Wednesday, 07 June 2023 18:04

ሁለት የዎላይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በፌዴሬሽን ም/ቤት ላይ ክስ መመሥረታቸውን አስታወቁ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

•  በቅርቡ በድጋሚ ሊደረግ የታሰበውን ህዝበ ውሳኔ እንደማይቀበሉትም  ገልጸዋል

ሁለት የዎላይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፤የወላይታ ዞን ወደፊት በሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ  ክልል ውስጥ ከሌሎች ዞንና ወረዳዎች ጋር እንዲደራጅ መወሰኑን በመቃወም፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ ክስ መመሥረታቸውን አስታወቁ፡፡ በቅርቡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በድጋሚ ሊደረግ የታሰበውን ህዝበ ውሳኔ እንደማይቀበሉትም ገልጸዋል፡፡

ፓርቲዎቹ በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን  የሚንቀሳቀሱት የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሲሆኑ፤ ዛሬ ከሰዓት በኋላ በ8 ሰዓት ላይ ቦሌ በሚገኘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ጽ/ቤት ውስጥ በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ወህዴግ) ሊቀ መንበር አቶ ጎበዜ ጎአ  እና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ሊቀ መንበር አቶ አማኑኤል ሞጊሶ፣ የዎላይታ ህዝብ የራሱን ክልል ለመመሥረት ያቀረበው ህገመንግሥታዊ ጥያቄ እየተስተናገደ ያለበት ኢ-ህገመንግሥታዊ ሂደት ምን እንደሚመስል ያወጡትን መግለጫ በንባብ ካሰሙ በኋላ፣ የወላይታ ዞን ወደፊት በሚመሰረተው የደቡብ ኢትዮጵያ  ክልል ውስጥ ከሌሎች ዞንና ወረዳዎች ጋር እንዲደራጅ መወሰኑን በመቃወም፣ በፌደሬሽን ምክር ቤት ላይ ክስ መመሥረታቸውን ያስታወቁ ሲሆን በቅርቡ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሊደረግ የታቀደው ህዝበ ውሳኔ የዎላይታን ህዝብ የማይወክልና ሂደቱም ኢ-ሞራላዊና ኢ-ህገመንግስታዊ በመሆኑ እንደማይቀበሉት ነው ያስታወቁት፡፡  

”ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም ተደርጎ ውድቅ በተደረገው ህዝበ ውሳኔ ለደረሰው የጉልበት፣ የጊዜ፣ የገንዘብ፣ የቁሳቁስ እንዲሁም የሞራል ኪሳራ ተጠያቂ የሚሆኑ አካላት ተጣርቶ በህግ ሳይጠየቁ፤ ለዎላይታ ህዝብ የራሱን ክልል ለመመሥረት የሚያስችል ዕድል፣ ህገመንግሥታዊ መብት በተነፈገበት ድጋሚ ህዝበ ውሳኔ ለማካሄድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰኔ 12 ቀን 2015 ዓ.ም ቀነ ቀጠሮ መያዙ ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ ከህዝቦች እኩልነት፣ ከእኩል ተጠቃሚነትና ከእኩል ተደማጭነት አንጻር ከፍተኛ ክፍተት ያለውና የህዝቡን ዕጣፈንታ አደጋ ላይ የሚጥል መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ” ብለዋል፤ ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ፡፡

ገዢው ፓርቲ በአሁኑ ሰዓት ዎላይታን ጨምሮ ስድስት ዞኖችንና አምስት ልዩ ወረዳዎችን ያለ ህዝብ ፍላጎት በሃይል በአንድ ክልል ጨፍልቆ ለማደራጀት የህዝብ ሃብት በማባከን ላይ ታች እያለ ይገኛል ያሉት ፓርቲዎቹ፤ ይህ በዎላይታ ህዝብ ላይ ህገመንግሥትን በሚጻረር መንገድ እየተፈጸመ ያለ አፈናና ኢ-ህገመንግሥታዊ ውሳኔ በህግ እንዲሻርና እንዲታገድ በፍርድ ቤት ክስ መሥርተናል ብለዋል፤ በመግለጫቸው፡፡

ፓርቲዎቹ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የወላይታ ዞን ከሌሎች መዋቅሮች ጋር እንዲደራጅ ያሳለፈው ውሳኔ እንዲሻርና የዞኑ ምክር ቤት ከአራት ዓመት ተኩል ገደማ በፊት ወላይታ ክልል እንዲሆን የሰጠው ውሳኔ እንዲጸና መጠየቃቸውን ነው ያስታወቁት፡፡

Read 1628 times