Saturday, 03 June 2023 19:53

ሁለት የፍቅር ትረካዎች- ከአዲሱ መፅሐፍ!

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 የአጫጭር ልብወለዶች ነው መጽሐፉ - “አዎ! እሱ ጋ ያመኛል” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ:: የአድኃኖም ምትኩ ድርሰት።
የትረካዎቹን ጠቅላላ ይዘትና የድርሰት ጥበቦቹን በደፈናው ከመዳሰስ፣ ከዳር እስከ ዳር ከመቃኘት ይልቅ፣ ሁለት አጫጭር ትረካዎችን በምሳሌነት ብንመለከት መርጫለሁ። የትኛውን እናስቀድም?
ሁለቱም ትረካዎች ፈጣን ናቸው። - የመስፈንጠሪያ ሰበባቸው ምንም ሆነ ምን፣ ወደ ዋናው ታሪክ ይንደረደራሉ። ጥሩ ነው። ለነገሩ፣ ረዥም ልብወለድም፣ ገና ከመነሻው ወደ ታሪኩ ህብለ ሰረሰር ቢገሰግስ ይመረጣል። ለአጭር ልብወለድ ግን፣ ፍጥነት የግድ ነው።
ተዓማኒነትንና አስደናቂነትን አንድ ላይ የማዋሀድ ጥበብም አሟልተዋል - ሁለቱም አጫጭር ትረካዎች።
በአንድ በኩል፣ የገፀባሕርያትና የታሪክ ተዓማኒነትን፣…
 በሌላ በኩልም ያልተጠበቁ አስደናቂ የታሪክ ቅያሶችን ወይም እጥፋቶችን በብልሃት ማሟላት፣ አንዱ የጥበብ መለኪያ ነውና።
እስቲ እኛም ለመፍጠን እንሞከር። አንዱን እናስቀድምና፣ ከአጀማመሩ ተነስተን ትረካውን እንመልከት፤ እናጣጥም።
ከቀልድ እስከ ረዥም ልብወለድ፣ ከአጭር ግጥም እስከ ትያትር ሁሉም የፈጠራ ድርሰቶች፣ የዚህ ተዓምር ጌቶች ናቸው። ተዓማኒ የታሪክ ጅረትንና አስደናቂ የታሪክ እጥፋትን በአንድነት ማዋሃድ፣… ለዚያውም በፍጥነት!
ኀሰሳችን ከሽፎ እንጂ
“ጥዑም ጊዜ ላይ ነበርን። ወይን እየተጎነጨን፣ እየተሳሳምን”…
የትረካው አጀማመር፣… ያው፣… “መዋደዳቸውን ያዝልቅላቸው” የሚያስብል ነው። “መጨረሻቸውን ያሳምርላቸው” የሚያሰኝ፣ ከፍቅር ታሪክ ውስጥ የተቀነጨበ አንድ ጥዑም ጊዜ ሳይሆን ይቀራል? ጨዋታቸውም፣… ዘና ያለ፣ ደግሞም ከልብ የመነጨ ይመስላል። እንዲህ ይላል።
ትክ ብዬ ሳያት፣ ፈገግ ብላ፣ “እቺን የመሰለች ልጅ ጠበስክ ኣ?” አለችኝ -ወደ ራሷ እያመለከተች። በትንሹ ፈገግ አልኩ። ፈገግታዬን እንደ መስማማት ቆጥራ፣ የሚያምር ፈገግታዋን እያሳየችኝ፣ “እናትህማ መርቀውሃል” ስትለኝ”፣…
የትረከካውን ጅረት እየተከተላችሁ፣…የሚያስቀና ፍቅር ብላችሁ ልታደንቁ ትችላላችሁ። ነገር ግን፣…
…”ይሄኔ ነው የልቤ እውነት ያመለጠኝ።” ይለናል። ይቀጥላል።
“ታወቂያለሽ ግን አንቺ ህልሜ እንዳልሆንሽ። የመጣሽበት መንገድ፣ ዕቅድሽ፣ መርህሽ፣ ከእኔ ጋር መች ይሄዳል?” አልኳት።
ዎው፣ ዎው… ዋው! ምን ሆኗል? በጠራ ሰማይ ላይ መብረቅ፣… ምን የሚሉት ጨዋታ ነው ይሄ?  ዘመኑ ነው በማንኛውም ሰዓት መብረቅ ጠብቁ! ዱብዳ ያልሰማችሁበት ቀን አለ? የዘመኑ መንፈስ ይሆን? ወይስ፣ መጠጡ ወይኑ በዛ? እስቲ ጉዱን እንስማለት።
ሽማግሌ ከላክሁኝ በኋላ፣ በጋራ ስለምንወልዳቸው ልጆቻችን ስናወራ ከርመን፣ እንዴት እንዲህ ይባላል? ትበሳጫለች ብዬ ነበር። ግን፣… ረጋ እንዳለች፣ ፊቷ ሳይለዋወጥ ትክ ብላ አየችኝ። ቅፍፍፍ የሚል ስሜት ዋጠኝ። ምናለ አስማተኛ በሆንኩና እንዳልሰማች ማድረግ፣… እንዳልተናገርኩ መሆን ብችል።
“ፍቅርን የመሰለ አስማት” በስለታም ቃላት አስተንፍሶ ሲያበቃ፣ ሌላ አስማት ይመኛል። ፍቅረኛው፣ ሙሽሪት ለመባል የተቃረበች እጮኛው፣ እንደ ሐውልት ፊቷ ሳይለዋወጥ የተቀመጠችው፣ ድንጋጤው አደንዝዟት ቢሆን ነው። ለማመን ቢከብዳት ይሆናል! መቼም ሳትፈነክተው ከተረፈ፣ ትልቅ አስማት ነው? “ህልሜ አይደለሽም” የተባለች ፍቅረኛ ምን ልትል ትችላለች?
“ትክክል!!” አለች።
ምን? ትክክል! ምን ለማለት ፈልጋ ነው። ኧረ ተናሪ። ያለ ጎትጓች እንዲህ ትናገራለች።
…”ጊዜው አሳዝኖን ነው አብረን የሆንነው። አብረን ሆነን በስሱ ሌላ የፍለጋ ሙከራ ስላልተሳካልን ነው የምንጋባው። `Messenger`ህን ከፍቼ አይቻለሁ። የምታወራቸውን እንስቶች ቀልብ ለመግዛት የምትሄድባቸውን መንገዶች፣ መሻፈዶች፣ ላጤ ነኝ ጨዋታዎች፣ ብልግናዎች ተመልክቻለሁ። ሁሉም ከእኔ ጋር አንድ ዓይነት ነበሩ። የማደርገውን ነበር የምታደርገው። ከፍቶኝ ነበር። እንዳላኮርፍ፣ እንዳልጨቀጭቅህ፣ እንዳልጣላህ ካንተ አለመሻሌ አሸማቀቀኝ። የብዙ ሰዎች ትዳር እንዲህ እንደሆነ አይቻለሁ፤ ከገቡበት በኋላ በልጆቻቸው ይጽናናሉ። ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሚስት እና ባላቸውን እየከሰሱ ኑሮን ይገፉታል።”
በሰርግ ዋዜማ፣ በየፊናቸው እንዲህ አይነት የፍንዳታዎች ናዳ የሚያወርዱት ምንድነው? ደግሞ፣ የሷ ባሰኮ። መች በዚህ አበቃች? እንዲያውም “ተመስጌን ብንል ይሻላል” የምትል ትመስላች። “የፍቅር ትዳር”፣… ከንቱ ምኞት እንደሆነ ትነግረዋለች።…
ለዛ ነው እንከን የለሽ ትዳር የሚያስሱት ቆመው የሚቀሩት! በቆዩ ቁጥር መለኪያቸውን እየቀየሩ፣… ካጣጣሉት ከተጠየፉት የኑሮ ቀንበር ላይ ራሳቸውን ያገኙታል። ለዛ ነው እንደሚታረድ በግ ሁሉን እያወቅኩ ሽማግሌ ስትልክ፣ ቀለበት ስታጠልቅልኝ፣ የልቤን እውነት አፍኜ የምከተልህ።”
ሲዘበራረቅብኝ ይታወቀኛል።… በዚህ ደረጃ ይገባታል ብዬ አላሰብኩም። ሴት ልጅ ትታለልልሃለች እንጂ አታታልላትም።…
ለምን ታዲያ አብረን እንሆናለን ሁለታችንም እንዲህ ከተሰማን? (ስሜታችንን ከተዋወቅን?)… አለማወቅ ጠቀሜታ ይኖረው ይሆን? አንዳንድ እውቀት ምቾት አይሰጥም። እውቀት ትካዜን ታበዛለች እንዲል መጽሐፉ። አንዳንድ ውይይቶች ሽንቁር ያበጃሉ። የጀመርኩትን ወይኔን በአንድ ትንፋሽ ወደ ጉሮሮዬ አንቆረቆርኩት።
እንዳለችው ፍርሀት ነው? እጦት ነው? መላመድ ነው? ምን ይሆን ያጋመደን?... እውነታ ከተዘራዘሩ በኋላ እንዴት ጎጆ ይቀለሳል?...
እንዲህ ከተፈላሰፈ በኋላ “ያጋመዳቸውን” ነገር ለመቁረጥ፣ በርካታ ምክንያቶችን ይደረድራል። ምክንያት ይሁኑ ማመካኛ እርግጡን እናንተ ፍረዱ። ግን፣ “ልጅ ሳይመጣ፣ ንብረት ሳናፈራ፣ ኑሮ ሳይንጠን”… ቶሎ መቁረጥ ያስፈልጋል ባይ ሆኗል። “አሁን የምጎዳት ነገ ከምሰብራት አይበልጥም፤ ዛሬ የሚሰማኝ ሕመም ነገ ከሚያጋረጥብኝ መከራ አይበልጥም።” በማለትም “ቁርጡን” ይነግራታል።
“ማሬዋ ሰው ውድ ፍጡር ነው። ችኮላችን፣ ብልጣብልጥነታችን፣… የእኛ የራሳችን ከሆኑት ሰዎች ጋር እንድንሸዋወድ ያደርገናል።…
“ብቸንነት አባብቶን፣ የአቻ ግፊት ወትውቶን፣ መላመድ አሳስሮን፣ የቤተሰብ ግፊት ገፈታትሮን… ኑሮ አይመሰረትም። የሁሉም ጓዳ እንዲህ ነው ተብሎ፣ አዲስ ጎጆ አይበጅም። ሁሉም ሄዷል ተብሎ፣ እንኳን በስሕተት መንገድ በትክክለኛ መንገድ መሄድ ተገቢ አይደለም።… ከመጣንበት መንገድ የምንሄድበት ሩቅ ነው።…
ስለዚህ? …እንዲህ ስለ ሰው ልጆችና ስለ እውነት፣ ስለ ፍቅርና ስለ ትዳር ከተናገረ በኋላ፣… ከተፈለሰፈ በኋላስ? ራሳችሁ እንድትጨርሱት እንድታነብቡት ብተውላችሁ ይሻላል። ወደ ሁለተኛው አጭር ትረካ እናምራ።
“አንተ የሌለህ ጊዜ”
ተማሪ እያለን ለብዙ ጊዜ የፍቅር ሕይወት ተጋርተናል። ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ ትልቅ ሰው ከሆንን፤ የተለያየ የሕይወት መሥመር ውስጥ ከሰመጥን፣ አጀንዳዎቻችን ከተቀየሩ፣ ፍላጎት እና ህልማችን ሌላ ከሆነ በኋላ ስራ አገናኘን።
የወዳጅነት ሰላምታ ሰላም ተባባልን። ሁለታችንም አይናችን የጣት ቀለበት ሲያስስ ተገጣጠምን፤ ሁለታችንም አግብተናል። ያገናኘን ሥራ ላይ ተጠመድን። ደጋግሞ ሥራ አገናኘን፤ ደጋግመን `e-mail` ተለዋወጥ።
(ኦኦ። “የከረመ ፍቅር” የሚል ዜማ ሊያመጣ ነው እንዴ? የከረመ ፍቅር፣ የአስደሳች ትዝታ ግሩም ዓለም ሊሆን ይችላል። ግን በየፊናቸው የተለያየ ቀለበት ውስጥ ከገቡ በኋላ፣ የፍቅር ትዝታዎችን መምዘዝ፣ ከጥቅሙ ጣጣው መዘዙ ይብሳል። እንግዲህ፣ የከረመ ፍቅር የሚነካኩ ከሆነ፣ ምን ይባላል? “በጥበቡ ይርዳቸው”። ትረካው ይቀጥላል።)
አንድ ቀን ማኪያቶ እየጠጣን፣ ከላይ ከላይ እየተጨዋወትን፣… የሕይወትሽ አስቸጋሪ ጊዜ መቼ ነበር? አልኳት።
(የባሰ መጣ። የከረመ ፍቅር ሳይሆን የከረመ ሕመም መቀስቀስ ነው የፈለገው? እሱም ምክንያቱን የሚያውቀው አይመስልም።
 ሕመም ባይሰማው ይሆናል። ወይ የሷ ሕመም እንደሚበልጥ ለማየትና ራሱን ለማጽናናት… ወይስ የህሊና ወቀሳ ቢከነክነው? ምን ለማግኘት እንደፈለገ ምኑ ይታወቃል? ግን ይተርክልናል።)
አየችኝ፤ በትንሹ ፈገግ አለች። ፈገግ ስትል ዲምፕል አላት። ጥርሶቿ እንደ ድሮው ያምራሉ። ከፊት ለፊት በግንባሯ የመጡት ዘለላ ጸጉሮቿን በቄንጥ ወደኋላ መለሰቻቸው።
ዝም ብዬ ስመለከታት…
“አንተ የሌለህ ጊዜ። ማለቴ የተውከኝ ለታ” አለችኝ።
ስትቀልድ መስሎኝ ሳቅሁ። “እማ ትሙት” አለችኝ። በእናቷ ምላ ዋሽታ አታውቅም።…
ወደ ተመደብኩበት ዩኒቨርስቲ … መራመድ እንደመብረር እየከበደኝ ሄድኩ። ቀልቤን፣ ሳቄን ትቼ ነበር የሄድኩት።
ዶርም ሜቶቼ ለሚያወሩት ቋንቋ ባዳ ነበርኩ።
አብሮነታቸው ሲደራ ባይተዋርነት አራቆተኝ።… የካምፓስ ምግብ አልተስማማኝም፤… ናፍቆት ገላዬን በላው። ምግብ ስለማይስማማኝ ብዙ አልበላም። ሰለልኩ። የጨጓራ ህመም ጨፈረብኝ”
“እንደማትፈልገኝ፣… ሁሉ ነገርህ ይናገር ነበር። ስልክህ ረጅም ሰዓት ይያዛል። በፍጥነት ተቀያየርክ። ለስሜቴ መጠንቀቅ አቆምክ። እንደቀለልኩብህ ድርጊትህ ይናገር ነበር።… ነገሮችን ለማስተካከል በአፍላ ጭንቅላቴ ተፍጨረጨርኩ። ጓደኞቼ ሊሰሙኝ እንጂ መንገድ ለማሳየት ጥበብ እና ልምዱ አልነበራውም። ታላላቆቼ ጋ በዛ ዕድሜዬ በዚህ ጉዳይ ማውራት… ነውር ነበር።
ሸሸሁ!
የባሰ የቀዘቀዘ ድምጽ እንዳልሰማ ሸሸሁ። አዲስ የተወዳጀሃት ልጅ እንዳለች ስድስተኛ ስሜቴ አንሾካሾከልኝ። ስደውል በእሷ ፊት ተራ ጓደኛዬ ነች ዓይነት ወሬ እንዳታወራኝ ሰጋሁ። አትደውይልኝ እንዳትለኝ… ሸሸሁ።…
 ላ´ንተ ያለኝን ፍቅር የባሰ አጣጥለህ እንዳይቋጭ ስለሳሳሁ ሸሸሁ!
የጋራ ጓደኞቻችን በልቤ ያለውን ፍርሃት እንዳይነግሩኝ ሁሉንም ዘጋኋቸው። …ፍቅር ነክ ልብ-ወለድ ጽሑፎች ትውስታዬን ቀስቅሰው ናፍቆቴን እንዳያብሱት ማንበብ አቆምኩ።… ኪዳነ-ምህረት ቤተክርስቲያን ረጅም ሰዓት እቀመጣለሁ፣ ስብከት አዳምጣለሁ፣ ጉባኤ እከታተላለሁ።
ጾታዊ ፍቅር ስለሌለው፣ የሁሉ ነገር መሠረት ክርስቶስ እንደሆነ ስለሚነገር፣ በፈተናው የጸና የተባረከ ነው ስለሚባል፣ ብዙ ነገር በዲያቢሎስ ስለሚላከክ፣ የጭንቀታች ችግር መፍቻ፣… ጸሎት፣ ንሰሃ መሆኑን በአማረ ቋንቋ ስለሚያስተምሩ ጣፈጠኝ። መጽሐፍ ቅዱስን የሙጥኝ አልኩ። ችግሮቼ እየቀለሉኝ መጡ። አዳስ ሃይማኖተኛ ጓደኞች ተወዳጀሁ።
የመጀመሪያ ዓመት ጨርሼ ስመጣ፣… ግሬይ ሱሪ፣ ቀይ ቲሸርት አድርህ ቆመህ አየሁህ። ሳይህ፣ ከእስራቴ ከሱሴ መላቀቄ ነው የተገለጠልኝ። የሆነ ቀጫጫ ልጅ፣ ኖርማል ወንድ፣ ለዓይን የማይሞላ ልጅ አየሁኝ። ለካ ችግራችንን የምናይበት መንገድ የገዘፈ ስለሆነ ነው ከችግራችን በታች የምንሆነው።
… የሕመሟን ታሪክ ትነግረዋለች። ወይስ ተፍጨርጭሮ የመዳን ታሪክ? ከመነሻውስ፣ ፍቅር ነበራቸው? ወይስ ፍቅር የመሰለ ሱስ ነገር? “ለዓይን የሞይሞላ ልጅ” ሆነባትኮ!
አጀማመሩ፣ የከረመ ፍቅር ይመስላል። እጥፍ ብሎ፣ የከረመ ሕመም ይሆናል። ዞር ብለው  ሲያዩት የማንሰራራት ታሪክ ነው። ለዚያውም ለዓይን በማይሞላ ልጅ ሳቢያ የተፈጠረ ነው ያ´ሁሉ ውጣ ውረድ።


Read 608 times