Saturday, 03 June 2023 13:47

አማራ ባንክና ”ሳንቲም ፔይ” በጋራ ለመሥራት ተስማሙ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

አማራ ባንክ የተገልጋዩን  የክፍያ ሥርዓት አካች፣ ዘመናዊና ቀላል እንዲሁም ከካሽ ነጻ ለማድረግ ከሚያከናውናቸው መጠነ ሰፊ ሥራዎች ጋር በተያያዘ፣ ከሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ድርጅት ጋር በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ፡፡

አማራ ባንክና ሳንቲም ፔይ የስምምነት ሰነዱን የተፈራረሙት፣ ዛሬ ረፋድ ላይ በባንኩ ዋና መሥሪያቤት ነው፡፡

በዚህ ስምምነት መሰረት፣ አማራ ባንክ ከበርካታ የንግድ አካላት ጋር የሥራ ግንኙነት በመፍጠር ደንበኞች ለሚፈጽሙት ግብይት፣ በንግድ ተቋማት ውስጥ የሚገኘውን ኪው አር ኮድ፣ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው አማካኝነት በማንበብ፣ በቀላሉ እንዲከፍሉ ከማስቻሉም ባሻገር፣ ደንበኞች ልዩ ልዩ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉበት ይሆናል ተብሏል፡፡

ደንበኞች በጤና ተቋማት፣ በአልባሳት መደብሮች፣ በግንባታ ዕቃ መሸጫዎች፣ በኤሌክትሮኒክስ ሱቆች፣ በሆቴሎች፣ በካፌዎችና በሌሎችም ለተጠቀሙት አገልግሎትና ለፈጸሙት ግዢ፣ በተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸው ብቻ ክፍያ መፈጸም እንደሚችሉ ታውቋል፡፡

”ደንበኞች ካርድ መጠቀም ሳያስፈልጋቸው በስልካቸው ብቻ ክፍያዎችን መፈጸም የሚችሉ ሲሆን፤ የንግድ አካላት ደግሞ ምንም ዓይነት ተጨማሪ መሳሪያ ሳያስገጥሙ፣ ሳንቲም ፔይ በአማራ ባንክ ሂሳባቸው አማካኝነት የሚያዘጋጅላቸውን ኪው አር ኮድ ብቻ ለደንበኞች ዕይታ ምቹ በማድረግ ክፍያዎችን ይቀበላሉ፡፡” ብሏል፤ ባንኩ ባወጣው መግለጫ፡፡

በዚህ የክፍያ ማሳለጫ ነጋዴዎች ከደንበኞች ጋር ግብይት ለመፈጸም፣ ከአማራ ባንክ የክፍያ ልዩ ሂሳብና ከሳንቲም ፔይ አጋርነት ስምምነት እንዲኖራቸው የሚጠበቅ ሲሆን፤ በዚህም ደንበኞች በቀጥታ ወደ ነጋዴው የአማራ ባንክ ሂሳብ በስልካቸው ብቻ በቀላሉ ክፍያ ይፈጽማሉ ተብሏል፡፡

ይህ የክፍያ ማሳለጫ ለነጋዴዎችና ለደንበኞች ምቾትን የሚያጎናጽፍ ከመሆኑም ባሻገር ደንበኞች ካሉበት ሆነው የተለያዩ ክፍያዎችን መፈጸም እንደሚያስችላቸው ነው የተገለጸው፡፡

ሳንቲም ፔይ ፋይናንሻል ሶሉሽን አክስዮን ማህበር፣ በኢትዮጵያ የክፍያ ሥርዓት ኦፕሬተር ሆኖ እንዲያገለግል በብሔራዊ ባንክ የክፍያ ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 718/2011፣ ሃምሌ 2014 ዓ.ም የተቋቋመ ድርጅት ነው፡፡

Read 2489 times