Saturday, 03 June 2023 13:21

በታላቁ አንዋር መስጂድ በፀጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት የሰዎች ህይወት ማለፉ ተገለጸ

Written by  መታሰቢያ ሳሣዬ
Rate this item
(2 votes)

በትላንትናው ዕለት ለጁምአ በወጡ የሙስሊም ምዕመናን ላይ በፀጥታ ሃየሎች በተተኮሰ ጥይት ቁጥራቸው በውል ያልተረጋገጠ ሰዎች መሞታቸውን ምንጮች ተናገሩ።
በትናንትናው ዕለት የመንግስት በመስጂዶች ላይ እያካሄደ ያለውን  ፈረሳ እንዲያቆምና የፈረሱትን መስጂዶች እንዲያሰራ ተቃውሞ በማሰማት ላይ የነበሩ ሙስሊም ምዕመናን ከፀጥታ ሃይሎች በተከፈተባው ተኩስና በአስለቃሽ ጭስ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶባቸዋል ተብሏል።በጥይት ተመተው ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች ወደ አሜን ሆስፒታል እንዲወሰዱ መደረጉን የገለጹት ምንጮች፤ በርካታ በጥይት የተመቱና በግርግሩ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች በመስጂዱ ግቢ ውስጥ መታየታቸውንም ገልጸዋል።የጸጥታ ሃይሎች መንገዱን በመዝጋታቸው ሳቢያ አንቡላንሶች በስፍራው ደርሰው ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ወደ ህክምና ቦታ ለማድረስ እንደተቸገሩም ተናግረዋል።
በታላቁ አንዋር  መስጂድ የጁምአ ሶላት በመስገድ ላይ የነበሩ ህዝበ ሙስሊም ላይ ያለርህራሄ በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተወሰደውን እርምጃ አጥብቀው እንደሚቃወሙና የተናገሩት ኡስታዝ አቡበከር፤ የፀጥታ ሃይሎች በንጹሃን ላይ ከሚወስዱት እርምጃ እንዲታቀቡ ኡስታዝ አቡበከር አሳስበዋል። በመስጂዱ ተጠልለው በሚገኙና በጥይት ተመትተው የወደቁ ወገኖች አስቸኳይ ህክምና እንዲያገኙም ኡስታዝ ጠይቀዋል። ባለፈው ሳምንት አርብ በተመሳሳይ በመርካቶ አንዋር መስጂድና በኒን መስጂድ በተቀሰቀሰ ግጭት ቢያንስ ሁለት ሰዎች መሞታቸው መዘገቡ ይታወሳል።
ማተሚያ ቤት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ በጉዳዩ ላይ ከመንግስትም ሆነ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉባኤ የተሰጠ መግለጫ የለም።

Read 1492 times