Saturday, 06 May 2023 17:59

የኢትዮጵያ የሚዲያ ነፃነት አደጋ ላይ መውደቁ ተገለፀ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

“ኢትዮጵያ በፕሬስ ነፃነት አሽቆልቁላለች”

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ ባለፈው ረቡዕ በተከበረው የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ስነ-ስርዓት ላይ ባደረጉት ንግግር፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ በሚዲያ ባለሙያዎች ላይ እየደረሰ ያለው እንግልትና እስር አሳሳቢ ሆኗል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነት አደጋ ውስጥ መውደቁን የጠቆሙት ዶ/ር ዳንኤል፤ በዚህ ወቅት ቢያንስ 8 ጋዜጠኞች እስር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ብዙኃን መገናኛ ም/ቤት ሊቀመንበር አቶ አማረ አረጋዊ በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት መሰረት እንዲኖረው፣ መንግሥት፣ ህገ-መንግስታዊ ግዴታውን ሊወጣ እንደሚገባ አሳስበዋል።የሚዲያ ነፃነት ለሰብአዊ መብቶች መከበር መሰረት መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ ከአራት ዓመት በፊት የታየው የነፃነት ዝንባሌ በሂደት አደገኛ ወደሆነ ሁኔታ መለወጡን አመልክተዋ፡፡ “በወቅቱ የታየውን የሚዲያ ነፃነት ዝንባሌ ተከትሎ የተሻሻለው የሚዲያ አዋጅ ትልቅ ለውጥ የታየበት ቢሆንም በርካታ ክፍተቶች ታይተዋል” ብለዋል- ኮሚሽነሩ።የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀን ባለፈው ረቡዕ ሚያዚያ 25 ቀን 2015 ዓ.ም በመላው ዓለ ም የተከበረ ሲሆን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ም/ቤትም ከዩኔስኮ ጋር በመተባበር በኢንተር ሌግዠሪ ሆቴል ማክበሩ ታውቋል።
በኢትዮጵያ ባለፈው የፈረንጆች ዓመት 2022 የሚዲያ ነፃነት ከፍተኛ ጥቃት ደርሶበታል ያለው አምነስቲ ኢንተርናሽናል፤ በመላው አገሪቱ ቢያንስ 29 ጋዜጠኞች ለእስር ተዳርገው እንደነበር አስታውሷል።
ባለፈው ረቡዕ የዓለም የፕሬስ ነፃነት ቀንን ለማስታወስ ከደቡባዊ አፍሪካ ሚዲያ ተቋም ጋር መግለጫ የወጣው አነስቲ፤ በዚያው ዓመት የትግራይ ባለስልጣናት አምስት ጋዜጠኞችን “ከጠላት ጋር በመተባበር” በሚል መክሰሳቸውን አንስቷል።
በመላው የምስራቅና ደቡባዊ አፍሪካ አገራት የሚገኙ ባለስልጣናት፣ የሙስና እና የሰብአዊ መብት ጥሰት ዘገባዎችን ለማፈን ሲሉ በጋዜጠኞችና በፕሬስ ነፃነት ላይ የሚፈጽሟቸውን ጥቃቶች ተባብሰዋል ብሏል- መግለጫው።ይህ በእንዲህ እንዳለ “ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደር” በቅርቡ ባወጣው የፕሬስ ነጻነት መጠቆሚያ ኢንዴክስ መሰረት፤ በኢትዮ የፕሬስ ነፃነት ሁኔታ ማሽቆልቆሉ ነው የተመለከተው።ኢትዮጵያ በ2022 ዓ.ም በፕሬስ ነፃነት ኢንዴክስ፣ ከ180 አገራት 114ኛ ደረጃ ላይ የነበረች ሲሆን በ2023 ዓ.ም 130ኛ ደረጃ ላይ ነው የተቀመጠችው- ከ180 አገራት።

Read 1285 times