Monday, 24 April 2023 18:41

ከተማ አቀፍ የህክምና መሣሪያዎችና ዕቃዎች ጥገና ዘመቻ በይፋ ተጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ፣ በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅና በቶም የህክምና መሳሪያዎች ተከላና ጥገና ማዕከል በጋራ የተዘጋጀው ከተማ አቀፍ የህክምና መሳሪያዎችና ዕቃዎች ጥገና ዘመቻ፣ “የህክምና መሳሪያዎችና ዕቃዎች ብክነትን በጋራ እንከላከል!” በሚል መሪ ቃል፣ ዛሬ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም በተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በይፋ ተከፍቷል።

በፕሮግራሙ ላይ የአዲስ አበባ የምግብ የመድሀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ታደሰ አጥላባቸው ፣የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ወንድሙ፣ የተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ዋና ዲን አቶ ግሩም ግርማ ፣ የቶም የህክምና መሳሪያዎች ተከላና ጥገና ማዕከል ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቶማስ ገ/መስቀል እና ጥሪ የተደረገላቸው የተለያዩ እንግዶች ተገኝተዋል።

ፕሮግራሙን በንግግር የከፈቱት የኮሌጁ ዲን አቶ ግሩም ግርማ፤ ዘመቻው መከፈቱ  ለሀገር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የተናገሩ ሲሆን ፤ የዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ታደሰ አጥላባቸው በበኩላቸው፣ ይህ ዘመቻ በተለያዩ ምክንያቶች የጥገና አገልግሎት ሳያገኙ ቁጭ ላሉ የህክምና መሳሪያዎች ትልቅ ዕድል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ታደሰ አክለውም፤ በዚህ ዘመቻ ሁሉም የግልና የመንግስት ጤና ተቋማት ያላቸውን አገልግሎት የማይሰጡ ወይም የተበላሹ የህክምና መሳሪያዎች  ወደ ዘመቻው በማምጣትና እንዲጠገኑ በማድረግ የዘመቻው አካል ከመሆን ባለፈ ያለአግባብ የሚባክኑ ሀብቶችን እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።

 በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ወንድሙ ደግሞ  ይህ ዘመቻ ለህክምና አገልግሎት ጥራት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ጠቁመው፣በከተማ አስተዳደሩ ስር የሚገኙ ሆስፒታሎችና በአስራ አንዱም ክፍለ ከተሞች ስር የሚገኙ ጤና ጣቢያቸው እንደሚሳተፉም ገልፀዋል።

ዘመቻው በአዲስ አበባ ተግባረ ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚካሄድ ሲሆን ከሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም  እስከ ሰኔ 16 ቀን 2015 ዓ.ም ለሁለት ወራት የሚቆይ መሆኑ  በፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል።

Read 1449 times