Saturday, 13 May 2023 21:09

ሙዚቃ የዋጠው ፖለቲካ - አሊ ቢራ!

Written by 
Rate this item
(2 votes)

   ንጉሳዊው ሥርዓት ከዙፋኑ ላይ አልወረደም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካም ለትጥቅ ካልሆነ ለፓርቲ ትግል አልታደለም፡፡ በ1953 የመፈንቀለ መንግስት ሙከራ የተደረገባቸው ቀዳሚው ኃይለስላሴ ያንን ክፉ ቀን አስታውሰው አንፃራዊ ነፃነትን ይሰጣሉ ተብሎ ቢጠበቅም የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ ንጉሳዊ አስተዳደሩ ፍፁም አምባገነናዊ እየሆነ ሔደ፡፡ ሜጫና ቱለማ የመረዳጃ ማኀበርን የመሰረቱት የኦሮሞ መብት ተቆርቋሪዎችም መጨረሻቸው የሚያምር አልነበረም፡፡ ብልጭ ያለው ትግል ለአፍታ አሸለበ፡፡
ይሁንና በእዚያው አላንቀላፋም፡፡ በ1960 (እ.ኤ.አ 1967) የብሔሮች ጭቆና ያገባናል ያሉ ወጣቶች የህቡዕ አደረጃጀትን ፈጥረው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ነፃ አውጭ ግንባርን መሰረቱ፡፡ በ”ሶርያ”ና በየመን ወታደራዊ ስልጠናን ወስደው ለማይቀረው ትግል የተዘጋጁት የምስጢራዊ ቡድኑ አባላት አዲስ አበባ ውስጥ መዋቅራቸውን ለመዘርጋትም እንቅስቃሴ ጀመሩ፡፡ “ሶርያ” የከረሙት የድሬዳዋ ተወላጆቹ መኸዲ መሐመድ እና ሙሣ ቡሽትም ተልእኳቸውን መሬት ለማውረድ አብሯቸው የሚኖረውን ሰው የሕቡእ አደረጃጀቱ አባል አደረጉ፡፡
አሊ መሀመድ ሙሣ ከሁለቱ ወጣቶች መረጃዎችን እየተቀበለ ለሌሎች ማድረስና ማደራጀት ላይ መሳተፉን ቀጠለ፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ እያለም ነበር ድብቋ አሜሪካ ግቢ አካባቢ የሚኖርባት ቤት ድንገት የተንኳኳችው፡፡ በሩን ከፈተው፡፡ አንድ ሰው መኸዲ መሐመድን እንደሚፈልግ ነገረው፡፡ አብሮት የሚኖረውን ሰው ለመጥራት አላንገራገረም፡፡
መኸዲን ከፊቱ ያለውን ሰው አቤት አለው፡፡ 200 ብር ተልኮልህ እርሱን ለመስጠት ነበር ብሎ መልዕክተኛው እጁን ወደ ኋላ ኪሱ ላከ፡፡ የመዘዘው ግን የብር ኖቶችን አልነበረም፡፡ ሽጉጥ አውጥቶ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን መንግስት እንደሚያውቅ ተናግሮ፣ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዲሔዱ አዘዛቸው፡፡ አሊ መሀመድ ሙሳ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የደህንነት ሰዎች እጅ መውደቁን ሲረዳ ማታ የምለብሰው ነገር ብቻ ልያዝ ብሎ ወደ ቤቱ ተመልሶ ገባ፡፡ ሳያመነታ በመስኮት አንድ ፎቅ ወደ ታች ዘሎ አመለጠ፡፡
አሊ መሃመድ ሙሳ የመድረክ ስሙን የአዘቦት መጠሪያው ያደረገ ድምፃዊ ነው፡፡ ግን ይኼም ታሪክ ከፖለቲካ አላመለጠም፡፡ በ14 ዓመት እድሜው የ”አፍራን ቀሎ” የሙዚቃ ቡድን አካል ከሆነው “ሂሪያ ጃለላ” የታዳጊዎች ስብስብ ጋር የመጀመሪያ ዜማው “ቢራ ዳ በርሄን” ሲጫወት “ፀሀይም አበራች አበቦቹም ፈኩ፤ አቤቱ አምላኬ እኔ ምን በደልኩ” ሲል አንጎራጉሯል፡፡ ታዳሚው በትንሹ ልጅ አጨዋወት ተማርኮ የላቀ አድናቆቱን ለገሰው፡፡ የመጀመሪያ ስራውም የአባቱን ስም አስረሳች፡፡ አሊ መሀመድ መባሉ ተረስቶ አሊ ቢራ በሚለው ናኘ፡፡ አሊ ትውልዱ ድሬዳዋ ነው፡፡ የአባቱ ስም መሀመድ ሙሳ ሲሆን የእናቱ ስም ደግሞ ፋጡማ አሊ ይባላል፡፡ አሊ፤ አሊ የተባለው አያቱን (የእናቱን አባት) ለማስታወስ ነው፡፡
ይሁንና የወይዘሮ ፋጡማን አባት ስም መጠሪያው ያደረገው አሊ ከእናቱ ስምን እንጅ ፍቅርን አልወረሰም፡፡ ገና በሕፃንነት እድሜው ወላጆቹ ፍች በመፈፀማቸው አባቱ ጋር ቀረ፡፡ የመሀመድ ሙሳ ገቢ አነስተኛ መሆን ደግሞ  ከአባቱም ነጠለው፡፡ አቶ መሀመድ ለአጎታቸው የትዳር አጋር ወይዘቶ ሜይሮ አሊ አደራ ሰጡ፡፡ ሜይሮ ከአቶ መሀመድ ቢሻሉ እንጂ የእሳቸውም የገቢ ምንጭ እንጀራ መሸጥ ነበር፡፡ እናም ታዳጊው አሊ እንጀራ የመሸጥ ኃላፊነት በለጋ እድሜው ወደቀበት፡፡ የአሊ ለስላሳ የህይወት ዜማ ጅማሮው ያኔ ነው፡፡”አለ ትኩስ እንጀራ አለ” እያለ የሚሸጥበት መንገድ ለዛ ያለው ነበረ፡፡ ከሰፊዋ ዓለም ያገኛት ትንሿ ቀዳሚ የሙዚቃ መድረክ እሷ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ዜማና ማንጎራጎር ለመደባት፡፡
አቶ መሀመድ ለራሳቸው የሚሆን ቁራሽ ቢያጡም ለልጃቸው ግን የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ መፍጨርጨራቸው አልቀረም፡፡ በመሆኑም የእስልምና ትምህርትን እንዲከታተል አስመዘገቡት፡፡ ቁርዓን ሊቀራ ከዕኩዮቹ ጋር ዋለ፡፡ የአቶ መሀመድ ዓረብኛ መቻል ደግሞ ቋንቋውን አቀለለለት፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላም ተመረቀ፡፡ አሊን በሃይማኖታዊ አገልግሎት የጠበቁት አልታጡም፡፡ ልጅነቱን እየተሰናበተ የነበረው ታዳጊ ግን ለራሱ መሀንዲስ ሆኖ አቅጣጫውን ቀየሰ፡፡
ጓደኞቹ ወደ ነገሩት “አፍራን ቀሎ” የሙዚቃ ቡድን ሄዶም ተመዘገበ፡፡ አባልነቱ አንጋፋዎቹ የሙዚቃ ቡድኑ አባላት በደረሱለት ሶስት ዜማዎች ታጅቦ ከህዝብ ፊት አቆመው፡፡ “ቢራ ዳ በርሔ” በድሬዎች መንደር ተወዳጅ ሆነች፡፡ አላቆመምም፡፡ የተለያዩ የዓረብኛ፣ ሱዳንኛ እንግሊዝኛ ዜማዎችን እየተዋሰ የሚሰራቸው የኦሮምኛ ሙዚቃዎች ከዕድሜው በላይ የእውቅና ከፍታ ላይ ሰቀሉት፡፡ ይሁንና የድሬዳዋና “አፍራን ቀሎ”ን ፍቅር ፖለቲካ መረዘው፡፡ እነዛ አሊን የወደዱ የሙዚቃ አፍቃሪያንም ትንሹን ልጅ ከዓይናቸው አጡት፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ስደትን መርጦ ወደ ጂቡቲ ጉዞ መጀመሩ ነበር፡፡
ይሁንና ጂቡቲ የነበሩ ወታደሮች ሕገ-ወጥ ነው ብለው ወደ እስር ቤት ወረወሩት፡፡
 የአምስት ወራት እንግልቱን ሲጨርስ አማራጭ አልነበረውም፤ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡
የትውልድ መንደሩ ግን የጠፋባትን ልጅ በደስታ አልተቀበለችውም፡፡ የንጉሱ የደህንነት ሰዎች አሊና ጓደኞቹን በፖለቲካ ክስ ወደ ማረሚያ ላኳቸው፡፡ በትንሹ ልብ ውስጥ የበቀለው የፖለቲካ ተሳትፎ ነፍስ የዘራው አሳሪዎቹ ወደ ጠቅላይ ግዛቱ መቀመጫ ሐረር በ1957 ካዛወሩት በኋላ ነበር፡፡ በነፍስ ማጥፋት ወንጀል ተጠርጥሮ የታሰረ አንድ ወጣት በፖሊሶች ይህ ቀረሽ የማይባል ግፍ ሲፈጸምበት ያስተውላል፡፡
በአሊ ገለጻ ተጠርጣሪው ወንጀሉን አለመፈጸሙ እሙን ቢሆንም፣ ፖሊሶች ግን የጭካኔ በትራቸውን ለአፍታ ሊያስቀምጡ አልወደዱም፡፡
በመጨረሻም ስቃዩ የከበደው ሰው ያላደረገውን ወንጀል አመነላቸው፡፡ አላመነቱም፡፡ በፍርድ ቤት አስወስነው በስቅላት ገደሉት፡፡ አሊ ከትንሿ የእሥር ክፍሉ ሆኖ ያን ሰው ሲያጣጥር አይቶታል፡፡ ኋላም ላይመለስ ሲያሸልብ እንደዛው፡፡ አሊ ቢራ በልጆቿ ላይ የምትጨክነው ኢትዮጵያ ትቅርብኝ ያልኩት ያኔ ነበር ይላል፡፡ የድሬዳዋው መልከ መልካም ወደ አዲስ አበባ ያቀናው ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላ በሰኔ ወር 1958 ነው፡፡
ብዙ አልቆየም፡፡ በአንድ አጋጣሚ ሲያንጎራጉር የተመለከቱት የክብር ዘበኛው ኮለኔል ጣሒር ኤልተሬ ወደ ክብር ዘበኛ ሙዚቃ ክፍል እንዲቀላቀል እድሉን አመቻቹለት፡፡ በ1959 አሊ መሀመድ ሙሳ በአገሪቱ ትልቅ የሚባለው የሙዚቃ ክፍል አባል ሆነ፡፡ ስራዎቹ አድናቆት ማግኘታቸው የትናንት አምሮቱን አልረታውም፡፡ በዚህ ምክንያትም በኦሮሞ የትግል ታሪክ ውስጥ ከግንባር ቀደሞቹ ተርታ በሚመደበው የሜጫና ቱለማ መረዳጃ ማህበር ውስጥ በሙዚቃው ድጋፍ ማድረግ ጀመረ፡፡ ለድሬዳዋው ፈናን ወግ አጥባቂው ክቡር ዘበኛ የሚመቸው አልነበረም፡፡ የሚያገኘው ገቢ ማነስ ተጨምሮበት ሙዚቃን አቁሞ አዋሽ ሌላ ስራ ጀመረ። ሙዚቃን ከአንገት በላይ ቢያኮርፋትም ልቡ ግን እሷው ጋር ነበር፡፡
“አዋሽ ነማ ሾኪሶ” የተሰኘ ስራውን ከህዝቡ ትውፊት ተውሶ ውብ አድርጎ የተጫወተው ከዛ መልስ ነው፡፡ ነፃነትን ናፋቂው አሊ፤ ከዚህ በኋላ ፊቱን ያዞረው ወደ ምሽት ክበቦች ነበር፡፡ በአብዮቱ ዋዜማ ሰሞን ጠመንጃ ያዥ አካባቢ በሚገኘው “ዋዜማ ክለብ” ሥራውን አሀዱ አለ፡፡ የጭቆና ምንጭ ነው ባለው ስርዓት ላይም በድፍረት ማዜሙን ቀጠለ፡፡ አሊ የናፈቀው አብዮት ዘገየ አንጂ አልቀረም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ዙፋን ተገርስሶ ወታደራዊው የደርግ ሥርዓት አራት ኪሉ ደረሰ፡፡ ንጉሳዊውን መንግስት አምርሮ የሚጠላው የድሬው ፈናንም፣ ባላባቱን የሚነቅፍ “አባ ለፋ” የሚል ሙዚቃውን ይዞ ብቅ አለ፡፡
አሊ ለውጥን ቢናፍቅም በመጣው ለውጥ ለመሰላቸት ግን አፍታ አልወሰደበትም፡፡ በመሆኑም በተለያየ መንገድ ለኦሮሞ ማንነት ሲታገሉ የነበሩና ዘግየት ብለው ኦነግን ከመሰረቱ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በቅርበት መስራት መረጠ፡፡ እነዚህ ወገኖች ድሬዳዋ ያሉ የሙዚቃ ሰዎችን አምጥተህ ስልጠና ስጥልን ባሉት መሰረትም ስልጠና ሰጠ፡፡
 አሊ መሀመድ ሙሳ ወዲህ የኦሮሞን ማንነትና ባህል ለማስተዋወቅ እየታገለ ወዲያ በምሽት ቤቶች ስሙ መናኘት ጀመረ፡፡“ዛምቤዚ ክበብ” የተጀመረው ተወዳጅነት፣ ሜክሲኮ አቅራቢያ ባለው “ዲያፍሪክ” ሆቴል ገነነ፡፡ ማሕሙድ አህመድን የመሰሉ ተወዳጅ ድምፃዊ የያዘው በራስ ሆቴል የነበረው አይቤክስ ባንድም ከአሊ ቢራ ጋር መጣመርን መረጠ፡፡ ይህ አብሮነትም “አማሌሌ” የተሰኘ አልበሙን አዋለደ፡፡ አሊ በ1970ዎቹ አጋማሽ የእውቅና ማማ ላይ ቢደርስም የስዊድን ኤምባሲ ሰራተኛ ከነበረችው ባለቤቱ ብርጊታ አስትሮም ጋር ኑሮውን ሊያደላድል ወደ አሜሪካ መጓዙ ግን አልቀረም፡፡
ይህም ቢሆን ከሙዚቃው ሰማይ እንጂ ከኦሮሞ የትግል ጥያቄ አላራቀውም፡፡ ሳዑዲ ዓረቢያ ውስጥ “የኦሮሞ ነፃነት ግንባር” እና “የኦሮሞ እስላማዊ ነፃነት ግንባር” ያላቸውን ልዩነት በውይይት እንዲፈቱና በአንድነት እንዲታገሉ ያልተሳካ ሙከራ አድርጓል፡፡ አሊ በፖለቲካ ቡድኖች ገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅቶች ላይ ከፍ ያለ አስተዋጽኦ ቢኖረውም፣ ይፋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አባልነት ግን ኖሮኝ አያውቅም ይላል፡፡ ይልቁኑስ በውጪ ዓለምም ቢሆን በያዝ ለቀቅ ሙዚቃውን ገፋበት፡፡ እንዲህ ያለው ሕዝባዊ ቅቡልነትን የያዘ ፖለቲካዊ ተሳትፎ ደግሞ በኢህአዴግ መራሹ መንግስት ላይ ጫና መፍጠሩ አልቀረም፡፡
በመሆኑም አሊን ወደ አገሩ መመለስ ትልቅ የፖለቲካ ፕሮጀክት ሆነ፡፡ የወቅቱ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ሳዶ የመሩት ተልዕኮ ከመግባባት ተደርሶበትም የሁለት አስርታት ስደተኛው ወደ አገሩ ተመለሰ፡፡ የአሊ መሀመድ ሙሳ ወደ አገር ቤት መመለስ በበርካታ ደጋፊዎቹ ነቀፌታን ቢያስከትልም፣ እርሱ ግን የመመለሱ አንዱ ምክንያት “በ1997 በነበረው የምርጫ ቅስቀሳ የአንድነት ኃይል የሚባሉት “ጨፍላቂ” አስተሳሰብን የያዙ ወገኖች በፖለቲካው ሜዳ ጎልቶ መታየት የፈጠረው ስጋት ነበር” ይላል፡፡
የድሬዳዋው ፈናን ወደ አገሩ ከተመለሰ በኋላ ከጊዜው የትዳር አጋሩ ሊሊ ማርክስ ጋር በመሆን የ”ቢራ ፋውንዴሽን”ን በመመስረት በትምህርት ቤቶች አነስተኛ ገቢ ያላቸው ወላጆች ልጆችን ለመርዳት ሰፊ እንቅስቃሴ አድርጓል፡፡ አሊ በረጅሙ የሙዚቃ ዘመኑ እልፍ ጊዜ ሞትን ፊት ለፊት ገጥሟል፡፡
አስቀድሞ በጉበት ካንሰር ተይዞ በተደረገለት ቀዶ ጥገና በተአምር ከሞት አምልጧል፡፡ በሌላ ወቅትም የጭንቅላት ዕጢ ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ዳግም ሞትን ረቷል፡፡ አሊ መሀመድ ሙሳ ለሶስተኛ ጊዜ የወገብ ቀዶ ጥገና ሲደረግለትም የከፋ የጤና ችግር ገጥሞት ነበር፡፡ ይሁንና ሞትን አሳፍሮ በበርካታ መድረኮች ላይ እየተገኘ ለህዝቡ የደስታ ርችት፤ ላመነበትም የትግል ቃፊር ሆኖ ዘለቀ፡፡
ለአሊ ቢራ ሙዚቃ ምሽጉ ናት፡፡ ነፃነትና እኩልነትን አሻግሮ የሚመለከትባት፡፡ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ሁሌም የማናጣት የድብቅ ወዳጁም ለዚህ ምስክር ናት፡፡
አንዴ በውብ ሴት፣ ሌላ ጊዜ በጨረቃ፣ ሲያሻው በፀሀይ የሚመስላት፡፡ “ሲን በርባዳ ሆጉ”፣”ኦሮሞ ቦሩ”፣”ያ ሁንዴ አያና” እና “ገመቹ” ውስጥ ያች ውብ ተዚሞላታል፡፡ በአሊ ቢራ ሙዚቃዎች ላይ ትንታኔ የፃፈው ዘመድኩን ምስጋናው፤ በአሊ ሙዚቃዎች ውስጥ ያለችው ሴት ቅኔ ፍች “ኦነግ” ነው ይላል፡፡ የመሀመድ ሙሳ ልጅ በይፋ አይንገረን እንጂ ስለ ኦነግ አብዝቶ በስስት ተጫውቷል፡ በአደባባይ ስለ ኦሮሞ ህዝብ ያለውን አስተሳሰብ ተናግሯል፡፡
“አኒስ ቢያን ቀባ” (የአገር ፍቅር) እና “አዴ ኦሮሚያ” ( እምዬ ኦሮሚያ) ብሎ ኦሮሞን አምሳለ አገር አድርጎ አዚሟል፡፡
ዕውቁ የታሪክ ምሁር ፕሮፌሰር መሀመድ ሀሰን፤ አሊን ድል አድራጊ የነፃነት አርበኛ ያደርጉታል፡፡
 ምክንያታቸውም ከአምሳ አመት በፊት ኦሮምኛን በማዜሙ ለእስርና ስደት የተዳረገው አሊ፤ ከ50 ዓመት በኋላ በአገሪቱ መሪዎች ፊት የሚሸለም ስመ ገናና ወደ ከመሆን መሸጋገሩ ነው፡፡ ገለፃቸው የሙዚቃና ፖለቲካን ድንበር ያፈርሳል፡፡ አሊንም እንደ ሙዚቀኛ ብቻ እንዳንመለከተው ያስገድዳል፡፡
(ከይነገር ጌታቸው (ማዕረግ) “ጠመንጃና ሙዚቃ” መጽሐፍ የተወሰደ)


Read 1082 times