Saturday, 27 May 2023 17:04

የማህፀን በር ካንሰር

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

  በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለምአቀፍ ደረጃ ሴቶችን ከሚያጠቁ የካንሰር በሽታ አይነቶች መካከል የማህፀን በር ካንሰር በ4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። እ.ኤ.አ በ2020 6መቶ 4ሺ በህመሙ የተጠቁ ሴቶች መገኘታቸው ይገመታል። እንዲሁም የ342ሺ ተጠቂዎች ህይወት ማለፉ ተመዝግቧል። በበሽታው መጠቃታቸው ከታወቀ አዲስ ታካሚዎች እንዲሁም ህይወታቸው ካለፈ ሴቶች መካከል 90በመቶ የሚሆኑት መካከለኛ እና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው ሀገራት ውስጥ ይገኛሉ።
የህብረተሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት መምህር አራጋው ተስፋው እንደተናገሩት ካንሰር ከሰው ወደ ሰው ከማይተላለፉ በሽታዎች ውስጥ ይመደባል። የማህፀን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር በመቀጠል ሴቶችን በማጥቃት በኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ይዞ ይገኛል። የማህፀን በር ካንሰር መንስኤ በመሆን በዋናነት የሚጠቀሰው ሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ መሆኑን ባለሙያው ተናግረዋል። እንዲሁም የእድሜ መጨመር (ከ50 ዓመት በላይ) ፣ በበሽታው የተጠቃ የቤተሰብ አካል ካለ ወይም ከነበረ (በዘር)፣ ሲጋራ ማጨስ እና የአልኮል መጠጥ ለበሽታው አጋላጭ ምክንያቶች ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ እንደ ባለሙያው ንግግር መንስኤው ሳይታወቅ የማህፀን በር ካንሰር ሊከሰት ይችላል።  
የማህፀን በር ካንሰር ምልክቶች
በግብረስጋ ግንኙነት ወቅት የህመም ስሜት መኖር
ደም መፍሰስ [ከግብረ ስጋ ግንኙነት በኋላ ወይም በማንኛውም ወቅት]
ከማህፀን የሚወጣ ያልተለመደ ፈሳሽ
ማህጸን አከባቢ የህመም ስሜት
የታችኛው የወገብ ክፍል ወይም ከሆድ ዝቅ ብሎ የህመም ስሜት መኖር
የወር አበባ መጠን መጨመር
የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት መምህር አራጋው በማህፀን በር ካንሰር የተጠቁ ሴቶች ከበሽታው ጋር ምን ያህል ጊዜ መቆየት እንደሚችሉ እንዲሁም ከበሽታው ለማገገም ስለሚፈጀው ጊዜ ጥናት አድርገዋል። ዓላማውም በ5 ዓመታት ውስጥ ምን ያህል የበሽታው ተጠቂዎች ከበሽታው እንዳገገሙ፣ ለምን ያህል ጊዜ ከበሽታው ጋር እንደቆዩ እና ህይወታቸው እንዳለፈ ለማወቅ ነው። በጥናቱ ከተካተቱ ከ441 የበሽታው ተጠቂ ሴቶች መካከል 18.6 በመቶ አገግመዋል ወይም ለ5 ዓመታት ያህል በህይወት ለመቆየት ችለዋል። እንዲሁም 95 ታካሚዎች (22በመቶ) ህይወታቸው አልፏል። የተቀሩት ታካሚዎች የህክምና ክትትላቸውን በማቋረጣቸው ያሉበት ሁኔታ አይታወቅም። ከሌሎች ተመሳሳይ ጥናቶች ጋር ሲነፃፀር ያገገሙ ታካሚዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ባለሙያው የተናገሩ ሲሆን ለዚህም እንደ ምክንያት የጠቀሱት ለህክምና የሚያገለግሉ ግብአቶች እጥረት መኖሩን ነው። ከዚህ በተጨማሪ የታካሚዎች ሙሉ መረጃ አለመኖር በጥናቱ ውጤት ላይ ክፍተት መፍጠሩን ተናግረዋል።
በተደርገው ጥናታዊ ፅሁፍ ውጤት መሰረት በማህፀን በር ካንሰር የተጠቁ ሴቶች ከበሽታው እንዳያገግሙ ምክንያት በመሆን የተጠቀሰው እድሜ እና የበሽታው ደረጃ ነው። እንዲሁም በበሽታው ተጠቅተው ህክምና እየተከታተሉ የነበሩ ታካሚዎች ህክምናቸውን እንደሚያቋርጡ ባለሙያው ተናግረዋል። ለዚህም ምክንያት የሆነው ታካሚዎች ከሚኖሩበት አከባቢ እስከ የህክምና ማዕከል ያለው ርቀት፣ የግንዛቤ እና የገንዘብ እጥረት፣ የህክምና ተቋማት ብዛት እና የግብአት እጥረት፣ በታካሚዎች ዘንድ በሽታው እንደማይድን የማሰብ እና ሌሎች ባህላዊ ወይም ሀይማኖታዊ የህክምና ዘዴዎችን የመጠቀም ሁኔታ በመኖሩ ነው።
“የካንሰር ህክምና በመከታተል ከበሽታው መዳን ይቻላል” ያሉት ባለትዳር እና የ1 ልጅ እናት የሆኑት ወ/ሮ ሂሩት ወንድወሰን ናቸው። ወ/ሮ ሂሩት እንደተናገሩት ስራቸው በጣም ውጥረት የሚበዛበት በመሆኑ ጤናቸውን አይከታተሉትም ነበር። የዛሬ 3 ዓመት አከባቢ በቅርብ ጓደኛቸው ጉትጎታ አማካኝነት የማህፀን በር ካንሰር ምርመራ አደረጉ። በምርመራውም “ወደ ሰውነቴ ያልተሰራጨ ነገር ግን ቃሉን ካልተሳሳትኩ ከካንሰር በፊት ወይም የካንሰር ምልክት ሴል መገኘቱን ተነገረኝ” ብለዋል። በሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የነበረ ቢሆንም ካንሰር የሚለው ቃል ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። በወቅቱ የነበረው ስሜታቸውንም “ካንሰር የሚለውን ቃል ከባለሙያዎቹ ገና ስሰማ የምሞት ነበር የመሰለኝ” በማለት ገልፀዋል። አክለውም “ተስፋ ቆረጥኩ፤ የ7 ዓመት ልጄን አሰብኩ፤ የባለቤቴ እና የወላጆቼን ድንጋጤ አሰብኩ። ስለምሰራው ስራ፣ ለወደፊት ስላቀድኩት ህይወት... ብቻ ምን ልበል የሞት መልአክ ፊትለፊቴ ቆሞ ነው የታየኝ” ብለዋል። ወ/ሮ ሂሩትን ከዚህ ስሜት ለመመለስ እና ለማረጋጋት የህክምና ባለሙያዎች ጥረት ቢያደርጉም እንዲሁም ስለ በሽታው ማብራሪያ ቢሰጧቸውም መረጋጋት አልቻሉም። “እንደደነዘዝኩ ከህክምና ተቋም ወደ ቤት ሄድኩ፤ እንደውም ትዝ ይለኛል ልጄን ከት/ቤት ወደ ቤት ስወስዳት እኔን ስታጣ እንድትጠነክር እራሷን የምታዘጋጅበት ንግግር ነበር እያወራሁላት የነበረው፤ ያንን ጊዜ ሳስበው  ይዘገንነኛል!” ብለዋል። እንደ ወ/ሮ ሂሩት ንግግር የባለለቤታቸው፣ የወላጆጆቻቸው እና የጓደኞኞቻቸው እገዛ ባይኖር ከበሽታው በላይ የስነልቦና ጉዳት ካጋጠማቸው የማህፀን በር ካንሰር የከፋ ጉዳት ሊያደርስባቸው ይችል ነበር።
ወ/ሮ ሂሩት ለማህፀን በር ካንሰር የሚሰጠውን ህክምና ተከታትለው ከበሽታው ማገገም ችለዋል። “በሽታው ወደ ሰውነቴ ሳይሰራጭ ሙሉበሙሉ መዳን ችያለው፤ ወደ ቀደመ ህይወቴ ተመልሼ እየኖርኩ ነው” በማለት ተናግረዋል። ወ/ሮ ሂሩት በሽታው የከፋ ደረጃ ላይ ቢሆን እና በህይወት የመቆየት ጊዜ ረዥም ባይሆን እንኳን ህክምና እየተከታተሉ ቀሪውን ጊዜ በአስፈላጊ ቦታ ማዋል እንጂ ተስፋ መቁረጥ አያስፈልግም ብለዋል። “ተስፋ በመቁረጤ ምን አተርፋለው? ዘገየም ፈጠን ሁላችንም መሄዳችን አይቀርም፤ ዋናው ቁምነገር ባለን ጊዜ ምን ማድረግ ችለናል የሚለው ነው” ብለዋል። እንደ ወ/ሮ ሂሩት በማህፀን በር ካንሰር የተጠቁ እንዲሁም በማንኛውም አይነት የካንሰር በሽታ የተጠቁ ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ ህክምናቸውን እንዲከታተሉ ነው ወ/ሮ ሂሩት መልዕክት ያስተላለፋት። አክለውም ሰዎች ጎልቶ የሚታይ አካላዊ ህመም ካላጋጠማቸው በቀር ለጤናቸው ትኩረት እንደማይሰጡ አስታውሰዋል። ስለሆነም ማንኛውም ሰው በበሽታ ሊጠቃ እንደሚችል በመገንዘብ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል። በተጨማሪም “ሴቶች የማህፀን ጫር ካንሰር ምርመራ እናድርጋ፣ እንዳጠቃላይ ያልወለዳችሁ ሴቶችም ብትመረመሩ፤ ባሎች (ወንዶች) በዙሪያችሁ ያሉ ሴቶች ምርመራ እንዲያደርጉ ብታበረታቱ በሽታው ሲገኝባቸው ደግሞ ብትደግፉ” በማለት ተናግረዋል።  “የቅድመ ካንሰር ደረጃ ላይ ማለትም በሽታው ሳይሰራጭ ከበሽታው ሙሉበሙሉ የማገገም እድል አለ” በማለት የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት መምህር አራጋው ተስፋው ተናግረዋል። እንዲሁም የበሽታው ደረጃ ከፍ ሲል ማለትም ካንሰር ወደ ሰውነት ሲሰራጭ ያሉ ከበሽትልው የማገገም እድል አነስተኛ ይሆናል። ነገር ግን ህክምናውን በመከታተል የህመም ስሜት መቀነስ እና በህይወት የሚቆይበትን ጊዜ ማራዘም እንደሚቻል ባለሙያው ተናግረዋል።
የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ መንገዶች
ቅድመ ምርመራ ማድረግ
የግብረ ስጋ ግንኙነት ከተለያዩ(ከብዙ) ሰዎች ጋር አለመፈፀም
በሽታው ሳይሰራጭ ወደ የህክምና ተቋም መሄድ
የሂውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ክትባት መውሰድ
በቤተሰብ ውስጥ በበሽታው የተጠቃ ሰው ካለ(ከነበረ) የህክምና ክትትል ማድረግ
የማህፀን በር ካንሰር ህክምና መከታተል [አለማቋረጥ
የማህበረሰብ ጤና ባለሙያ የሆኑት መምህር አራጋው ተስፋው በሽታው ቶሎ ከተገኘ የማገገም እድል ሰፊ መሆኑን ጠቅሰው ሴቶች(እናቶች) አስቀድመው ምርመራ እንዲሁም በሽታው ከተገኘ በኋላ ህክምና ክትትል እንዲያደርጉ መልዕክት አስተላልፈዋል። ከዚህ በተጨማሪም የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት የማህፀን በር ካንሰር ለመከላከል የጤና ማዕከላትን በማስፋፋት፣ ለባለሙዎች አስፈላጊውን ስልጠና በመስጠት እና ህብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲያገኝ በማድረግ በሽታውን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል።

Read 593 times