Saturday, 06 May 2023 17:34

ኢሰመኮ አራተኛውን ዙር ግልጽ የምርመራ መድረክ በአዳማ ከተማ አካሄደ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በባሕር ዳር፣ በጅግጅጋ እና በሃዋሳ ከተሞች ያካሄደውን ግልጽ የምርመራ መድረክ (National Inquiry/Public Inquiry) ተከትሎ፣ በአዳማ ከተማ ከሚያዝያ 17 እስከ 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ አራተኛውን ግልጽ የምርመራ መድረክ ማካሄዱን አስታውቋል፡፡
በመድረኩም በተለይ የዘፈቀደ እስርን፣ የተራዘመ የቅድመ ክስ እስርና በእስር ወቅት ተከስተዋል ስለተባሉ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጎጂዎችና ምስክሮች ያቀረቧቸውን አቤቱታዎች እንዲሁም ጉዳዩ በሚመለከታቸው አካላት የተሰጡ ምላሾችን ማዳመጡ ተጠቁሟል፡፡
 ለአብነት ተመርጠው ከቀረቡት 18 አቤቱታዎች መካከል:- ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ መያዝና መደበኛ ባልሆኑና በማይታወቁ ቦታዎች በእስር ማቆየት፣ በሕግ በተቀመጠው ጊዜ መሠረት የታሰረን ሰው ፍርድ ቤት ያለማቅረብ፣ የፍርድ ቤት የዋስትና መብት ትእዛዝ አለማክበር ይገኙበታል ተብሏል።
በተጨማሪም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን፣ በእስር ወቅት በቤተሰብ የመጎብኘት መብትን፣ በቂ ምግብ፣ ውሃ፣ መጸዳጃና ሕክምና የማግኘት መብትን አለማክበርና ጭካኔ የተሞላበትና የማሰቃየት ድርጊት መፈጸም በቀረቡት አቤቱታዎች በተደጋጋሚ ከተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መካከል እንደሚገኙበት ኮሚሽኑ አመልክቷል፡
የግልጽ ምርመራ መድረክ፤ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ደርሶብናል የሚሉ ሰዎች፣ ምስክሮች፣ ሌሎች ባለድርሻ አካላት እንዲሁም የሚመለከታቸው የመንግሥት ተወካዮች በአንድ መድረክ በተገኙበት በሕዝብ ፊት የሚከናወን የምርመራ ስልት መሆኑን ኢሰመኮ ጠቁሟል፡፡
“አቤቱታ አቅራቢዎች ደርሶብናል የሚሏቸውን የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በግልጽ መድረክ ምስክርነት መስጠትና ማስረጃ ማቅረብ የሚችሉ ሲሆን፤ የሚሰጡት ቃል ሚስጥራዊ ባሕርይ ወይም የደኅንነት ሥጋት ያለባቸው ሰዎች ደግሞ በልዩ ሁኔታ በሚስጥር ቃላቸውን የሚሰጡበትን ዕድልንም ያካትታል፡፡” ብሏል፡፡
 ለግልጽ ምርመራው በኦሮሚያ ክልል ነጻነታቸውን ከሕግ አግባብ ውጪ እና በዘፈቀደ የተነፈጉ ሰዎች መብቶች ላይ ያተኮረ ጥናትና ምርምር ወይም የምርመራና ክትትል ግኝቶች ያሏቸው አካላት ይህንኑ እንዲያቀርቡ ኮሚሽኑ ያደረገውን ጥሪ ተከትሎ፣ መቀመጫውን በውጭ ሀገር ያደረገ Oromo Legacy Leadership & Advocacy Association/OLLAA የተባለ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅትን ጨምሮ ሌሎችም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የየበኩላቸውን መረጃዎችና ትንተናዎች በጽሑፍ ለኮሚሽኑ ማስገባታቸው የታወቀ ሲሆን፤ በግልጽ ምርመራ መድረኩም ላይ በበይነ መረብ ቴክኖሎጂ በመታገዝ ዋና ዋና ሐሳቦቻቸውን አቅርበዋል ተብሏል፡፡
ሌሎች የሲቪል ማኅበራት ተወካዮችም ከሕግ ውጪ የሆኑና የዘፈቀደ እስራትን በተመለከተ አጣርተን ደርሰንበታል ያሉትን መረጃዎች በመድረኩ አቅርበው የመንግሥት አካላት ምክረ ሐሳቦቻቸውን በመቀበል ተግባር ላይ እንዲያውሉና ለሰብአዊ መብቶች መከበር አብረዋቸው እንዲሠሩ ጥሪ ማቅረባቸው ተመልክቷል፡፡
 “በኦሮሚያ ክልልና በተለያዩ ዞኖች በየደረጃው ያሉ የፍርድ ቤት፣ የፍትሕ ቢሮ፣ የፖሊስ ኮሚሽንና የሰላምና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ለቀረቡት አቤቱታዎችና ተፈጽመዋል ለተባሉት የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፤ በተጨማሪም የፍትሕና  የጸጥታ ተቋማቱ ያሉባቸውን ተግዳሮቶች እንዲሁም ለመብት ጥሰቶቹ መነሻ ምክንያት የሆኑ የክልሉን ነባራዊ ሁኔታም አስረድተዋል::” ብሏል ኮሚሽኑ በመግለጫው፡፡በአዳማ ከተማ የተካሄደውን ግልጽ ምርመራ መድረክ የኢሰመኮ የሲቪል፣ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል፣ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ እና የሰብአዊ መብቶች ክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል የሪጅን ዳይሬክተር ኢማድ አብዱልፈታህ መርተውታል፡፡
የዝግጅቱን መጠናቀቅ ተከትሎ የመርማሪ ኮሚሽነሮች ሰብሳቢ ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጅብሪል ባደረጉት ንግግር፤ “በግልጽ የምርመራ መድረኩ ተጎጂዎች፣ ባለግዴታዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች ዙሪያ በግልጽ መነጋገር መቻላቸው እንዲሁም ለወደፊት ሊወሰዱ ስለሚገባቸው እርምጃዎች በሁሉም አካላት በኩል ለመደጋገፍ የመፍትሔ ሐሳቦች መቅረባቸው የሚያበረታታ ነው፡፡” ብለዋል፡፡


Read 1165 times