Saturday, 03 June 2023 13:30

የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

   “ከእርግዝና በፊት በቂ ፎሊክ ንጥረነገር መኖሩን ማረጋገጥ ያስፈልጋል”
                       ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መሰረት በለጠ

      ከእርግዝና በፊት፣ በእርግዝና እና ጡት በማጥባት ወቅት የተመጣጠነ የአመጋገብ ስርአት ለእናቶች እና ለልጆች ደህንነት መሰረታዊ ነው። ሴቶች ከእርግዝና በፊት በሚመገቡት ምግብ አማካኝነት በእርግዝና ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ንጥረነገር ማከማቸት ይችላሉ። ይህም በእርግዝና ወቅት ከሚወሰዱ ምግቦች በተጨማሪ እንዲሁም እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ መከማቸት የሚገባቸውን ንጥረነገሮች በመያዝ በተለይም በመጀመሪያ የእርግዝና ወቅት ለፅንሱ እድገት የሚያስፈልጉ ንጥረነገሮችን ለማግኘት ያስችላል። ነገር ግን በዩኒሴፍ (UNICEF) መረጃ መሰረት በዓለምአቀፍ ደረጃ በብዛት የሴቶች የአመጋገብ ስርአት ከሚፈለገው አንፃር ደካማ ነው። ለምሳሌ እንደ አዮዲን፣ ብረት፣ ፎሌት፣ ካልሲየም እና ዚንክ ያሉ አስፈላጊ ንጥረ ነገሮችን የማግኘት እድላቸው አነስተኛ ነው። ይህም በእናቲች ላይ የደም ማነስ፣ ቅድመ-ኤክላምፕሲያ፣ ደም መፍሰስ እና ሞት ሊያስከትል ይችላል። እንዲሁም የሚወለደው ልጅ ህይወት እንዲያልፍ፣ ዝቅተኛ ክብደት ያለው ሆኖ እንዲወለድ እና የእድገት ችግር እንዲኖርበት ያደርጋል። የዩኒሴፍ መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ ከሚወለዱ ህፃናት መካከል ከ20 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ዝቅተኛ የክብደት መጠን አላቸው።
ነፍሰጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት ሊያገኙት ከሚገባቸው ንጥረነገሮች መካከል ፎሊክ ንጥረነገር አንዱ ነው። በወለጋ ዩኒቨርስቲ መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መሰረት በለጠ እንደተናገሩት ንጥረነገሩ ለተፀነሰው ልጅ የስነአዕምሮ (ማዕከላዊ የነርቭ ስርአት) አስፈላጊ ነው። የፎሊክ ንጥረነገር ከማክሮ ንጥረነገር (Macronutrients) ውስጥ ይመደባል። እንዲሁም ለሰውነት የሚያስፈልገው መጠን አነስተኛ ነው። “የምንፈልገው መጠን በጣም አነስተኛ ነው። ነገር ግን በጣም አስፈላጊ እና ጠቃሚ ነው።” ብለዋል የህክምና ባለሙያው።
ረዳት ፕሮፌሰር ዶ/ር መሰረት በለጠ የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት እና ተያያዥ ጉዳይ በነፍሰጡር እናቶች ላይ ስለሚያስከትለው ችግር ጥናት አድርገዋል። ጥናቱ የተደረገው በሀሮማያ በሚገኙ 12 ወረዳዎች ውስጥ ሲሆን 450 ነፍሰጡር እናቶች ተሳታፊ ሆነዋል። በጥናቱ ተሳታፊ ከሆኑት ነፍሰጡር እናቶች መካከል 50በመቶ የሚሆኑት የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት እንዳለባቸው መረጋገጡን ዶ/ር መሰረት ተናግረዋል።
የፎሊክ ንጥረነገር የሚገኝባቸው የምግብ አይነቶች
የእንስሳት ተዋፅኦ; ዓሳ፣ እንቁላል እና ቀይ ስጋ
እፅዋት; ጎመን፣ ቆስጣ እና ሰላጣ እንዲሁም በባህር ዳርቻ የሚበቅሉ ዕፅዋቶች
ንጥረነገሩ በብዛት የሚገኘው ከዓሳ መሆኑን ዶ/ር መሰረት ተናግረዋል። አክለውም በኢትዮጵያ በባህር ዳርቻ የሚበቅል እፅዋት በብዛት የሚገኝ ባለመሆኑ ነፍሰጡር እናቶች ቆስጣ እና ጎመን በመመገብ ንጥረነገሩን ማግኘት ይችላሉ ብለዋል።
በጥናቱ ውጤት መሰረት ፎሊክ ንጥረነገር እናቶች እንዳያገኙ ማለትም እጥረት እንዲፈጠር ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች;
የትምህርት ደረጃ; የትምህርት ደረጃ ከፍ እና ዝቅ ማለት የፎሊክ ንጥረነገር ያለው ምግብ ከመመገብ ወይም ካለመመገብ ጋር ተያያዥነት አለው። ማለትም ለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ የአመጋገብ ስርአታቸው የተስተካከለ ወይም ያልተስተካከለ እንዲሆን ያደርጋል።
ፎሊክ አሲድ ሰፕልመንቴሽን (Folic acid supplementation) አለመውሰድ; በህክምና ተቋማት የንጥረነገሩን እጥረት ለመከላከል የሚሰጠውን ይህን ህክምና(መድሀኒት) ያልወሰዱ እናቶች ለእጥረቱ ተጋላጭ ሆነዋል።
የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በስፋት የሚስተዋለው ነፍሰጡር እናቶች የቅድመ ወሊድ ክትትል ለማድረግ ወደ የህክምና ተቋም የሚሄዱት ከ3 ወር የእርግዝና እርዝማኔ በኋላ ነው። ስለሆነም ለንጥረነገሩ እጥረት መፈጠር አንደ አንድ ምክንያት ይጠቀሳል።
ከዚህ በተጨማሪ በዩኒሴፍ መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሴቶች አመጋገብ ላይ ተፅእኖ በማሳደር ነፍሰጡር እናቶች ለንጥረነገሮች እጥረት እንዲጋለጡ የሚያደርጉ 4 ምክንያቶች ተቀምጠዋል። የምግብ አቅርቦት ውስንነት መኖር እና የምግብ ዋጋ ከፍተኛ መሆን፣ የፆታ እኩልነት አለመኖር እንዲሁም ማህበራዊ እና ባህላዊ እሴቶች ሴቶች ስለአመጋገብ ወይንም እራሳቸውን ስለሚንከባከቡበት መንገድ በእራሳቸው ውሳኔ እንዳይወስኑ የሚያደርጉ (የሚገድቡ) ናቸው።
እንደ ዶ/ር መሰረት በለጠ ንግግር አንዲት ነፍሰጡር እናት ፎሊክ ንጥረነገር ማግኘት ያለባት በመጀመሪያ የእርግዝና 28 ቀናት ውስጥ ነው። “የተፀነሰው ልጅ የነርቭ ስርአት ተገንብቶ የሚያልቀው በመጀመሪያው የእርግዝና 28 ቀናት ውስጥ ነው። ስለሆነም ከዚህ ጊዜ በኋላ ነፍሰጡር እናት ንጥረነገሩን በብዛት ብትወስድ እንኳን ለውጥ(ጥቅም) አይኖረውም” በማለት ዶ/ር መሰረት ተናግረዋል። እንዲሁም በዋናነት ፅንስ ከመፈጠሩ አስቀድሞ የንጥረነገሩ ክምችት በሰውነቷ ውስጥ እንዲኖር ማድረግ እርግዝና ከተፈጠረ በኋላ ለፅንሱ ጠቃሚ(ግብአት) ይሆናል።
የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት የሚያስከትለው ችግር
የጀርባ አጥንት ችግር; የጀርባ አጥንት (Spinal cord) ክፍት እንዲሆን በማድረግ የእንቅስቃሴ (መዘርጋት እና ማጠፍ) ችግር እንዲያጋጥም ያደርጋል
የአዕምሮ ችግር; ጭንቅላት በውሀ እንዲሞላ እና ትልቅ እንዲሆን በማድረግ የማሰብ ችሎታን ይቀንሳል
የወሊድ ጊዜ ሳይደርስ(አስቀድሞ) እንዲወለድ ማድረግ
የክብደት ማነስ; ማንኛውም ጤናማ ልጅ ሊኖረው ከሚችለው ከ2500 ግራም በታች ክብደት እንዲኖር ያደርጋል። ይህ የክብደት ማነስ ለተለያዩ በሽታዎች ያጋልጣል።
የእርግዝና የመጀመሪያ 28 ቀናት ካለፉ በኋላ የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት ሊስተካከል የሚችል ባለመሆኑ ለእናት የሚሰጥ ህክምና የለም። ነገር ግን በእጥረቱ ሳቢያ ጉዳት ደርሶበት ለተወለደ ልጅ ህክምና ይሰጣል። ይህም እጥረቱን የሚያካክስ ምግብ እንዲመገብ እንዲሁም የጀርባ አጥንት ቀዶ ጥገና ማድረግ ነው።
የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት መከላከያ መንገድ
እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ የህክምና ተቋም በመሄድ በሰውነት ውስጥ ያለውን የፎሊክ ንጥረነገር መጠን ማወቅ እና መጠኑ የተስተካከለ እንዲሆን ማድረግ እንዲሁም የመጠኑን መስተካከል ማረጋገጥ
የፎሊክ ንጥረነገር ያላቸውን ምግቦች እርግዝና ከመፈጠሩ አስቀድሞ መመገብ
በህክምና ተቋም የሚሰጠውን የፎሊክ ንጥረነገር ሰፕልመንቴሽን መውሰድ
ዶ/ር መሰረት በለጠ እንደተናገሩት በነፍሰ ጡር እናቶች ላይ የሚያጋጥመውን የፎሊክ ንጥረነገር እጥረት ማጥናት ያስፈለገው ማለትም የጥናቱ ዋና አላማ የችግሩን ስፋት ለማወቅ ነው።
እንደ ባለሙያው ንግግር እንደዚህ አይነት ጥናቶች በሌሎች ሀገራት የፓሊሲ አቅጣጫ ለማስተካከል፣ ግንዛቤ ለመፍጠር እና የምግብ አቅርቦት ለማመቻቸት ጥቅም ላይ ይውላሉ።
ስለሆነም በኢትዮጵያ ይህ የጥናት ውጤት ተገቢው አገልግሎት ላይ እንዲውል ጥረት እንደሚደረግ ባለሙያው ተናግረዋል። እንዲሁም እናቶች የፎሊክ ንጥረነገር ያላቸውን ምግቦች እንዲመገቡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Read 517 times