Saturday, 18 November 2023 00:00

“የምግብ እርዳታው ዳግም መጀመር የመኖር ተስፋን ሰጥቶናል”

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በአሜሪካው ተራድኮ ድርጅትና በአለም ምግብ ፕሮግራም ይሰጥ የነበረው ተቋርጦ የነበረው የቆየው የምግብ እርዳታ ዳግም መጀመር የመኖር ተስፋን እንዳሳያቸው ተረጂዎች ገለፁ፡፡ እርዳታው በተገቢው መንገድ ለተረጂዎች የሚደረስበትን መንገድ በማመቻቸቱ ረገድ እርዳታ
አቅራቢ ድርጅቶቹ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባልም ብለዋል፡፡
የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤይድ) እና የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) ባለፈው አመት ሰኔ ወር ላይ ሰብአዊ እርዳታው እየተሰረቀ ላልተፈለገ ዓላማ እንዲውል ተደርጓል በሚል ምክንያት ሰብአዊ እርዳታውን መቋረጡን ተከትሎ፣ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የነበረው
ሰብአዊ ቀውስ እንዲባባስ ረሃብና ረሃብ ወለድ ሞት እንዲበራከት ምክንያት መሆኑም ተገልጿል፡፡በጦርነቱ ሳቢያ ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለው በትግራይ በአማራና በአፋር  ክልሎች የተለያዩ አካባቢዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች፣ የሰብአዊ እርዳታው ዳግም መጀመር በእለት ደራሽ እርዳታ እጦት ሳቢያ ለአስከፊ ረሃብና ሞት የሚዳረጉ ወገኖችን የሚታደግ በጎ እርምጃ ነው ብለዋል፡፡ የሰብአዊ እርዳታ አሰጣጥ ላይ ግን ትኩረት ተደርጎ ለእርዳታው ፈላጊዎች
ብቻ እንዲደርስ የሚደረግበት አሰራር ተግባራዊ ሊደረግ እንደሚገባው ተረጂዎቹ ተናግረዋል፡፡
የዓለም የምግብ ፕሮግራም በስርቆት ሳቢያ ኢትዮጵያ ውስጥ አቋርጦት የቆየውን የምግብ እደላ ዳግም ሲጀምር አሰራሩን በመቀየር ግልጽ፣ በማስረጃ በተደገፈና ገለልተኛ በሆነ አሰራር ላይ በማተኮር፣ እርዳታው ከ3.2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑት ተረጂዎች መድረስ የሚያስችልበትን አሰራር ተግባራዊ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡
አዲሱ አሰራር በስፋት የተሞከረና ጠንካራ የቁጥጥር አሰራርን ተግባራዊ ያደረገ ይሆናልም ተብሏል፡፡ ሰብአዊ እርዳታው ምግብ ወደ ሚከማችባቸው መጋዘኖችና እደላው ወደሚካሄድባቸው አካባቢዎች በሚጓጓዝበት ወቅት የተጠናከረ ጥበቃና ክትትል እንደሚደረግባበትም የአለም ምግብ
ድርጅት አስታውቋል፡፡ የምግብ እርዳታው ከታለመለት አላማ ውጪ ውሎ በሚገኝበት ወቅት አስቸኳይ ጥቆማና ሪፖርት በማቅረብ አፋጣኝ እምጃ መውሰድ የሚቻልበትን አሰራር እንደሚከተልም የዓለም ምግብ ድርጅት በመግለጫው አስታውቋል፡፡

Read 1067 times