Saturday, 15 April 2023 21:56

መሰናክሎች፤ መልካም ዕድሎች ናቸው!

Written by 
Rate this item
(0 votes)

በጥንት ጊዜ ነው፡፡ አንድ ንጉስ  ቋጥኝ ድንጋይ ሆን ብሎ  ዋናው መንገድ ላይ ያስቀምጣል፤መንገዱን ዘግቶ ማለት ነው፡፡ ከዚያም ተደብቆ በዚያ ከሚያልፉ ሰዎች መካከል  ያንን ቋጥኝ  ከመንገዱ ላይ ማን እንደሚያነሳው  በጉጉት መመልከት ይጀምራል፡፡
 መጀመሪያ ላይ  ለንጉሱ ቅርብ የሆኑ ሃብታም ነጋዴዎችና ባለሟሎች መጡ፡፡ ነገር ግን ያ መንገዱን  የዘጋው  ቋጥኝ ድንጋይ ፈጽሞ አላሳሰባቸውም፡፡ ከአነ መኖሩም ትዝ ያላቸው አይመስሉም፡፡ በራሳቸው ወሬ በእጅጉ ተጠምደው ድንጋዩን ታከው  አለፉት፡፡
በዚያ መንገድ ያለፉ በርካታ ሰዎች ግን፤ “ለምን ንጉሱ ይሄን  ቋጥኝ ድንጋይ አያስነሳውም?!” ብለው በእጅጉ  አማረሩ፡፡
አንዳቸውም ግን በግልም ሆነ ተባብረው ያንን ድንጋይ ከጎዳናው ላይ ለማንሳት አልሞከሩም፡፡ አማረው ብቻ ነው የሄዱት፡፡
በመጨረሻ ግን አትክልት  የተሸከመ አንድ ገበሬ መጣ፡፡ መንገድ ዘግቶ የተቀመጠውን  ቋጥኝ ድንጋይ እንደተመለከተም፣ የተሸከመውን አትክልት ከራሱ ላይ አውርዶ መሬት  አስቀመጠና፣ከቋጥኙ ጋር ብቻውን ይታገል ገባ፡፡ ረዥም ጊዜ ወሰደበት፡፡ ከብዙ ልፋትና ድካም በኋላም ተሳካለት፡፡ ድንጋዩን ከመንገዱ  ላይ ገፍቶ ገፍቶ ዳር ላይ ማድረግ ቻለ፡፡
ከዚያም  መሬት ላይ ያስቀመጠውን አትክልት አንስቶ ሊሸከም ሲል፣ ቋጥኙ ድንጋይ ተቀምጦ የነበረበት ቦታ ላይ አንድ ቦርሳ  ተቀምጦ ተመለከተ፡፡ ቦርሳው በብዙ ወርቆች የተሞላ ነበር፡፡ ገበሬው ደነገጠም፤ ተገረመም፡፡  ዙሪያ ገባውን ቃኘና፣ ቦርሳውን ልውሰድ አልውሰድ በሚል ሃሳብ ለአፍታ ተጨነቀ፡፡
ወዲያው ግን የንጉሱ መልዕክት የሰፈረበት  ብጫቂ ወረቀት እዛው ቦርሳው ውስጥ አገኘ፡፡ “ይህን ቦርሳ፤ ቋጥኙን ከመንገድ ላይ   ያነሳ  ሰው ይውሰደው፤ ሽልማቱ ነው” ይላል፤የንጉሱ ማስታወሻ፡፡
ሁሌም በመንገዳችን ላይ  የሚገጥሙን ፈተናዎችና መሰናክሎች፣ ህይወታችንን ለማሻሻል የሚጠቅሙን መልካም ዕድሎችና አጋጣሚዎች  ናቸው፡፡ ሰነፎች በገጠሟቸው ፈተናዎችና መሰናክሎች ሲያማርሩና ሲያለቃቅሱ፤ ጎበዞች ግን  ችግሮችና ፈተናዎችን ወደ መልካም አጋጣሚ በመቀየር ስኬት ይቀዳጁበታል፡፡

Read 938 times