Saturday, 29 April 2023 18:12

“ማርደን” ማር እና ሰም ለአገር ውስጥ ገበያ መቅረብ ጀመረ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

 “ማር ሲሰፍሩ፤ማር ይናገሩ”

       ከ2010  ጀምሮ ኦርጋኒክ ማርና ሰም በከፍተኛ የጥራት ደረጃ  ለአሜሪካ፣ አውሮፓና ጃፓን ገበያዎች ሲያቀርብ የቆየው  ግሪን ፌስ ትሬዲንግ ኃ.የተ.ግ.ማህበር፤አሁን ደግሞ ኦርጋኒክ ማርና ሰም ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
ድርጅቱ ሀሙስ ሚያዚያ 19 ቀን 2015 ዓ.ም ከ8፡30 ጀምሮ በኢሊሊ ሆቴል ባዘጋጀው የማብሰሪያ ሥነስርዓት ላይ “ማርደን” በሚል ሥያሜ ኦርጋኒክ ማርና ሰም፣ በፋብሪካው እያቀነባበረ፣ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን በይፋ አስተዋውቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከዓለም  የመጀመሪያዎቹ አሥር የማር አምራቾች አንዷ ስትሆን፤ከአፍሪካ ቀዳሚዊ የማር አምራች እንደሆነች  ይታወቃል፡፡ ሆኖም የአምራችነቷን ያህል ማርን የመመገብ ባህል በአገሪቱ  አላደገም ተብሏል፡፡
በአገሪቱ ማር የመመገብ ባህል ያልዳበረበት አንዱ ምክንያት ተብሎ የተጠቀሰው፣ በከተማዋ ለሽያጭ የሚዘዋወረው ማር፣ ባዕድ ነገሮች ያልተቀላቀሉበት ንጹህ መሆኑን ማረጋገጥ ከባድ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡
በመርሃግብሩ ላይ የአገር ውስጥ የማር አቅርቦት ጥራትን በተመለከተ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ተረፈ ዳምጠውም፣ በጥናታቸው ያረጋገጡት  ይህንኑ ነው፡፡
ይህንን ችግር በሚገባ የተገነዘበው ግሪን ፌስ ትሬዲንግ፤በአውሮፓ ስታንዳርድተመርምሮ ተቀባይነት ያገኘውን ንጹህ ኦርጋኒክ ማር በማምረት፣ የህብረተሰቡን ፍላጎት ለማሟላት፣ ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመሩ  ተነግሯል፡፡
 የግሪን ፌስ ትሬዲንግ ኃ.የተ.ግ.ማህበር መሥራችና ባለቤት አቶ ጆኒ ግርማ፤ በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ላይ ድርጅታቸው፣ “ማርደን” በሚል ስያሜ፣ ኦርጋኒክ ማርና ሰም ለአገር ውስጥ ገበያ ማቅረብ መጀመሩን አብስረዋል፡፡
***
በነገራችን ላይ የመድረኩ አጋፋሪ፣ በየመድረኩ ከሚያጋጥሙንና የሚናገሩበትን ርዕሰ ጉዳይ ከማያውቁ ወይም ተዘጋጅተው ከማይመጡ ብዙዎች በእጅጉ ይለያል፡፡   ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ፣ በቅጡ ተዘጋጅቶና ተለማምዶ (Rehearse አድርጎ) መምጣቱን አለመመስከርና አለማድነቅ ንፉግነት ነው፡፡ የመድረክ አጋፋሪነቱን ማር ማር በሚሉ ተረቶችና ቀልዶች አሽሞንሙኑ ነው ያቀረበው፡፡ ሳቅ ብርቅ በሆነበት በዚህ ዘመን፤ ታዳሚውን ሁለት ሦስቴ ማሳቅ ድንቅ ችሎታ ይጠይቃል፡፡



Read 1650 times