Saturday, 20 May 2023 15:18

ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት

Written by  ሀይማኖት ግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(0 votes)

ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎትን አስመልክቶ የህክምና ባለሙያዎችን ልምድ፣  አገልግሎቱን ለማግኘት በኢትዮጵያ ህግ መሰረት ስለተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎች እና ደህነነቱ ባለተጠበቀ መንገድ ጽንስ ማቋረጥ ያስከለው እንዲሁም እያስከተለ ስላለው ችግር ከዚህ ቀደም በነበረ እትም ለንባብ አቅርበናል። በዚህ እትም የዚህ ርእሰ ጉዳይን ቀጣይ ክፍል ቀርቧል።በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል ኢትዮጵያ የፓሊሲ ጥናት፣ ተግባቦት እና የውጭ ግንኙነት ከፍተኛ ስራ አስኪያጅ የሆኑት የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ምስክር ገበየሁ ፅንስ ከማቋረጥ ጋር ተያይዞ የነበራቸውን ልምድ ካካፈሉን ባለሙያዎች መካከል አንዱ ናቸው። የህክምና ባለሙያው እንደተናገሩት በሙያው ላይ ከዚህ ቀደም በነበራቸው ቆይታ ፅንስ ከማቋረጥ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ‘የእኔነት’ ስሜት አልነበራቸውም። “ፅንስ ማቋረጥ ከእምነት ጋር በተያያዘ ልክ ነው ብዬ አላምንም፤ እንደውም በጣም የምቃወም ሰው ነበርኩ፤ ሴቶች በእራሳቸው ጥፋት ያመጡት ነው፤ በእራሳቸው ጥፋት ላመጡት ችግር ደግሞ ዋጋ መክፈል አለባቸው በማለት ነበር ለረዥም ጊዜ የማስበው” ብለዋል። እንደ የህክምና ባለሙያው ንግግር ይህ እሳቤያቸው የተለወጠው ከ15 ዓመታት በፊት የወረዳ ጤና ፅ/ቤት ሀላፊ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት ነበር። ዶ/ር ምስክር በቅርበት የሚያውቁት ሰው(ዘመዳቸው) እህት ደም እየፈሰሳት እና እራሷን ልትስት እንደሆነ ተነገራቸው። ታካሚዋ ወዳለችበት አከባቢ በመሄድ የህክምና እርዳታ ከሰጧት በኋላ ለተጨማሪ ህክምና ወደ ሌላ የህክምና ተቋም ይዘዋት ሄዱ።
ባለታሪኳ ለደም መፍሰስ የተዳረገችው ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንስ ለማቋረጥ በመሞከሯ ነበር። ፅንሱ የተፈጠረው የቤት ሰራተኛ ሆና በምትሰራበት ወቅት በተቀራራቢ ጊዜ ውስጥ በቤቱ አሰሪ(አባወራ) እንዲሁም በልጃቸው አስገድዶ መደፈር ተፈፅሞባት ነው። ባለታሪኳ “ልጁን ብወልደው እንኳን የማን ልጅ ነው እላለው” በማለት ፅንሱን ለማቋረጥ ወደ ህክምና ተቋም መሄዷን ነው ዶ/ር ምስክር የተናገሩት። ነገር ግን የሄደችበት ክሊኒክ አገልግሎቱን ሊሰጣት አልቻለም። ቀጥላ ወደ ሌላ ክሊኒክ ስትሄድ ደግሞ የፅንሱ ሳምንት ስለገፋ አገልግሎቱን የመስጠት አቅም እንደሌለ ተነገራት። ስለሆነም ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንሱን ለማቋረጥ ሞከረች። ይህም የተፈፀመው በብረት(ሚስማር) ስለነበር ማህፀኗ ተጎዳ። ከማህፀኗ ደም ሲፈሳት የቆየችው ባለታሪክ የደም አይነቷ ኦ ማይነስ (O negative) ሲሆን ከእሷ ጋር ተመሳሳይ የደም አይነት በሆስፒታሉ ስላልነበር ደም ልታገኝ አልቻለችም። ህይወቷ አለፈ።
“እኛ ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ አገልግሎቱን ስንከለክል ደህንነቱ ባልተጠበቀ መንገድ ፅንሱን ያቋርጣሉ። ህይወት መጥፋቱ አልቀረም” ብለዋል የህክምና ባለሙያው። አክለውም ፅንሱን ለማዳን ተብሎ አገልግሎት አይሰጥም ሲባል ፅንሱን ብቻ ሳይሆን የእናትንም ህይወት እንደሚያሳጣ ካጋጠማቸው ሁኔታ መገንዘባቸውን ተናግረዋል። ዶ/ር ምስክር ከተፈጠረው ክስተት አስቀድሞ አገልግሎቱን ከእምነት ጋር በማያያዝ(ሀጢያት ነው በሚል) አለመስጠታቸውን አስታውሰው የባለታሪኳ ህይወቷ ካለፈ በኋላ ግን የፅንስ ብቻ ሳይሆን የእሷ[እናት] ህይወት መጥፋት እንደሚያስጠይቃቸው በማሰብ አገልግሎቱን መስጠት መጀመራቸውን ተናግረዋል። እንደ ባለሙያው ንግግር በሴቷ ላይ ጉዳቱን ያደረሱ አካላት ምንም አይነት ጉዳት ሳያጋጥማቸው ተጠቂዋ ግን ህይወቷን እስከማጣት እየደረሰች እንደ የህክምና ባለሙያ አገልግሎቱን አለመስጠት ተገቢ አይደለም። እንዲሁም ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት መስጠት ማለት ፅንሱ እንዲቋረጥ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በቅድሚያ በተቻለ መጠን እናትን አግባብቶ እርግዝናው እንዲቀጥል የማድረግ [የማማከር] አገልግሎትን ያጠቃለለ መሆኑን ተናግረዋል።
ዶ/ር ምስክር ገበየሁ በማሪስቶፕስ ኢንተርናሽናል መስራት ከጀመሩ በኋላ በአባቷ ወይም በወንድሟ የተደፈረች ሴት ማየታቸው ይህን አገልግሎት ለመስጠት ይበልጥ ፍቃደኛ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። “አባት ሲደፍር ፅድቅ ሆኖ ፅንሱ ሲቋረጥ ሀጥያት የሚሆንበት ሁኔታ ስላልታየኝ የእራሴንም ሆነ በዙሪያ ያሉ ሰዎችን አስተሳሰብ ለመቀየር ሞክሪያለው” ብለዋል። አክለውም “ከዚህ ቀደም እንደነበረኝ አመለካከት የቀበጡ ሴቶችን ፅንስ በማቋረጥ የማገዝ ሳይሆን ችግር ላይ ያሉ ሴቶችን ማገዝ እንደሆነ ለወጣት የህክምና ባለሙያዎች እየነገርኩ፣ እያሰለጠንኩ እና እያገዝኩ እገኛለው” ብለዋል ባለሙያው። እንዲሁም ባለሙያው እንደተናገሩት ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጡ የህክምና ባለሙያዎች እንዳይገፉ እና እንዳይገለሉ ስራዎችን በመስራት ላይ ይገኛሉ። በተጨማሪም ፅንስ የማቋረጥ ጉዳይ ከሴቶች ጋር ብቻ ይያያዛል። ይህም የሆነው ፅንስ ያለው ማለትም የእርግዝናው ውጤት የሚታየው በሴቶች ላይ በመሆኑ እና የወንዶች የፅንሱ አካል መሆን የሚረጋገጠው በቃል ብቻ በመሆኑ ነው ብለዋል ባለሙያው። እንደ ዶ/ር ምስክር ንግግር በቤት፣ በትምህርት ቤት እና በስራ ቦታ በወንዶች ላይ የግንዛቤ ስራ አለመሰራቱ ማህበረሰቡ ዘንድ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ፈጻሚዎችን ሳይሆን ተጠቂዎችን ጥፋተኛ የማድረግ ልማድ እንዲኖር አድርጓል።
ታያ በተባለ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ የስነተዋልዶ ጤና እና መብት ፕሮግራም ማኔጀር የሆኑት ጠቅላላ ሀኪም ልዕልና ሽመልስ ከዶ/ር ምስክር ገበየሁ ጋር በተመሳሳይ መልኩ “ወደዚህ ስራ ከመግባቴ በፊት ፅንስን ማቋረጥ በአጠቃላይ ደጋፊ አነበርኩም” ብለዋል። ለዚህም እንደ ምክንያት የሆናቸው በማህበረሰቡ ዘንድ ፅንስ ያቋረጡ ሴቶች የሚደርስባቸውን መገለል በመመልከታቸው እና ስለጉዳዩ ብዙም እውቀት ስላልነበራቸው ነው። “ዩኒቨርሲቲ ከገባሁ በኃላ የቅርብ ጓደኛዬም በዙርያዬ ያሉ ሴቶችም ይህ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው እና ህይወት ወደ መጥላት ሲያመሩ እንዲሁም ብቻቸውን ያመጡት ይመስል ሁሉንም ችግር ብቻቸውን ሲያሳልፉ ፍትሀዊ እንዳልሆነ ተሰማኝ” ብለዋል። “አብረውኝ ይማሩ የነበሩ በጣም ጎበዝ ተማሪዎች ለማህበረሰቡ አስተማሪ ይሆናሉ ተብሎ የሚታሰቡ በዚህ ሁሉ አልፈው አንዳንዶች ከአላማቸው ሲሰናከሉ አንዳንዶች ደግሞ ተጨማሪ ሸክም ሆኖባቸው ሳይ እኔስ ማነኝ? እኔ እራሴ በዚህ ቦታ ላለመገኘት ምን ዋስትና አለኝ? ደግሞስ እኔ ማነኝ እነሱን የምኮንነው” በማለት ሀሳባቸውን መቀየራቸውን ባለሙያዋ ተናግረዋል።
ዶ/ር ልዕልና እንደተናገሩት በታያ ውስጥ በዋነኛነት በወጣቶች የስነ-ተዋልዶ ጤና ላይ የጤና መረጃ የመስጠት እና አቅም የማጎልበት ስራ እየተሰራ ይገኛል። ወጣቶች የሚባሉት ከ18 -35 ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሲሆኑ ከ10-19 እድሜ ያላቸው ደግሞ አፍላ ወጣቶች ይባላሉ። ወጣቶች በህይወታቸው ትክክለኛውን ውሳኔ እንዲወስኑ የሚረዱ አቅም ማጎልበቻ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ባለሙያዋ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪም ወጣቶች ስልጠናዎች ካገኙ በኃላ ከውሳኔ ሰጪ አካላት ጋር ተገናኝተው ጥያቄ እንዲያቀርቡ እና መልስ እንዲያገኙ ይደረጋል። “የወንዶች ተሳትፎ አንድ ትልቁ እስትራቴጂያችን ነው” ብለዋል የህክምና ባለሙያዋ። የስነ ተዋልዶ ጤና ኘሮግራሞች ሴቶች ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ስለሚሰሩ እና የወንዶች ሚና ስለሚዘነጋ ውጤታማ አይሆንም በማለት አክለው ተናግረዋል። በአፍላ የወጣትነት እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች የግብረ ስጋ ግንኙነት ቶሎ እንዳይጀምሩ ነገር ግን ከጀመሩ የቤተሰብ እቅድ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ትምህርት እንደሚሰጥ ነው ባለሙያዋ የተናገሩት። እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ያልተፈለገ እርግዝና ሲፈጠር የኢትዮጵያ ህግ በሚፈቅደው መሰረት ደህንነቱ የተጠበቀ የፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት እንዲያገኙ የማማከር አገልግሎት ይሰጣል። “ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ በእራሱ ምንድን ነው? አገልግሎቱ የት ይገኛል? ብዙ ጊዜ ፅንስ ማቋረጥ ሲባል የምናስበው ደህንነቱ ያልተጠበቀ እና ሴቶችን ለአካል ጉዳት ብሎም ህይወት እስከማሳጣት እንደሚያደርስ መሆኑን ነው” ብለዋል ባለሙያዋ። ስለሆነም የተሳሳተ አመለካከትን በመቅረፍ በጤና ተቋማት የሚሰጥ ደህንነቱ የተጠበቀ የፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት መኖሩን የማሳወቅ ስራ እንደሚሰሩ ነው ዶ/ር ልዕልና የተናገሩት። ይህ የማሳወቅ ስራ የሚሰራው በማህበራዊ ድረገፆች እና በተለያዩ የመገናኛ ብዙሀን አማካኝነት ነው። ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት ማለት በጤና ተቋም ውስጥ፣ አቅም እና ክህሎት ባለው የህክምና ባለሙያ የሚሰጥ ነው። እንዲሁም በኢትዮጵያ ፅንስ ማቋረጥ ተብሎ የሚጠራው እስከ 28ሳምንት ላሉ እርግዝናዎች ነው። ደህንነቱ ያልተጠበቀ ፅንስ ማቋረጥ የሚባለው ደግሞ በጤና ተቋም ያልሆነ፣ ንፅህናው ያልተሟላ፣ ደህንነቱ ባልተረጋገጠ አካባቢ እና አገልግሎቱን ለመስጠት ክህሎት እንዲሁም አቅም በሌላቸው ሰዎች ሲፈፀም ነው።
የፅንስ እና የማህፀን ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ምስክር ገበየው በኢትዮጵያ ህግ መሰረት በህክምና ተቋማት ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት መሰጠቱ ያለውን ጠቀሜታ አስታውሰው ህጉ ቢሻሻል ደግሞ ይበለጥ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ለዚህም እንደምሳሌ የጠቀሱት አንዲት እናት 8 ልጆች ወልዳ ያልታሰበ እርግዝና(9ኛ) ልጅ ቢያጋጥማት እና ፅንሱን ወልዶ ለማሳደግ አቅም ባይኖራት፤ ወይም አንዲት የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪ ያልተፈለገ እርግዝና ቢያጋጥማት እና ለትምህርቷ ችግር ከሆነባት አማራጭ ሊኖራት የገባል የሚል ነው። እርግዝናን አስቀድሞ መከላከል እንዳለ ሆኖ ሴቶችን ከህመም፣ አካል ጉዳት እና ሞት ለመታደግ ህጉ ተሻሽሎ ደህንነቱ የተጠበቀ ጽንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚያገኙበትን ማዕቀፍ ቢዘጋጅ የሚል መልዕክት ዶ/ር ምስክር ገበየሁ አስረላልፈዋል። አከለውም ደህንነቱ የተጠበቀ ፅንስ የማቋረጥ አገልግሎት የሚሰጥ የህክምና ባለሙያ የማህበረሰቡ አካል የሆነ፣ ከባህል እና ከእምነት ያላፈነገጠ እንዲሁም ጎጂ የሆነ ተልዕኮ የሌለው መሆኑን ህብረተሰቡ እንዲረዳ በማለት የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።


Read 513 times