ማክበርና መጠበቅ፣ ህዝባዊ  ምርጫዎችን በተመለከተ የወጡ ህገመንግስታዊ ድንጋጌዎችንና የአፈፃፀም ደንቦችን ማክበር፣ በሀገሪቱ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ የዜጐችን እኩል ተጠቃሚነት ማረጋገጥና መጠበቅ፣ የዜጐችን በህግ ፊት እኩል መሆንና የመልካም አስተዳደር ተጠቃሚነት ማረጋገጥና መጠበቅ የዲሞክራሱ አሠራር ሀሁ እንደሆኑ ያስረዳሉ፡፡ ለምን ቢባል … የአንድ ሀገርና መንግስት ዲሞክራሲያዊነት የሚለካው እነዚህን መሠረታዊ ጉዳዮች በህገመንግስትም ሆነ በሌላ በመደንገግ ብቻ ሳይሆን መከበራቸውና መጠበቃቸው በዋናነት በተግባር ሲረጋገጥ ብቻ በመሆኑ ነው፡፡

ታዋቂው አሜሪካዊ ጋዜጠኛ ዊልያም ኸርስት፤ ፖለቲከኞች ስራቸውን ላለማጣት ሲሉ ማናቸውንም ነገር ከማድረግ አይመለሱም እንዳለው አይነት ካልሆነ በቀር ዲሞክራሲንና ዲሞክራሲያዊ አሠራርን በግላችን ወይም በቡድናችን እንደተመቸን ትርጉምና ቀለም ልንሠጠው አንችልም፡፡

አንድ ሲደመር አንድ ሁለት እንጂ ሶስት መሆኑን እስካሁን በተጨባጭ ያረጋገጠልን ስለሌለ ኢትዮጵያዊ ወይም ኩባዊ አሊያም ካናዳዊ ደመረው ያው ሁለት ነው፡፡ ዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊ አሠራርም ያው ነው፡፡ መብትን በማክበርና በመጠበቅ፤ የፖለቲካ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ኑሮ የጨዋታ ህጐችን በማክበርና በማስከበር ጉዳይ ላይ ለኢህአዴግም ሆነ ለቅንጅት፤ ለመድረክም ሆነ ለአጋር ድርጅቶች የመስፈሪያ ሚዛኑ አንድና አንድ ብቻ ነው፡፡

በዲሞክራሲያዊ አሠራር የስልጣን ሽግግር የሚወሠነው ሁሉንም ወገን በእኩልነት በሚያገለግል ህግና ህጋዊ አሠራር መሠረት ነው፡፡ እናም አንድ ፓርቲ በራሱ ድክመትም ሆነ በተቃዋሚዎቹ ጥንካሬ ወይም ደግሞ በራሱና በተቃዋሚዎቹ ጥንካሬ አሊያም በራሱና በተቃዋሚዎቹ ድክመት ቢወድቅ፣ ስልጣን የመያዝና ያለመያዝ ጥያቄው የሚስተናገደውና የሚወሠነው ለዚህ ተብሎ በወጣው ህግና ደንብ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ ህግና ደንብ ማፈንገጥ ወይም ደግሞ ለራስና ለቡድን የተለየ ጥቅም ለማግኘት በማሠብ ይህን ህግና ደንብ መሻር መሸራረፍ፤ መቀየርም ሆነ ማዛባት በወንጀል የሚያስጠይቅ ህገወጥ ድርጊት ነው፡፡

ህጋዊ አሠራሩ ከሚፈቅደው ውጭ ተቃዋሚዎች የፈለገውን ያህል ደካማ፣ የስልጣን ጥመኛ፣ አይረቤ፣ አላማና መርህ የለሽ ወዘተ ቢሆኑ የመንግስት ስልጣን መያዝ የለባቸውም ብሎ በግልም ሆነ በቡድን በመወሠን፣ በህግ ከተደነገገው አሠራር ውጪ መብትና እንቅስቃሴያቸውን ማፈን፣ ማደናቀፍ፣ ማዋከብ ወዘተ … በህግ የሚያስጠይቅ የወንጀል ድርጊት ነው፡፡

ስንቱን ህይወት ደምና አጥንት ገብሬ ያገኘሁትን ስልጣን በአንዲት የምርጫ ካርድ ብቻ እንዴት አይኔ እያየ ለሌሎች አሳልፌ እሠጣለሁ በሚል፣ ስልጣንን የልፋትና የመስዋዕትነት የእድሜ ልክ የውለታ ካሳ አድርጐ በመቁጠር፣ እኔ ብቻ ካልመራሁዋት ሌሎቹ ይህችን ታላቅ ሀገር ያፈርሷታል እያሉ ማደናገርና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ከህግ አግባብ ውጭ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፤ አባልና ደጋፊዎቻቸውን ማዋከብ ማንገላታት፤ በሠበብ አስባብ ህጋዊ እንቅስቃሴያቸውን ማደናቀፍ ቢሮዎቻቸውን መዝጋት፤ በህገመንግስቱ በግልጽ የተደነገገውን የዲሞክራሲ መብቶቻቸውን ማፈን፤  የምርጫ ኮሮጆን መቅደድና መገልበጥም እንዲሁ በህግ የሚያስጠይቅ ዲሞክራሲን የሚገድል ወንጀል ነው፡፡ እነዚህንና የመሳሠሉትን ወንጀሎች እየፈፀሙ ስለ ዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊነት ማውራት ጨርሶ አይቻልም፡፡

አቶ በረከት ስምኦንም ሆኑ አብዲ መ በጽሁፎቻቸው ሊያስረዱን ከሞከሩት በተቃራኒ በባለፈው ጽሁፌም ሆነ አሁንም እንደገና በማንሳት ለማስረዳት የምፈልገው አብይ ቁም ነገር፣  ከአቶ በረከት ስሞኦንም ሆነ ከአብዲ መ ጋር ያለን ልዩነት እነሱ እንዳሉት ኢህአዴግ ስንት አመት ይግዛ የሚለው ሳይሆን ይልቁንስ እንዴት አድርጐ የሚለው ነው፡፡መሠረታዊው ቁም ነገርም ያለው እዚህ ልዩነት ውስጥ ነው፡፡ ልዩነታችን ስንት ጊዜ ሳይሆን እንዴት አድርጐ ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ዋነኛ መነሻችን ዲሞክራሲና የዲሞክራሲያዊ አሠራር መርህ ከሆነ ያለን እድል አንድ ብቻ ነው፡፡ የመንግስት ስልጣንን ለመያዝ የወጣውን ያልተንጋደደ፣ ፍትሀዊ ህግና ደንብን በኢህአዴግና ልጆቹ የተለመደ አገላለጽ በማክበርና በማክበር ብቻ ነው፡፡

በዲሞክራሲና በዲሞክራሲያዊ አሠራር መርህ ለሚያምን ማናቸውም ሰው ዋነኛ ትኩረቱና ፍላጐቱ የሚሆነው የትኛው ግለሰብ ወይም የትኛው ፓርቲ ለምን ያህል ጊዜ ይገዛል የሚለው ሳይሆን የዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊ አሠራር መርሆች ሳይሸራረፉ፤  ህግና ደንቦች ሳይጣሱ በትክክል መከበራቸውና ግለሰቡም ሆነ ፓርቲው በዚህ ህጋዊ አግባብ ብቻ ወደ ስልጣን መምጣት መቻሉ ነው፡፡

ህጋዊውን አሠራር የምንከተል ከሆነ ተቃዋሚዎች ደካማ፣ የስልጣን ጥመኛ፣ የማይረቡ፣ አላማ ቢስ ወዘተ ስለሆኑ የመንግስትነት ስልጣኑን እኔ እንጂ እነሱ ሊይዙት አይገባም፤ እኔ ካልመራሁዋት ተቃዋሚዎች ሀገሪቱን ያፈርሷታል ወዘተ ወዘተ … በማለት ማምታታት ጨርሶ አይቻልም፡፡

በዚህ አይነት አስተሳሠብ በመመራትና የመንግስትን ስልጣን በመጠቀም የምርጫ ስርአቱን ማዛባት፣ ኮረጆዎችን መነካካት፣ ውጤቱ ሲገለጥም የ”እኔን ለእኔ የእነሱንም ለእኔ” ማለትና በድርቅና መፎረሽም በምንም መልኩ ቢሆን የተፈቀደ አይደለም፡፡

በህግ ከተደነገገው የጨዋታ ህግ ውጭ የመንግስትነት ስልጣን ያስገኘውን የመጨቆኛ መሳሪያዎች (Coercive forces) የጦር የደህንነትና የፖሊስ ሀይሎችን በመጠቀም ከላይ የተመለከቱትንና የመሳሠሉትን ከዲሞክራሲና ዲሞክራሲያዊ አሠራር መርህ ውጭ የሆኑ ህገወጥ ድርጊቶችን መፈፀም ሀ ተብሎ የተጀመረ ጊዜ ወንጀለኛነትና አምባገነንነት ይጀመራል፡፡

አቶ በረከትም ሆኑ አብዲ መ. እንደነገሩን ብቻም ሳይሆን እኛም ቢሆን ኢህአዴግ ለቀጣዮች ሠላሳና አርባ አመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት የቆየ እቅድ እንዳለው ቢያንስ እርግጠኝነት እየተሠማን እንገምታለን፡፡ የእኔ ችግር ግን የኢህአዴግ ለሠላሳና ለአርባ አመታት በስልጣን ላይ ለመቆየት ማቀዱ ሳይሆን እቅዱን የሚያሳካው እንዴት አድርጐ ነው የሚለው ነው፡፡

በሌላ አነጋገር ክርክሩ የህገመንግስቱ መኖርና አለመኖር ወይም መከበርና አለመከበር ነው፡፡ የተቃዋሚዎችም ሆነ የኢህአዴግ ጥንካሬና ድክመት የእኛን ድምጽ የመስጠት ውሳኔ ይወስናል እንጂ በህገመንግስቱ የተደነገገ መብታቸውን እንድንጥስ አያደርገንም፡፡

የእኛ መብት ደካማ ናቸው ስንል ድምፃችንን መንፈግ፣ ጠንካራ ናቸው ላልናቸው ደግሞ ድምፃችንን መስጠት ብቻ ነው፡፡ ደካማ ናቸው ያልናቸውን ፓርቲዎች ከድምፃችን አልፈን ስልጣን መያዝ የለባቸውም በሚል ከህጋዊ ውድድር ልናግዳቸው ወይም ልናደናቅፋቸው ግን ጨርሶ አይቻልም፡፡ ይህን ማድረግ በኢህአዴግ አገላለጽ ህገመንግስቱን መናድ ነው፡፡

የኢህአዴግን አውራ ፓርቲነት ለመግለጽ በማሰብ አቶ አብዲ መ. ያቀረቡልን የአሜሪካ የፓርቲ ፖለቲካ እና ተቃዋሚዎች ኢትዮጵያን የመምራት ብቃት እንደሌላቸው ለማሳየት ያቀረቡት መከራከሪያ በጊዜ እጥረት የተነሳ በወጉ ያልተሰለቀና ምናምኒት ውሃ የማያነሳ ነው፡፡

አሁን ባለው እውነታ ኢህአዴግ ከተቃዋሚዎች የበለጠ የሰው ሃይልና የገንዘብ አቅም ያለው አውራ ሳይሆን ጉልበተኛ ፓርቲ በመሆኑ እንደሆነ ማንም ያውቃል፡፡

አቶ አብዲ መ ሳያስረዱን የቀሩት ዋናው ጉዳይ ኢህአዴግ አሁን የሆነውን አይነት ፓርቲ መሆን የቻለው ለራሱ ምን ምን አይነት ስራዎችን ሰርቶ ተቃዋሚዎችን ደግሞ ምን ምን አድርጓቸው ነው የሚለውን ፍሬ ጉዳይ ነው፡፡

ባለቤቷን የተማመነች በግ ላቷን ውጪ ታሳድራለች እንደሚባለው አይነት ሆኖ የኢህአዴግና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ልጆች በደንብ አያስተውሉት እንደሆን እንጂ ከእርዳታ እህል፣ ከማዳበሪያና ተጓዳኝ የግብርና ግብአት አቅርቦት እስከ አባላት ምልመላ፤ ከተራ የደመወዝ እድገት እስከ የትምህርት፣ የስራና የብድር አገልግሎት ጀምሮ “አውራ ፓርቲ” ለመሆን ኢህአዴግ ትናንት ምን እንደሠራ፣ ዛሬም ምን እንደሚሠራ በግልጽ እያየነው ያለው ጉዳይ ስለሆነ ብዙ ገለፃ አያስፈልገውም፡፡

ተቃዋሚዎች ደካማ፣ የስልጣን ጥመኛ፣ አላማና ራዕይ የለሽ ወዘተ ስለሆኑ ኢህአዴግ የሠራትን የዛሬይቷን ኢትዮጵያ መምራት አይገባቸውም በሚል ከዲሞክራሲና ከዲሞክራሲያዊ አሠራር መርህ ውጭ የግል ወይም የቡድን ብያኔ መስጠት የለየለት ድንቁርናና አምባገነንነት ነው፡፡

አብዲ መ. በተቃዋሚዎች ላይ እንዲህ አይነት አምባገነናዊ ፍርድ ለመስጠት የደፈሩትም በዚህ የተነሳ ነው፡፡

ቀደም ብሎ የተዘረጋ ዲሞክራሲያዊ አሠራርና ዲሞክራሲያዊ ተቋማት ባለመኖራቸው ማዘንና መቆጨት እና እነዚህ ተቋማት እንዳይኖሩ ከሃያ አመታት በላይ ቀን ከሌት መጣር እጅግ የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ “ሌሎች ያበላሹትን ሀገር ተረክቦ ኢህአዴግ ምን ፍጠር ይባላል?” የምትለው የሞኝ ለቅሶ አምባገነንነትን እስከወዲያኛው ለማቆየት የሚያገለግል ተራ የማጭበርበሪያ ዘዴ ናት፡፡

ኢህአዴግ ከትናንት እስከ ዛሬ እያደረገው ያለው፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ባለመኖራቸው አዝኖና ተቆጭቶ እንዲመሠረቱ መጣር ሳይሆን እንዳይኖሩ፣ ከኖሩም ከስም ያለፈ ሚና እንዳይጫወቱ ማድረግን ነው፡፡ ይህ እንዲሆን የሚደረግበት የመጀመሪያም ሆነ የመጨረሻ አላማው ድጋሚ ማሰብን እንኳ የማይጠይቅ ተራና  ቀላል ነገር ነው፡፡

ኢህአዴግ፤ የዲሞክራሲ አሠራር ልምድ የሌለው ህዝብ እና የዲሞክራሲ ተቋማት ያልተገነባበት ሀገር ተረክቤ ምኑን ከምን ላድርገው እያለ በኢ ዲሞክራሲያዊነትና በአምባገነንነት አሠራሩ እስከወዲያኛው እንዲቀጥል ሲረዳው፤ እነ አቶ አብዲ መ. እና መሠሎቻቸው ደግሞ የቀደሙ አገዛዞች ደህና አድርገው ያበለሻሹትን ሀገር ተረክቦ “ኢህአዴግ ምን ፍጠር ይባላል” እያሉ በአይጥ ምስክርነት እንዲከራከሩ እድል ይሰጣቸዋል፡፡

ደሀ ሀገራትን በማስመልከት ያቀረቡት የመጀመሪያው አረፍተ ነገር ከቀጣዩ ጋር የሚጣረስ ገለፃ፤ አቧራውን ወልውለን ደሀ ሀገራት ሀገራዊ መዋቅር ስለሌላቸው አሊያም የተደራጀ ስላልሆነ ተወቃቅሶ የመደጋገፍ፣ እንደ ሀገር የማውራት እድሉን አያገኙም የሚለውን የተሻለ ነው ብለን እንምረጠው፡፡ ኢህአዴግ ሁሌ አጨብጭቡልኝ ማለቱ አቶ አብዲም ትችቶችን እንደተቃውሞ የመቁጠር አባዜአችሁ እንዴት እንደጀመራችሁ ማብራሪያ ቢያስፈልገንም ይህ ሃሳብ የተወሰነ እውነት ስላለው ተቃውሞ የለኝም፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ሀሳብ ላይ ጥርት ያለ ማብራሪያ የሚያስፈልገው አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ይነሳበታል፡፡

ሀገራቱን ሀገራዊ መዋቅር እንዳይኖራቸው ያደረገው ድህነት ቀድሞውኑ እንዴት ሊፈጠር ቻለ? የአርባ ቀን እድላቸው ሆኖ ወይስ ህዝቡ አባያ እንዲሆን በአማልእክቶቹ ድግምት ተተብትቦበት ወይስ ደግሞ በመንግስታቶቹ የአመራር ስህተት?

ቦትስዋና፣ ሞሪሸስ፣ ኬፕቨርዴ፣ ጋና የመሳሰሉት የአፍሪካ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ዘመን ማግስት የነበራቸውን ሀገራዊ መዋቅር ወይም በአቶ አብዲ ሳይንሳዊ አገላለጽ፤ ፖለቲካል ኢኮኖሚ ያኔ በወቅቱ ሀገራችን ከነበራት ሀገራዊ መዋቅር ጋር ቢወዳደር ምናልባት አንድ አይነት ነው ሊባል ይችላል፡፡

ዛሬስ እነሱ የት እኛስ የት ነን? ልማታዊው መንግስታችን ኢህአዴግ ለአስራ ሁለት አመታት አለአግባብና ምናልባትም በግፍ ሲለማመድብን ኖሮ ከተጨማሪ አስርና አስራ አምስት አመታት በሁዋላ ባለመካከለኛ ገቢ ህዝብና ሀገር አደርጋችኋለሁ በሚል የመጀመሪያውን የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ፕላን የነደፈው፣ የዛሬ ስልሳ አመት ልክ እንደኛው እፍ ያሉ ደሀ ሀገራት፣ በአብዲ ገለፃ ደግሞ ሀገራዊ መዋቅር ፈጽሞ የሌላቸው ይባሉ የነበሩት እነቦትስዋናና ሞሪሸስ ዛሬ ካሉበት ደረጃ ለመድረስ እንደሆነ መናገር የአንባቢን የመረዳት ችሎታ እንደማናናቅ ይቆጠራል፡፡

አብዲ መ. ቀደም ብለው ስለድሀ ሀገራት ያቀረቡትን ትንተና በሚሽር መልኩ ሀገራችን ደሀ ናት ግን ሀገራዊ መዋቅር አላት፡፡ ብንወድም ብንጠላም ደግሞ ይህንን ሀገራዊ መዋቅሯን የሠራላት የዛሬው መንግስታችን ኢህአዴግ ነው በሚል ያቀረቡት ሃሳብም ከመረቀኑት ሀሳቦቻቸው እንደ አንዱ ይቆጠራል፡፡ ይህን የመረቀነ ትንተና በተመለከተ አብዲ መ. ካቀረቡት ትንተና በመነሳት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ላቅርብ፡፡

ቀደም ብለው ሌሎቹ የቀደሙ መንግስታት ደህና አድርገው ገድለዋት የሄዱትን ሀገር የተረከበው ኢህአዴግ ምን ይፍጠር ነው የምትሉት በሚል አቅሙ እስከቻለ ጊዜ ድረስ እንዲሁ እያቦካ እንዲኖርና ለኢ.ዲሞክራሲያዊና አምባገነናዊ አሠራሩ እውቅናና ቡራኬ እንድንሰጥ የተማፀኑን ኢህአዴግ አብዲ መ. እና ምናልባትም የኢህአዴግ ልጆች ብቻ በሚያውቁት ተአምር የገነባውን ሀገራዊ መዋቅሩን እንዴትና ምን አድርጐ ገነባው? የዚህ ሀገራዊ መዋቅር ሁለንተናዊ ገጽታ ምን ይመስላል?

እነዚህን የዋህ ጥያቄዎች ያነሳሁት ለሌላ ሳይሆን እንደ ሸሚዞቹ ቁልፍ አቆላለፍ ሁሉ ሀገራዊ መዋቅሩ የተገነባበት መሠረትና የግንባታውም ዘዴ አሁን ያለውን ጠቅላላ ገጻቸውን ቁልጭ አድርገን እንድናየው ስለሚያስችለን ብቻ ነው፡፡

አቶ በረከት ስምኦን በፃፉልን መጽሐፍ አብዲ መ. ደግሞ ባለፈው ሳምንት ባስነበቡን ጽሑፍ በግልጽ እንዳረጋገልጡልን ኢህአዴግ የዲሞክራሲ ነገር አይሆንለትም፡፡ ስለ ዲሞክራሲያዊ አሠራርና የዲሞክራሲ ተቋማት ጉዳይ ያለው አተያይ ሸውራራ ነው እያልኩ ከምከራከርበት በርካታ ምክንያቶች አንዱ የሂደቱ የመጨረሻ ግብ ህግመንግስት ማጽደቅ፣ ህግና ፖሊሲ ማውጣት፣ አንዳንድ ተቋማትንም ማቋቋም ብቻ እንደሆነ አድርጐ መመልከቱ ነው፡፡ አቶ በረከት፤ ኢህአዴግ ከተፈጠረ ጀምሮ ህገመንግስቱን የሚፃረር ስህተት ፈጽሞ የማያውቅ ድርጅት ይመስል ተቃዋሚዎች ሊንዱት ነው እያሉ የሚሰጉበትን ህገመንግስት አርቅቆ በማጽደቁ ብቻ የዲሞክራሲ ሻምፒዮን ነው ብለው ይሸልላሉ፡፡  ዲሞክራሲያዊ ህገመንግስትን በማጽደቁ ብቻ አንድ ሀገርና መንግስት ዳሞክራሲያዊ ሀገርና መንግስት እንደማይባሉ ግን እንኳን የህዝቡ ጫማ የሆኑት አቶ በረከት ይቅርና ለህፃናትም ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ አብዲ መ. ደግሞ የኢህአዴግ አስኳል ፌደራላዊ ስርአቱ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ሀገራዊ መዋቅር መኖር የመጀመሪያው ተመስጋኝ ፌደራላዊ ስርአቱን እውን ያደረገው አካል ነው በሚል ፌደራላዊ ስርአትን መገንባት ብቻውን የፌደራል ስርአቱ በትክክል ስራ ላይ ስለመዋሉ ደንታ ሳይሰጣቸው ዲሞክራት ያደርጋል በሚል የልጆች አይነት ክርክር ያነሳሉ፡፡

ከመምህሩ ደቀመዝሙሩ እንደሚባለው አይነት የዲሞክራሲያዊ ህገመንግስትና የትክክለኛ የፌደራል ስርአት መገለጫ ስለሆኑት የተለያዩ ወሳኝ ጉዳዮች አብዲ መ. ያላቸው አቋም መክረሩና አስፈሪነቱ ከሁሉም የባሰ ነው፡፡

የኢኮኖሚ ፖሊሲ ጉዳይ የዲሞክራሲ መታሰር ጉዳይ፤ የምርጫ ኮሮጆ መቀደድ ጉዳይና ሌላም ተመሳሳይ ነገሮች ጉዳይ እንደ አብዲ መ. ብታምኑም ባታምኑም ብትወዱም ብትጠሉም በሚል የማንአለብኝነት አቋም የሚቀርቡልን ጉዳዮች አይደሉም፡፡

ለምን ቢባል? የህገመንግስቱንም ሆነ የፌደራል ስርአቱን ዲሞክራሲያዊነት የሚወስኑት ጉዳዮች እነዚህ ስለሆኑ ብቻ ነው፡፡ ለእነዚህ መሠረታዊ ጉዳዮች እውቅና ነፍጐ ዲሞክራሲያዊ መንግስትና ፓርቲ ነኝ ማለት፣ ኢህአዴግ ካልሆኑ በቀር ጨርሶ እንደማይቻል በጊዜ መገንዘብ ይገባል፡፡

 

 

Read 3017 times Last modified on Saturday, 21 January 2012 10:04