በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ግንቦት 20 ከህዝብ በዓልነት ወጥቷል
በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለውንና ግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የቆየውን የህዝብ በዓላትንና የእረፍት ቀናትን የሚወስነውን አዋጅ የሚተካ አዲስ አዋጅ ሊፀድቅ ነው፡፡ አዋጁ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአንድ ወር
የእረፍት ጊዜው መጋቢት ወር ላይ ሲመለስ ከሚያፀድቃቸው አዋጆች ቀዳሚው እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባለፈው ታህሳስ ወር ላይ አድርጎት በነበረው ስብሰባ ላይ ያጸደቀውና ወደ ህዝብ
ተወካዮች ምክር ቤት የመራው ረቂቅ አዋጅ፣ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ በ1967 ዓ.ም ያወጣውን አዋጅና ኢህአዴግ በ1988 ዓ.ም ያደረገውን ማሻሻያ አዋጆች የሚሽር ነው ተብሏል፡፡ላለፉት 49
ዓመታት በስራ ላይ የቆየውን ይህንኑ የህዝብ በዓላትንና የእረፍት ቀናትን የሚወስነውን አዋጅ በአዲስ ለመተካት የተፈለገበትን ምክንያት፣ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ማብራሪያ ላይ ተገልጿል፡፡ በዚሁ መሰረትም፤ የቀድሞው
አዋጅ የበዓላቱን አከባበር በዝርዝር ያልደነገገና በዓላቱ የሚከበሩበትን ሁኔታ በግልፅ የሚይዘረዝር በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤትና በፍትህ ሚኒስቴር ውሳኔ መሰረት የተዘጋጀው አዲሱ ረቂቅ
አዋጅ፣ ከቀድሞ አዋጅ፣ የሚለይበት ዋንኛ ጉዳይ፣ የበዓላት አከባበርን በተመለከተ ዝርዝር ሁኔታዎች ማካተቱ ነው ተብሏል፡፡አዲሱ ረቂቅ አዋጅ በዓላትን ተከብረው የሚውሉ ብሄራዊ በዓላት፣ ታስበው የሚውሉ
ብሄራዊ በዓላትና ተከብረው የሚውሉ ሃይማኖታዊ በዓላት በማለት የሚዘረዝራቸው ሲሆን መደበኛ የስራ ቀናት፣ ዝግ ሆነው የሚውሉባቸው በዓላትም በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፍረዋል። በዚህም መሰረት፤ ስራ ዝግ ተደርጎ
የሚከበሩ ብሄራዊ በዓላት የዘመን መለወጫ፣ የአድዋ ድል፣ የሰራተኞች ቀን እና የአርበኞች ቀን ተብለው የሚታወቁ ናቸው። ስራ ሳይዘጋ የሚከበሩ በዓላት ደግሞ የካቲት 12 ቀን የሰማዕታት በዓልና ህዳር 29 ቀን
የብሔር ብሄረሰቦች ቀን ነው ተብሏል፡፡
ወደ ምክር ቤቱ በተላከው ረቂቅ አዋጅ ላይ በሃይማኖታዊ በዓላትነት የተጠቀሱት አምስት የክርስትና እና ሶስት የእስልምና ሃይማኖት በዓላት ሲሆኑ በህዝብ በዓልነት እነዚህም መስቀል፣ ገና፣ ጥምቀት፣ ስቅለትና
ትንሳኤ (ፋሲካ) በክርስትና እንዲሁም ኢድ አል አድሃ (አረፋ) መውሊድ እና ኢድ አልፈጥር በእስልምና ሃይማቶች እንደሆነም ስፍሯል፡፡በዚሁ ረቂቅ አዋጅ ላይ ሁሉም ብሄራዊ በዓላት የሚከበሩበት ሁኔታ የተቀመጠ
ሲሆን፤ ከዘመን መለወጫና ከአርበኞች በዓላት ውጪ ላሉ የህዝብ በዓላት አከባበራቸውን የሚያስተባብር የፊደራል መንግስት መ/ቤት ተመድቧል፡፡
የአድዋ ድል በዓል አከባበር በሌሎች የህዝብ በዓላት አከባበር ላይ በተጠቀሰ መልኩ አከባበሩ በዝርዝር የተገለፁ ሲሆን፤ በዓሉን በባለቤትነት የማስተባበር ሃላፊነት ለመከላከያ ሚኒስቴር እንደተሰጠ በአዋጁ
ተደንግጓል፡፡
ከደርግ ውድቀት በኋላ ለአመታት ስራና ትምህርት ዝግ እንዲሆኑ ተደርጎ በድምቀት ሲከበር የቆየው ግንቦት 20፤ በዚሁ በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ላይ በህዝብ በዓልነት ሳይካተት መቅረቱ ታውቋል፡፡
Saturday, 10 February 2024 09:20
የህዝብ በዓላትን የሚወስን አዲስ አዋጅ በቅርቡ እንደሚፀድቅ ይጠበቃል
Written by መታሰቢያ ካሣዬ
Published in
ዜና