Saturday, 21 October 2023 20:57

ከጋዛ አስከፊ የሆስፒታል ፍንዳታ በኋላ-- ?

Written by 
Rate this item
(4 votes)

 *ከሊባኖስ እስከ ዌስተርን ባንክ እና ዋሺንግተን የተቀጣጠለው ተቃውሞ
       *ለጋዛ የሆስፒታል ፍንዳታ እስራኤል ተጠያቂ አይደለችም - ዋይት ሃውስ
       *አሜሪካ በመላው ዓለም ለሚገኙ ዜጎቿ የጉዞ ማስጠንቀቂያ ሰጥታለች
       *3500 ፍልስጤማውያን፤ ከ1400 በላይ እስራኤላውያን ተገድለዋል

          የእስራኤል ሃማስ ጦርነት በተጀመረ በ12ኛው ቀን ላይ፣ መላውን ዓለም ያስቆጣና ያሳዘነ የሮኬት ጥቃት በጋዛ ተፈፀመ፡፡ ባለፈው ማክሰኞ ጥቅምት 6 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በጋዛ የሚገኘው የአል-አህሊ ሆስፒታል ላይ በደረሰ ፍንዳታ 500 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን ታጣቂው ቡድን  ሃማስ ያስታወቀ ሲሆን፤ ትክክለኛውን ቁጥር በተመለከተ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልተቻለም ተብሏል፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች በሆስፒታሉ ተጠልለው የነበሩና ህክምና የሚጠባበቁ ፍልስጤማውያን ነበሩ ተብሏል፡፡
 ሃማስ ለጥቃቱ እስራኤልን ተጠያቂ ያደረገ ሲሆን፤ እስራኤል በበኩሏ ፍንዳታውን ያደረሰው የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ ነው ስትል ወንጅላለች፡፡ ለዚህም የተለያዩ ማስረጃዎችን አቅርባለች፤ የተጠለፈ የሃማስ ታጣቂዎች ንግግር ኦዲዮን ጨምሮ፡፡  
የጋዛው ፍንዳታ በተሰማ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከሊባኖስ እስከ ዌስት ባንክ እንዲሁም  ዋሺንግተን ዲሲ ድረስ ከፍተኛ የህዝብ ቁጣና ተቃውሞ ተቀጣጥሏል፡፡ የዓለም አገራትና መንግስታትም ጥቃቱን ክፉኛ አውግዘዋል፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት፣ አውሮፓ ህብረት፣ አፍሪካ ህብረት፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ኳታር፣ ፈረንሳይ፣ዮርዳኖስ፣ ግብጽና ሌሎች በርካታ አገራት አሰቃቂውን የጋዛ ፍንዳታ በማውገዝ፣ የጥቃቱ ፈጻሚ ናት ያሏትን፣  እስራኤልም አጥብቀው ኮንነዋል፡፡
በቤሩት መዲና ሊባኖስ፣በጋዛ በደረሰው ፍንዳታ የተቆጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች፤  በአሜሪካና ፈረንሳይ ኤምባሲዎች አቅራቢያ ተሰባስበው እስራኤልን ያወገዙ ሲሆን ለፍልስጤምም አጋርነታቸውን ገልጸዋል፡፡ የጸጥታ ሃይሎች፣ ረብሻና ግጭት ለመፍጠር በሞከሩ ተቃዋሚዎች ላይ አስለቃሽ ጭስ ተኩሰዋል፡፡
በዮርዳኖስ አማን ደግሞ ከ1ሺ በላይ የሚሆኑ ሰዎች በእስራኤል ኤምባሲ ደጃፍ ላይ በመሰባሰብ ለፍልስጤምና ሃማስ ድጋፋቸውን የገለጹ ሲሆን፤ እስራኤልን ክፉኛ አውግዘዋል - “ሞት ለእስራኤል!” በማለት፡፡ የእስራኤልንና የአሜሪካንን ሰንደቅ አላማ ሲያቃጥሉም ተስተውለዋል። ተቃዋሚዎች በእስራኤል ኤምባሲ ላይ ጥቃት ለመፈጸም ቢሞክሩም፣ የፀጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጭስ በመተኮስ ተቃውሞውን ለመበተን ችለዋል፡፡
በቱርክ ኢስታንቡል በሺዎች  ተቃዋሚዎች በእስራኤል ቆንስላ አካባቢ ተሰባስበው በጋዛ  ለደረሰው ፍንዳታ እስራኤልን ያወገዙ ሲሆን፤ ለፍልስጤም ድጋፋቸውን አሰምተዋል፡፡ ተቃዋሚዎቹ ወደ ቆንስላው ህንፃ ድንጋይ፣ ዱላና ተቀጣጣይ ነገሮችን ሲወረውሩም ታይተዋል፡፡ በተመሳሳይ በፈረንሳይ ኤምባሲ አቅራቢያ የተሰባሰቡ ተቃዋሚዎች፤ እስራኤል በጋዛ ላይ ፈጽማዋለች ያሉትን ጥቃት በህብረት አውግዘዋል፡፡ አንድ ተቃዋሚ ለጋዜጠኛ በሰጠው አስተያየት፤ የቱርኩ ፕሬዚዳንት፣ እስራኤልን ከማውገዝ ባለፈ ከድርጊቷ እንድትታቀብ የሚያደርጋት ተጨባጭ እርምጃ እየወሰዱ አይደለም ሲል ወቅሷቸዋል፡፡
 ባለፈው ረቡዕ በዋሺንግተን ዲሲ፣ አፍቃሬ - ፍልስጤም የሆኑ በርካታ የአሜሪካ- አይሁድ ተቃዋሚዎች፣ ካፒቶል  ህንጻ ውስጥ ተሰባስበው በመግባት፣ አስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ እንድታቆም ጠይቀዋል - በጭብጨባና በመዝሙር ታጅበው፡፡ “አሁኑኑ የተኩስ አቁም፤ ነፃነት ለፍልስጤማውያን፤ የዘር ማጥፋት ወንጀል ይቁም” የሚሉ መፈክሮችንም  አሰምተዋል፡፡ በመጨረሻ ግን ፖሊስ ለመበተን አሻፈረኝ ብለዋል ያላቸውን 300 የሚደርሱ ተቃዋሚዎች፣ በቁጥጥር ሥር  ማዋሉ ታውቋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሦስቱ ደግሞ የፖሊስ መኮንንኖች ላይ ጥቃት በመፈጸም መከሰሳቸውን የካፒቶል ፖሊስ አስታውቋል፡፡
 በተቃውሞ ትዕይንቱ ከተሳተፉት አንዱ የሆነው  ማቲው ሆህ፤ ከኖርዝ ካሮሊና ድረስ የመጣው በተቃውሞው ላይ ለመናገራል፡፡ በኢራቅና አፍጋኒስታን ጦርነቶች ውስጥ  መሳተፉን የገለጸው ማቲው፤ አሁን ግን ይጸጽተኛል ብሏል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ በጋዛ ሆስፒታል ላይ ለደረሰው ፍንዳታ፣ ሃማስ እስራኤልን ተጠያቂ ለማድረግ ያለ ወትሮው ተጣድፏል የሚሉ የፖለቲካ ተንታኞች፤ የሟቾችን ቁጥርም በዚያ ፍጥነት ይፋ ማድረጉ ጥርጣሬ እንደፈጠረባቸው ይገልጻሉ፡፡ ከሁሉም ደግሞ ዓለማቀፍ ሚዲያዎች ከሃማስ የተሰጠውን መግለጫ ተቀብለው እንደ ተዓማኒና ገለልተኛ መረጃ በእርግጠኝነት ማሰራጨታቸው ብዙዎችን አስገርሟል፡፡ “እስራኤል በጋዛ ሆስፒታል ላይ ባደረሰቸው ፍንዳታ 500 የሚደርሱ ፍልስጤማውያን ተገደሉ” የሚለው መረጃ በጥድፊያ መሰራጨቱ፣ በመካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ ቀስቅሷል የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች፤ የሃማስም ዓላማ በትክክል ይኸው ነበር ይላሉ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም የአረቡ ዓለም በእስራኤል ላይ በጋራ እንዲነሳ ማድረግ፡፡
ሃማስ የጋዛው ሆስፒታል ፍንዳታ የደረሰው እስራኤል በተኮሰችው የሮኬት ጥቃት ነው ሲል ቢከስም፤ እስራኤል ግን ክሱን በማጣጣል፣ ፍንዳታውን ያደረሰው የፍልስጤሙ ኢስላሚክ ጂሃድ መሆኑን በማስረጃ አስደግፋ አቅርባለች፡፡ የእስራኤል ጦር ሰራዊት ቃል አቀባይ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፣ ሮኬቱ ከእስራኤል የተተኮሰ ሳይሆን ከጋዛ የተተኮሰ ነው ብለዋል። የድምፅ፤ የምስልና የኢንተለጀንስ ማስረጃዎችንም ይፋ አድርገዋል፡፡
የጋዛ ሆስፒታል ፍንዳታን ተከትሎ፣ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ የተቀሰቀሰው ከፍተኛ ቁጣና ተቃውሞ፣ የምዕራብ አገራት ለዜጎቻቸው የጉዞ ጥንቃቄ አለርት እንዲያወጡ አስገድዷቸዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ወደ ሊባኖስ ከመጓዝ እንዲታቀቡ እያሳሰቡ ነው፡፡ የአሜሪካ ስቴት ዲፓርትመንት ሰሞኑን ባወጣው የማስጠንቀቂያ አለርት፤ በሊባኖስ የሚገኙ አሜሪካውያን አስቸጋሪ ነገር ተፈጥሮ በረራ ከመታገዱ በፊት በፍጥነት አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ አሳስቧል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ባለፈው ረቡዕ ለ7 ሰዓት ያህል በእስራኤል ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ፕሮዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከእስራኤሉ ጠ/ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔትንያሁና ከሌሎች ከፍተኛ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ጋር ተወያይተዋል፡፡ ሃማስ በእስራኤል ህጻናት እናቶችና አረጋውያን ላይ በጅምላ የፈጸመውን  አስከፊ ጥቃት አጥብቀው ያወገዙት ባይደን፤ “ሽብርተኛነት አያሰንፍም፤ አሸናፊው  ነጻነት ነው” ብለዋል፡፡
ጆ ባይደን ከውይይቱ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ የጋዛው ፍንዳታ የተፈፀመው ሃማስ እንደሚለው በእስራኤል ሳይሆን፣ በሌላ ታጣቂ ቡድን መሆኑን ተገንዝቤአለሁ ብለዋል፡፡ “ማክሰኞ በጋዛ ሆስፒታል ላይ በደረሰው ፍንዳታ የብዙዎች ህይወት በመጥፋቱ ተቆጥቻለሁ፤ አዝኛለሁም። ያሉት ማስረጃዎች ግን የሚያመለክቱት፣ ፍንዳታው የደረሰው በጋዛ በሚገኝ የሽብርተኛ ቡድን በተተኮሰ ሮኬት መሆኑን ነው፡” በማለት እስራኤልን ከተጠያቂነት ነፃ አድርገዋታል፡፡
ፕሬዚዳንቱ፤ ከእስራኤሉ ጉብኝታቸው በኋላ በዮርዳኖስ አማን ከተማ፤ ከግብጽ፣ ፍልስጤምና ዮርዳኖስ መሪዎች ጋር ተገናኝተው፣ በጋዛ ጉዳይ ለመምከር ቀጠሮ ይዘው እንደነበር ይታወቃል፡፡ የጋዛውን አስከፊ ፍንዳታ ተከትሎ ግን የአረብ መሪዎቹ ከባይደን ጋር የሚያደርጉትን ስብሰባ መሰረዛቸውን  አስታወቁ፡፡ ይህም የሃማስ ሃሰተኛ መግለጫና የሚዲያዎች ሙያዊ ሥነምግባር የጎደለው  ዘገባ ውጤት ነው ይላሉ - የፖለቲካ  ተንታኞች፡፡
በሌላ በኩል፤ 20 የሰብአዊ እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ጋዛ እንዲገቡ ግብፅ መስማማቷን የአሜሪካው ፕሬዚዳንት  ባለፈው ረቡዕ  አስታውቀዋል፡፡ ከእስራኤል ወደ ዋሺንግተን ሲመለሱ በፕሬዚዳንቱ አውሮፕላን “ኤር ፎርስ ዋን” ውስጥ ሆነው ለሪፖርተሮች  ማብራሪያ የሰጡት ጆ ባይደን፣ ከግብፁ ፕሬዚዳንት አብደል ፋታህ አል-ሲስ ጋር፣ ፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ በስልክ መወያየታቸውን የገለጹ ሲሆን፤ የግብፁ ፕሬዚዳንት የተወሰኑ ሰብአዊ እርዳታዎች በራፋህ በኩል ወደ ጋዛ እንዲገባ በመፍቀዳቸው፣ “ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡ እርዳታውን የተባበሩት መንግስታት ሠራተኞች ጋዛ ላይ ተቀብለው ለፍልስጤማውያኑ ያከፋፍሉታል ተብሏል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ልክ በዛሬው ዕለት፣ ኦክቶበር 17 ቀን 2023 ዓ.ም ታጣቂው የሃማስ ቡድን በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ፣ ከሁለቱም ወገን ከፍተኛ ዕልቂትና ውድመት እየደረሰ ሲሆን፤ እስካሁን 3ሺ 500 ገደማ ፍልስጤማውያን መገደላቸውንና ከ1ሺ 400 በላይ እስራኤላውያን መሞታቸው ተዘግቧል። ከሁለቱም ወገን ወደ 15ሺ ሰዎች ገደማ ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል፡፡
***

Read 1775 times