Saturday, 27 May 2023 17:13

ሽንፈትን (ውድቀትን) አታስቡት!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

የስኬታማ ህይወት ትልቁ እንቅፋት፣ የመውደቅ ፍርሃት ነው፡፡ እንቅፋቱ ውድቀት ራሱ ሳይሆን ፍራቻው ነው፡፡ እንደውም መውደቅ የበለጠ ያጠነክራችኋል፤ የበለጠ ቁርጠኛ  ያደርጋችኋል፡፡ የመውደቅ ፍርሃት ወይም ውድቀትን መጠበቅ ግን ሃሳባችሁንም ሆነ ተግባራችሁን ያሽመደምደዋል፡፡
አንድ ወጣት ጋዜጠኛ በአንድ ወቅት የIBM መሥራች ለነበረው ቶማስ ጄ. ዋትሰን (ሰር) እንዲህ ሲል ጠይቆት ነበር፤ “እንዴት በፍጥነት የበለጠ ስኬታማ መሆን እችላለሁ?” ዋትሰን ሲመልስም፤ “በፍጥነት ስኬታማ ለመሆን የምትሻ ከሆነ የውድቀትህን መጠን ከፍ አድርገው” ብሏል፡፡
ወደፊት ለመጓዝ ድፈሩ፡፡ በጥረታቸው ሚሊዬነር ለመሆን የበቁ ሰዎች ቁማርተኞች አይደሉም፡፡ ነገር ግን ወደ ግባቸው ለመድረስ   አደጋዎችን  ለመጋፈጥ ፈጽሞ አያመነቱም፡፡ ምናልባት ባለጸጋ ለመሆን ዝግጁ መሆናችሁን የሚያረጋግጠው ትልቁ ነገር፣አደጋዎችን መጋፈጥን በተመለከተ ያላችሁ አመለካከት ነው፡፡
ምንጊዜም ስኬታማነታችሁን አደጋ ላይ ከሚጥሉ ሁኔታዎች ጋር ስትጋፈጡ ተከታዩን ጥያቄ ለራሳችሁ አቅርቡ- “በእርምጃዬ ብገፋበት የሚደርስብኝ የመጨረሻው አስከፊ ነገር ምንድን ነው?” ከዚያም በነዳጅ ሃብት የበለጸገው ቢሊዬነሩ ጄ.ፖል ጌቲ የሚለውን ተግብሩ - “ያ አደገኛ ነገር ምንም ይሁን ምንም ፈጽሞ እንደማይከሰት እርግጠኛ መሆን!”
ሃቁ ምን መሰላችሁ? መውደቅን የማይፈራ ማንም የለም፡፡ ሁሉም ማጣትና ድህነትን ይፈራል፡፡ ሁሉም ስህተት መፈጸምና  መሰናከልን አይሻም፡፡ ሚሊዬነሮች ግን አውቀውና  ሥራዬ ብለው ይህን ፍርሃት ይጋፈጡታል፡፡ እናም ያሻቸውን ከማድረግ የሚያስቆማቸው ማንም የለም፡፡ ታዋቂው ገጣሚ ዋልዶ ኤመርሰን፤ “የምትፈራቸውን ነገሮች ማከናወንን የህይወትህ አካል አድርገው፡፡ የምትፈራቸውን ነገሮች ከሰራህ ያለ ጥርጥር ፍርሃት ይሞታል፡፡” ይላል፡፡  
በድፍረት ስትንቀሳቀሱ አንዳች የማታዩት ኃይል ለድጋፍ አጠገባችሁ ይቆማል፡፡
እያንዳንዱ የድፍረት እርምጃ ደግሞ የወደፊት ወኔያችሁንና አቅማችሁን ያሳድገዋል፡፡ ስኬት እንደምትጎናጸፉ እርግጠኛ ባልሆናችሁበት ሁኔታ ወደፊት ለመጓዝ እርምጃ ስትወስዱ  ፍርሃታችሁ ጠፍቶ ድፍረታችሁና ልበ ሙሉነታችሁ ይጨምራል፡፡
 የማታ ማታም አንዳችም ነገር የማትፈሩበት ደረጃ ላይ ትደርሳላችሁ፡፡
“APPOLLO 13”በተሰኘው ምርጥ ፊልም ላይ ሽንፈትን በተመለከተ የናሳ ስፔስ ቁጥጥር ሃላፊ ኢዩጂኒ ክራንትዝ የተናገረው ምርጥ አባባል ተጠቃሽ ነው፡፡
የህዋ ጣቢያው ሰራተኞች ስለ መንኩራኩሯና ጠፈርተኞቹ መጥፋት ማሰብ በጀመሩ ወቅት ጮክ ብሎ፤ “ሽንፈት አማራጭ አይደለም” ብሏቸዋል፡፡
እንግዲህ የናንተ ሥራ ሚሊዬነር ለመሆን ቁርጠኝነት ማሳየት ነው፡፡ የናንተ ሥራ ቁርጥ ያሉ ግቦችን መቅረጽ ነው - ከዚያም በጽሑፍ አስፍራችሁ በየዕለቱ መተግበር፡፡ ሁልጊዜም ግባችሁን ለማሳካት ስትንቀሳቀሱ ታዲያ፣ “ሽንፈት አማራጭ አይደለም” የሚለውን ልታስታውሱ ይገባል፡፡ ይሄ አመለካከት ነው፣ ከምንም ነገር የበለጠ ዘላቂ ስኬትን የሚያረጋግጥላችሁ፡፡
***
ውድቀትን ወደ ድል መቀየር ይቻላል!
በህይወት ጉዟችን  ሽንፈት ወይም ውድቀት ሲገጥመን ሁለት አማራጮች አሉን፡፡ አንድም ወድቆ ወይም ተሸንፎ መቅረት ነው አሊያም ከውድቀታችን ተምረን ለቀጣዩ  ድል መትጋት ነው፡፡ ወድቆ መቅረት ትክክለኛው አማራጭ አይደለም፡፡
የስኬት መንገዳችንን  ለመጥረግ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰናክሎችን ወይም ፈተናዎችን ከወዲሁ ማጥናትና መፈተሽ ብልህነት ነው፡፡፡ የሥነልቦና ዝግጅት ለማድረግና አማራጮችን በፍጥነት ለመውሰድ ያስችለናል፡፡
ብዙ ውጤት የጠበቅንበት ሥራ ባላሰብነው መንገድ ሳይሳካ ቢቀር (ፌይል ቢያደርግ) ምንድነው ማድረግ የሚጠበቅብን? ያልተሳካበትን ምክንያት በፍጥነት መርምረን፣  ከስህተቱ  መማርና  ለቀጣይ የስኬት ጉዟችን መትጋት ይገባናል፡ሁልጊዜም ራሳችሁንና ሥራችሁን ለመገምገም ድፍረት ይኑራችሁ፡፡ ጥቃቅን ስህተቶችና ክፍተቶችን እየተከታተላችሁ ከማረምና ከመድፈን ችላ አትበሉ፡፡ በራሳችሁ ሥራ ላይ ርህራሄ የለሽ ሃያሲ በመሆን ራሳችሁንና ሥራችሁን ከከፋ ጉዳትና ውድቀት መታደግ ትችላላችሁ፡፡
በሥራችሁ ላይ ችግር ሲገጥማችሁ ወይም ኪሳራ ሲደርስባችሁ ሰበብ ለመደርደር አትሯሯጡ፡፡ በዕድላችሁ ለማማኸኘትም አትሞክሩ፡፡ “እኔ እኮ አይሆንልኝም፤ዕድሌ ነው”  አትበሉ፡፡ ሰበብ በመደርደርም ይሁን በዕድል በማማኸኘት  ማንም የፈለገበት ውጤት ላይ አልደረሰም፡፡ የሚያዋጣው የችግሩን መንስኤ  በቅጡ መርምሮና ፈትሾ የመፍትሄ እርምጃ በመውሰድ ለተሻለ ውጤት  መትጋት ብቻ ነው፡፡
ያለማችሁትን ግብ ለማሳካት ጽኑና አይበገሬ  ሁኑ፡፡ በትናንሽ እንቅፋቶች ተስፋ ለመቁረጥና ለማቆም አትጣደፉ፡፡ አዳዲስ ያልተሞከሩ መላዎችንና ዘዴዎችን ተግብሩ፡፡ አዳዲስ አሰራሮችን ሞክሩ፡፡ ነገር ግን ውጤት ከማያመጣ ነገር ጋር የሙጥኝ ብላችሁ አትክረሙ፡፡
ውዱን ህይወትና ጊዜያችሁን በከንቱ ማባከን ሌላ ጥፋት ነው፡፡ የመጀመሪያው ዕቅዳችሁ (plan A) ካልተሳካ ወደ ሁለተኛው ዕቅዳችሁ (Plan B) ተሻገሩ፡፡
ልብ በሉ፤ ሁሉም ችግር በጎ ጎን አለው፡፡ ያንን በጎ ጎን ፈትሾ ማግኘት ግን የናንተና የናንተ ብቻ ሃላፊነት ነው፡፡
ከአቅም በላይ የሚመስል ትልቅ ፈተና ወይም ተግዳሮት ሲገጥማችሁ ከመደንገጥና ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ  አዕምሮአችሁን ክፍት አድርጋችሁ የመፍትሄ ሃሳቦችን አስሱ፡፡ የተሻለ ልምድ ያላቸው አዋቂዎችንና ባለሙያዎችን አማክሩ፡፡ በእርግጥም ከተጋችሁ  ውድቀትን ወደ ድል መቀየር ትችላላችሁ፡፡
(ምንጭ፡- ”ህይወትና ስኬት”)


Read 1512 times