Saturday, 03 June 2023 20:16

ቤት ለእንግዳ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በየጧት ይመጣል
ማለዳ ይመጣል
አዳዲስ እንግዳ!
ለሰው ፀጉረ-ልውጥ ለሀገሩ ባዳ።
እንደ ለሰው-ማሰብ ያለ አዲስ እንግዳ
እንደ ጭንቀት ያለ አዳዲስ እንግዳ
እንደ ሀሴት ያለ አዳዲስ እንግዳ
እንደ ሀዘን ያለ ቅስም እንደመስበር
ወይ እንደብልግና
ወይ እንደማቀርቀር
ድንገት ሳይጠበቅ ከተፍ የሚል ሀሳብ
አዳዲስ እንግዳ፣ ለቀልብ የማይቀርብ
ቀን በቀን ማለዳ
ሁሉም ይመጣሉ!
በል ተቀበላቸው!
ያዘን ማ´ት ቢሆኑም፤ ቤትን የሚያፈርሱ
ንብረት የሚያወድሙ
እንደ እንግዳ አክብረህ፣ በል ተቀበላቸው!
አንድ- ባንድ አጫውተህ
ለእያንዳንዱ ስቀህ
ኑ ግቡ በላቸው።
ማን ያውቃል ምናልባት፣ በእንግድነታቸው
ለተሻለ ደስታ እያዘጋጁህ ነው
እንግዳህ ብዙ ነው…
የጨለማ ሀሳብ የጽልመት ጥቀርሻ
የሀፍረት መቀመቅ የማንጓጠጥ ዋሻ
ሁሉም የአንተ እንግዶች፣ የአንተው እዳ
ናቸው
“ቤት ለእንግዳ´ኮ ነው ኑ ግቡ” በላቸው።
በሳቅ አጅባቸው።
ለአዳዲስ ሀሳቦች ደግ ሁን ውለታ ዋል
ምናልባት ማን ያውቃል?
የነገን ማን አይቷል?
ካልታወቀው አገር
ከወዲያኛው ማዶ
መንገድ እንዲመሩህ ተልከው ይሆናል!?
(ነ.መ)

Read 749 times