Saturday, 05 August 2023 11:13

የአሁን ዘላለም…

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(7 votes)

ሄኖክ ከእውናዊው አለም (Reality) ጋር ከተጣላ ቆየ፡፡ ፈጣሪውን ከሚያመልክበት ቅዱስ ስፍራ እግሩ ከደረሰ ቆየ፡፡ በህሊናው

ውስጥ ሲስላቸው እና ሲፈራቸው የነበሩትን የገነት እና የገሀነም እሳቤዎችን ንቆ ከተዋቸው ቆየ፡፡ ህይወቱ ፀጥ ብላለች፡፡

እውቀት ሰብስቦ መተርጎም የሚችለውን የአዕምሮውን ክፍል ማስታወስ ካቆመ ቆየ፡፡ ምንም ነገር ፈልጎ ለማንም ብሎ ወደ

ፈጣሪው ከፀለየ ቆየ፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት ውስጥ ብዙ ፍልስፍናዎች አልፈዋል፡፡ በአይነት በአይነት የተለያዩ የሀይማኖት አስተምርሆቶች

ተነስተው፣ ታምኖባቸው ተክደዋል። ህይወቱ ውስጥ ያጋጠሙትን የተለያዩ ክስተቶች ገጣጥሞ ትርጉም ያለው ነገር

ቢፈልግባቸውም ምንምነትን እና መረሳትን ብቻ ነው በውስጣቸው ሊያገኝ የቻለው፡፡ ገና በልጅነቱ ሁሉም አይነት እውቀት

ሰለቸው፡፡
ሆኖም አንድ ብቻ ያልሞከረው ነገር አለ፡፡ ያም ነገር እስካሁን ድረስ ከቤተሰቦቹ፣ ከሀይማኖት ሰባኪዎቹ እና ከግል ወዳጆቹ

ከነበሩት የተሰጠው ምክርና የተከለከለው እውቀት ነው፡፡ ያም እውቀት መናፍስት የሚባሉት ፍጥረቶች ጨለማው አለም

እውቀት ባለቤቶች ናቸው የሚል ነው። ስለ ጨለማ ብዙ አስቦ ያውቃል፡፡ ሆኖም ማሰብ ሲፈልግ ጨለማን መርጦ …ክፍሉን

አጨልሞ ነው መደመም የሚወደው፡፡ የማያስፈልገውን እውቀት እነዚህ መናፍስቶች እንደሚነግሩት ነው የተነገረው፤ ሆኖም

ይህን የሚመክሩት ሰዎች ራሳቸው መናፍስትን የሚያወናብድ ሀጥያት በመስራት ቀናቸውን እንደሚገፉት ያውቃል፡፡

የመናፍስቱን እውቀት ለምድር ህይወቱ ሊያደርግ ከቻለ የዘላለም ህይወቱንና ነፍስያውን በእሳት እያስማገደ እንደሚያኖራት

ነግረውታል፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ስለሚያመልኩት እና ስለሚሰብኩት ፈጣሪ ቢጠየቁ ምንም እውቀት እንደሌላቸው እና

ከገሀነም የባሰውን ማህይምነት ተሸክመውት እንደሚንቀሳቀሱ ትክ ብሎ አይቷቸውና አዳምጧቸው ገብቶታል፡፡
ስለዚህ ሊደፍር አሰበ፡፡ መሰልቸቱ “አሁን” የሚለው ጊዜውን እንዳይወስድበት እና ህይወቱን እንዳይቀማው ደፍሮ ለአዲስ

እውቀት ራሱን ማዘጋጀት አለበት፡፡ ስለዚህ ስለመናፍስቶቹ ጥናት ማድረግ ፈለገ፡፡ ብዙ መፅሀፍትን አነበበ፡፡ እንዳይፈራቸው

እና ፍፁም እንዳያምናቸው አድርጎ የልጅነት ጭንቅላቱ እስኪችል ድረስ ስለ ብዙ መናፍስቶች ማንነት  ለነፍሱ እውቀትን

ሰጣት፡፡
ከብዙ ጉዞ በኃላ የሚፈልገውን እውቀት የሚነግረው የመናፍስትን አካል ከነ ስሙና ምልክቱ አውቆት ረጋ አለ፡፡ ተረጋግቶም

አልቀረ፤ ያንን መንፈስ የሚያናግርበትን ጥበብ በሙሉ ታግሎ እውቀቱን የራሱ አደረገ፡፡ አንድ ሙከራ ነው የሚቀረው … መልስ

የሌለበት ምድር ላይ እየተወናበዱ  መኖር ትርጉም እንደሌለው ገብቶታል፡፡ ይህ የእውቀት መንገድ መልስ ካልሰጠው  በገዛ

ፈቃዱ በጥያቄ የምትረብሸውን ህይወቱን ለዘላለም ፀጥ እንድትል ማድረግ እንዳለበት ነው የተረዳው፡፡
ስለዚህ አንድ ሙከራ ማድረግ አለበት…
አንድ ብቻ…
ሰዓቱ ደርሶዋል፡፡ ሊያነጋግረው ነው፡፡ ሊጠራው ነው፡፡ ስለ እውናዊው አለም እና ከዛም በላይ ስለሚሄደው ሰማያዊው

እውቀት ትርጉም ያለው እውቀት እንዲሰጠው ዛሬ ላይ ሄኖክ የእውቀት ገላጭ መናፍስቱን ሊያዋራው ነው፡፡ ይህን ውሳኔ

ለመወሰን ብዙ የሀሳብ ዳገቶችን ወጥቶ ወርዷል። ሆኖም እረፍት የነሳው እውቀትን ሊቆጣጠረው አልቻለም። የፈጠረውን…

ሲያምንበት የከረመውን ፈጣሪውን ጠልቶ ግን አይደለም፡፡ በቃ፡፡ ይሄ ደረቅ አለም ሰለቸው፡፡ ከእንቅልፉ ተነስቶ የሚያያቸው

የሰው ልጆች ሰለቹት፡፡ ሁሌም ተመሳሳይ ናቸው ለሱ። አበላላቸው፣ አረማመዳቸው፣ አስተሳሰባቸው፣ አመላካከታቸው፣

አስተያየታቸው፣ አሳሳቃቸው፣ አለቃቀሳቸው…የሰው ልጅ የተባለ ፍጥረት ከስር መሰረቱ ማየትም መስማትም ሰልችቶታል፡፡

ነፍሱ አዲስ እውቀትን ትሻለች። ማንም ያልዳበሳትን እውቀት የግሉና የብቻው ማድረግ ፈልጓል፡፡ ብቻውን ሆኖ በግሉ

ባገኘው እውቀት…በአዲስ አስተሳሰብ ነው ይህን ደረቅ አለም መመልከት የፈለገው፡፡ ስለዚህ ከዚህ በፈት ሰምቶት

ወደማያውቀው እውቀት ነፍሱን ዘርግቶ ከአዲስ እውቀት ጋር ሊተዋወቅ ይህኛው የህይወቱ ምዕራፍ ላይ ደርሷል፡፡ ለህይወቱ

የእውቀት ብርሀን ፍለጋ ወደ ጨለማው አለም ነፍሱን ለመላክ ተዘጋጅቷል፡፡
ለዚህ ቀመር ብሎ ቤቱን አስተካክሏል፡፡ የቤቱ የማህከለኛው ክፍል ላይ ሰፋ ያለ ክብ ቅርፅ በነጭ ቀለም ተከቧል፡፡ በውስጡም

የሚጠራው መናፍስት ምልክቶች ተስሏል፡፡ ከፊቱም ራቅ ብሎ በሶሰት መዓዘን የተሳለ ቅርፅ ይታያል። የሚጠራውም

መናፍስት በዛው ቅርፅ ውስጥ ነው ራሱን እንደሚገልፅለት የተረዳው፡፡ እሱ ክቡ ውስጥ እግሮቹን አጣምሮ ተቀምጧል፡፡

ጉልበቱ ስር የመናፍስት መጥሪያውን መፅሀፍ አስቀምጧል፡፡
አንድ ጊዜ መፅሀፉን ገልጦ የመጥሪያውን ሚስጥራዊ ቃላት መጠቀም ከጀመረ ህይወቱ ተመልሶ እንደበፊቱ ተመሳሳይ መሆን

እንደማይችል ጥርት አድርጎ ተረድቷል፡፡ ሆኖም ከዚህ መሰላቸት ለመውጣት እና በአዲስ እውቀት ነፍሱን ደግሞ ለማደስ ሲል

ጊዜውን ሰጥቶ ሲያጠናው የከረመውን እውቀት ዝም ብሎት ማለፍ አልፈለገም፡፡
አንድ ጊዜ በሀይል ትንፋሽ ሳበ…
መፅሀፉን ቀስ ብሎ ገለጠው…
ማንበብ ጀመረ…
Thee I invoke, the Bornless one.
Thee, create the Earth and the Heavens:
Thee, that didst create the Night and the Day.
Thee, that didst create the Darkness and the Light.
Thou art Osorronophris: Whom no man has seen
at any time.
Thou art Jabas
Thou art Japos:
Thou hast distinguished between the Just and the
Unjust…
እያለ ሙሉውን የመጥሪያ ቀመሩን ተጠቅሞ መጥራቱን ተያያዘው፡፡ ሙሉውን ንባብ አንብቦ ከጨረሰ በኃላ መመሪያው ላይ

እንዳለው አይኖቹን ጨፍኖ የመናፍስቱን ምልክት በውስጠ ህሊናው በመመልከት ይመሰጥበት ገባ፡፡
ይህን በሚያደርግበት ወቅት ላይ ድንገት እንደ ሰልፈር ያለ ሽታ ይሸተው ጀመር፡፡ ሰውነቱ ከቁጥጥሩ ውጭ የድካም መንፈስ

ውስጥ ጠለቀ፡፡ አተነፋፈሱን እንደመጀመሪያው ማድረግ አቃተው፡፡ አተነፋፈሱ እየፈጠነና እየዘገየ ጭንቀት ውስጥ

ከተተው፡፡ ሆኖም በውስጡ አሳድጎት የነበረው ደፋርነቱ እና በራስ የመተማመን አቅሙ ስለነበር የሚመጣውን ነገር ሁሉ

ለመቀበል ብቁ የሆነ የፅናት አቅም ላይ ነው ያለው፡፡
አይኖቹን መግለጥ አልቻለም፡፡ ለመናገርም ቢፈልግ አንደበቱ የራሱ እስካይመስለው ድረስ ምላሱ ተሳሰረበት፡፡ እንደው ብቻ

አይኖቹን ጨፍኖ የሚመጣውን ነገር መጠባበቅ ላይ ነው፡፡
“ለምን ጠራህኝ?” የሚል ድምፅ ድንገት ሰማ፡፡ መልስ ከመመለሱ በፊት ለማሰብ ሞከረ፡፡ የእውነት ከመናፍስት ጋር ማውራት

ሊጀምር እንደሆነ እየደጋገመ ለራሱ ይጠይቀው ጀመር፡፡ በእርግጥም የሰማው ድምፅ የራሱ አዕምሮ ያስተጋባው ሳይሆን አንድ

እንግዳ ፍጥረት ጭንቅላቱን ተጠቅሞበት እያወራው እንደሆነ ነው እየተረዳ ያለው፡፡
ሆኖም መመለስ አለበት፡፡
የተጠየቀው “ለምን ጠራህኝ?” ተብሎ ነው፡፡
ሄኖክ እንደምንም ብሎ ድምፁን ዝቅ አድርጎ መልስ ሰጠ፡፡
“እውቀት ፈልጌ ነው? ከዚህ ከማየው አለም ውጭ የሆነ እውቀት፡፡ መሰልቸቴን የሚያክምልኝ እና የአዲስ አስተሳሰብ ባለቤት

የሚያደርገኝ እውቀት? ከራሴ ሀሳቦች በላይ ተንሳፍፌ አምልጬ አዲሱን ሄኖክ... አምላካዊ ባህሪውን በምሉዕ የተቀበለውን

ሄኖክን መፍጠር ነው የምፈልገው። አሁን ካሁበት እውነታው አለም ተለይቼ ራሴን ለደቂቃም ቢሆን ማግኘት እፈልጋለሁ?

የጠራውህ ለዚሁ ነው፡፡ አንተም ፍላጎቴን ልታደርስ እንደመጣህ አልጠራጠርም፡፡ “
መልሱ በፍጥነት አልመጣም፡፡ ሆኖም ትንፋሽ ይሰማዋል፡፡ ያ ትንፋሽ ግን ከየት እየመጣ እየሆነ ሊያውቅ አልቻለም፡፡ ከጥቂት

ቆይታ በኃላ መልስ መምጣት ጀመረ፡፡
“ከዚህ አለም ውጭ ያለው ማንነትህን ለመረዳት በቅድሚያ አሁን ያለህበትን አለም በቅጡ ተረድተህው ጨርሰሀል?”
“የእሬትን እሬትነት ለማወቅ አንዳንዴ መቅበስ ብቻ በቂ ሊሆን ይችላል? ነፍሴ በተመሳሳይ እውቀት ደክማለች፡፡ እዚሁ ምድር

ላይ ብቻ የሚዋልል እውቀት ለምድራዊ እንግድነቴ መልስ ሊሰጠኝ ቢሞክር እንጂ የመላውን ሁለንታ ሚስጥር አይነግረኝም፡፡

ደግሞ ሲጀመር በስጋና አጥንት ውስን ሆኜ ያሻኝ ቦታ ባሻኝ ሰዓት መገኘት እንዳልችል ተደርጌ የተፈጠርኩ ፍጥረት ነኝ…ይህ

የምድር ላይ የማይለቅ ድክመቴ ነው፡፡"
“አሁን የምትለኝን ድክመቶችህን ማነው የነገረህ?”
“እስካሁን ድረስ በአይን እና በጆሮዬ ውስጥ ያወቁትን እንዲዘሩብኝ የፈቀድኩላቸው የሰው ዘሮች ናቸው የዚህ እውቀት

ባለቤት ያደረጉኝ፡፡"
“እና አምነሀቸው እየኖርክ ሳለ ማን ድንገት እምነትህን ወሰደብህ?”
“ነፃ ፈቃዴ እና መሰልቸቴ፡፡"
“ከዚህ በኃላ ልነግርህ ያሰብኩትን እውቀት በኃላ ላይ ሊያሰለችህ እና ልትክደው እንደማትችል ምን ያህል እርግጠኛ ነህ?”
“እሱን መመለስ አልችልም፡፡"
“አሁን ስለምትፈልገው አንድ ነገር ላይ ትኩረት አድርገህ ጠይቀኝ እና መመለስ ልጀምር፡፡ አይዞህ አንተ እስከጠራህኝ ድረስ

መምጣት ስለምችል በመካከላችን ያለውን ዘላለም ማንም ሊቀማን አይችልም፡፡ ስለዚህ ረጋ ብለህ ጥያቄህን ጀምር፡፡ ስለምን

ማወቅ ትፈልጋለህ?”
“እውነታው አለም ማለት ምን ማለት ነው? አንተ ራሱ አሁን እያዋራህኝ መሆኑን በምን እርግጠኛ መሆን እችላለሁ?”
“በመጀመሪያ ደረጃ የምትመለከታቸው የነባራዊው አለም መገለጫዎች አንተ ከሌለህ እንደሌሉ መገንዘብ ነው ያለብህ፡፡ እስቲ

መልስልኝ… አንተ ማየት ከምትችለው ነገር ውጭ ተፈጥሮ የተመለከትከው ነገር አለ?... የለም፡፡ ካንተ እይታ ውጭ ያለን ነገር

ለማመንም ሆነ ትርጉም ሰጥተህው በዛ ነገር ለመመራት አትሞክር፡፡ የምታየውም ነገርም ሁሉ እውነት ነው ብለህ አትመን፡፡

ነፍስህ ከነትክመቷ እንደተፈጠረች ሁሉ የስሜት ህዋሶችህም የራሳቸው የሆነ ድክመት አላቸው፡፡  ልክ እኔና አንተ የተዋወቅን

ሰዓት ላይ ነው በህይወት መኖራችን መረጋገጥ የሚችለው፡፡ አለበለዚያ ለኔ አንተ የለህም ላንተም እኔ የለሁም፡፡ በህይወት

መኖርህን የምታውቀው አካባቢህ ካሉት ነገሮች ጋር ካለህ ግንኙነት አንፃር ነው፡፡ ሰውነትህን ብትመለከት የተገነባው

በውስጥህ ካሉት የአካል ክፍሎችና ለብሰህው ባለው ቆዳህ አማካኝነት ነው፤ ሰው የሚባለውን ቅርፅና ስብዕና ይዘህ ልትኖር

የቻልከው። ሁለቱ አካላቶች ካልተግባቡ በህይወት መኖር አትችልም፡፡ እውናዊውም አለም የለም፡፡
አንተ ራስህ የእውነት አለህ ላልከኝ ደግሞ …በእርግጥም አካባቢህ ልክ እንደምታያቸው የተፈጥሮ ውጤቶች ሁሉ በተመሳሳይ

ሁኔታ እኔም እንደዛው እገለጣለሁ…ሆኖም ይህ ሁሉ እውነት አይደለም፡፡ አንተ ካላየህኝና ካልሰማህኝ በፍፁም ላንተ እውነት

ልሆንልህ አልችልም፡፡"
“አንድ የሚያሰጋኝ ነገር አለ፡፡ እውነት እየተለማመድኩት ያለሁት ማንነቴ ዘላለም አብሮኝ መሰንበት ግዴታው ነው ማለት

ነው? ምን ማለት ነው ዘላለማዊነት ማለትስ?"
“ዘላለማዊነት እጅህ ላይ ነው ያለው፡፡ ሆኖም ነጻነትህን እንደያዘብህ የጊዜ እስር አድርገህ ለመመልከት አትሞክር፡፡ አንተ

ከዘላለማዊነትም በላይ ነህ…ራስህን በጥልቀት መርምረህ ልትረዳው ከቻልክ፡፡ የፈራህው ከዚህ በኃላ ምን ልትሆን

እንደምትችል ማወቅ ስላቃተህ እና ያንንም የተለወጠ ተፈጥሮህን ከሌሎች እንግዳ ስነፍጥረቶች ጋር አስተጋብረህ እንዴት

አድርገህ መኖር እንዳለብህ በማሰብ ስለምትጨነቅ ነው፡፡ እንደጭስ በነው እንደሚጠፉ አድርገህ እያሰብክ በምድር ላይ ሳለህ

ሀላፊነቶችህን በሙሉ ለመወጣት ሞክር፤ ሆኖም እነዚህ ሁሉ እንግዳ የህይወት ጉዞዎች ትርጉም መስጠት የሚጀምሩት አንተ

ልክ እንደ ንጉስ መኖር የመረጥክ ሰዓት ላይ ነው፡፡ በለማኞች መካከል የምትመላለስ ንጉስ እንደሆንክ አድርገህ ሁሌ ራስህን

ለመመልከት ሞክር፡፡ እውነትህ ያለው በፈቀድከው ሰዓት በሚቀያየረው ጭንቅላትህ ውስጥ ነው፡፡  
“ስለዚህ እኔ ከሌለሁ እውነት አብሮ ይጠፋል ማለት ነው?”
“ያንተ እውነት...በትክክልም ይጠፋል፡፡ አንድ ነገር እርግጠኛ ሁን፡፡ በተከራየህው ሰውነትህ ውስጥ አንተ ብቻህን

አይደለህም፡፡ የፈጠረህ ፈጣሪ አለምን በአንተ አይን ውስጥ ማየት ይፈልጋል፡፡ አለምን የግሉ ማድረግ የሚሻውም የጥልቁ እና

የተከለከለው አለም አለቃ መንፈስ ባንተ ውስጥ አላማውን ማሳካት ይሻል፡፡ ሁለቱም የመንፈስ አካሎች በሰው ልጅ ነፍስ እና

ነፃ ፈቃድ ላይ የባለቤትነት ጥያቄ አላቸው፡፡ ሆኖም አንተ በነሱ እስካላመንክ ድረስ አንተ ውስጥ መስራት አይችሉም፡፡ ነፃ

ፈቃድህ ያንተን ብቻ ሳይሆን የማይታየው አለምን ሁሉ ማስተዳደር እና አሰራሩን መቀያየር እንደሚችል ተገንዘብ፡፡ ይህም

የገዢነት መንፈስ ዝም ብሎ አይመጣም፡፡ እያንዳንዱ ድብቅ እውቀት የራሱ ዋጋ አለው፡፡”
ሄኖክ ይህ መናፍስት ሀሳቡ ወደየት እየሄደ እንደሆነ የገባው ይመስላል፡፡
“አሁን እያልከኝ ያለህው የምፈልገውን እውቀት ለማግኘት ግዴታ ዋጋ መክፈል አለብኝ ማለት ነው?”
“እርግጥም እንደዛ ነው፡፡ ነፍስህን እቆጣጠራት ዘንድ አሳልፈህ ብትሰጠኝ አይተህና አልመህ የማታውቃቸውን አለማት

አሳይሀለሁ፡፡ የነዚህ አለማት አለቃም እንድትሆን አደርግሀለሁ፡፡ ስትናፍቀው የነበረውም አዲስ እውቀት በእጅህ ላይ

ታገኘዋለህ፡፡”
ሄኖክ የፈራው ጥያቄ መጣበት፡፡ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ድንገት ከጭንቅላቱ ውስጥ ቢፈልገው ድራሹ ጠፋበት፡፡

ነፍሱን ግዞት ሰዶ መሰልቸቱን ሊያከስም ቢፈልግም ከመሰልቸቱ ጀርባ ያለ የእውቀት ማነስንም ለመረዳት መሞከር እንዳለበት

ተረዳ፡፡ ነፍሱ ለሱ የትና እንዴት እየጠቀመችው እንደሆነ ቢጠየቅ መመለስ እንደማይችል ያውቃል። ሆኖም ይህ መናፍስት

አንድ የነገረው ነገር አለ። ያም ነገር የአንድን ነገር መኖር እና ሞራላዊ አቅሙን ለመረዳት ቦታው ጋር ሆኖ ማሰቡ ነገሮችን

እንደሚያቀልለት ነግሮታል፡፡ ሆኖም አንድ ጥያቄ ብቻ ነው መጠየቅ የፈለገው፡፡
“እባክህን መልስልኝ… ላንተስ ቢሆን የኔ ነፍስ ምን ይጠቅመሃል? ያለህ እውቀትና ግዛት በቂ ሆኖ አላገኘህውም? ወይንስ ልክ እኔ

ካንተ እውቀት ጎሎኝ እንደመጣሁ አንተም ህይወትህ ውስጥ የጎደለችውን ነፍስህን ልትሞላት ነው በማይታየው አለማት

ውስጥ ነፍሳትን ፍለጋ ስትመላለስ የምትከርመው?”
ድምፁ ለጥቂት ደቂቃዎች መልስ ሳይሰጥ ቆየ። እያሰበ መሆን አለበት ብሎ ገመተ፡፡ ሆኖም ይህ መናፍስት እያሰበ እና በሎጂክ

እየተመራ መልስ የሚሰጠኝ ከሆነ ከኔ ምን ተለየ ብሎ ማሰብ ጀመረ። ሁለቱም የሚፈልጉት ነገር ተመሳሳይ ሆነበት፡፡ ሁለቱም

የፍላጎታቸው እስረኞች እንደሆኑ አድርጎ መረዳት ውስጥ ገባ፡፡ ይህን እያሰበ መናፍስቱ መልስ መስጠት ጀመረ፡፡
“ሁለታችንም ፍላጎት ያለን ፍጡሮች ነን፡፡ የሚለያየው እውነታችን ብቻ ነው፡፡ እኔ የማውቀውን ማወቅ ትፈልጋለህ …እኔም

ያሻኝን እጠይቅሀለሁ፡፡ ለምን ነፍስህን ለመቆጣጠር እንደጠየኩክ ለማወቅ በቅድሚያ ነፍስህ ያላትን ዋጋ ልታውቀው

ይገባል፡፡ ይህን ቀድመህ መገንዘብ አለብህ፡፡ አሁን ምንአልባት እያወራህ ያለህው ከነፍስህ ጋር ሊሆን ይችላል። ምናልባትም

እኔ አንተ ውስጥ የነበርኩና አብሬህ ያደኩኝ መንፈስም ልሆን እችላለሁ፡፡ ሁለታችንም ስንገናኝ ህይወት መስርተናል፡፡ የምለው

እየገባህም እየመለስክልኝም ነው፡፡ እስቲ ይሄን ጥያቄ አንተ መልሰው…ካንተ ውጭ የሆነ አካል እንዴት አድርጎ ጭንቀላትህ

ውስጥ ህይወት መስርቶ መኖር ይቻለዋል? እንዴት አድርጎ ነፃ ፈቃድህን እንዳሻው ሊያመንሽረው ይሆንለታል?"
ሄኖክም መለሰ…”ይህማ ሊሆን የሚችለው እኔ ስፈቅድ ብቻ ነው፡፡”
መናፍስቱን ወዲያው ተከትሎ ይህን ጠየቀው…"ታዲያ ፍቃድህን የት ውስጥ እና እንዴት ነው ማግኘት የምትችለው?”
ሄኖክ …"በህይወት መኖር ስችል ነው፡፡ አሁንን መኖር ስችል፡፡”
ሄኖክ ይህን እንደተናገረ በሌላ ሀይል ተይዞ የነበር የሚመስለው የአይኑ ቆብ ነፃ ወጥቶ አይኖቹ ተገለጡ። አካባቢውን

ተመለከተ፡፡ ማንም የለም፡፡ እስካሁን ሲያወራ የነበረው ከራሱ ጋር እንደሆነ ተረዳ፡፡ የእውቀት መቃተቱ የፈጠረው እውቀት

እዚህ ድረስ ሲወስደው…በነጻ ፍቃዱ እና በግል ፍላጎቱ መካከል ያለውን ልዩነት አጥርቶ አልተመለከተውም ነበር፡፡
ሲያወራ የነበረው ሁሌም ነፃ ሆኖ በእውቀት ሲዋልል ከነበረው ማንነቱ ጋር እንጂ መናፍስት ጋር እንዳልነበረ አድርጎ አመነ፡፡

ነፍሱንም ሊሸጥ የፈለገው ለእውቀት ለሚዳክረው እና ከዛሬ ጀምሮ መኖር ለሚጀምረው አዲሱ ማንነቱ ነበር፡፡ የመናፍስቱ

ምልክት ላይ ሲመሰጥ አዕምሮው ውስጥ ያለውን የተደበቀ የእውቀት በር መክፈቻ ምልክት እንጂ የተለየ ጥበብ በውስጡ ይዞም

አልነበረም ብሎ ተረጎመው፡፡
ስለዚህ ሄኖክ ከዛሬ ጀምሮ አካባቢውን በአዲስ አይን በማየት አዲስ እውቀትን ማስተናገድ እንደሚችል ተገነዘበ፡፡ ሲጠራው

የነበረው መናፍስት ማንንም ሳይሆን ራሱን እንደሆነ ተገንዝነቦ ባሻው ሰዓት ማንኛውንም አይነት ሰው መሆን እንደሚችል

አመነ፡፡ ይህም እውቀቱ መናፍስት ፍለጋ እግሩን አጣምሮ በተቀመጠበት ክበብ ውስጥ ሆኖ ፈገግ እንዲል አደረገው፡፡

ሲናፍቀውም የነበረው ይህን ነበር…በራሱ ሀሳብ ውስጥ አዳዲስ አለማትን ሰርቶ ፈገግ እያለ መኖርን፡፡ ይህንንም ለማድረግ

ከአሁን ውጭ ምንም አይነት ጊዜ እንደሌለው በመረዳት አሁንን ለመኖር…በአሁን ውስጥ ያለን እውቀት እንዳያመልጠው

አሁኑ ውስጥ ሆኖ ህይወቱን እንዳዲስ ሊሰራት ከተቀመጠበት ተነሳ…አሁን ዘላለም ነው…ዘላለምም አሁን፡፡  

Read 534 times