Saturday, 15 April 2023 20:25

‹‹የባላገሩ ምርጥ›› ምርጥ 10 ተወዳዳሪዎች በዕለተ ፋሲካ ይታወቃሉ ተባለ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

በባላገሩ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው ‹‹የባላገሩ ምርጥ›› ተወዳዳሪዎች ወደ ምርጥ 10 የሚያልፉበት ውድድር ነገ በዕለተ ፋሲካ እንደሚካሄድና ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ በቀጥታ ስርጭት ለተመልካች እንደሚቀርብ ተገለፀ፡፡
በውድድሩ ከአንደኛ እስከ አስረኛ የሚወጡ አሸናፊዎች ከ3 ሚሊዮን ብር እስከ 100 ሺ ብር ይሸለማሉ ተብሏል፡፡
የባላገሩ ቴሌቪዥንና ‹‹የባላገሩ ምርጥ›› ባለቤትና አዘጋጅ አርቲስት አብርሃም ወልዴ፣ ከአጋሩ ‹‹ያሆ ኢንተርቴይመንት›› እና ከስፖንሰሩ ጊፍት ሪል እስቴት ሃላፊዎች ጋር በመሆን ባለፈው ረቡዕ በቦናንዛ ሆቴል ውድድሩን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት 27 ተወዳዳሪዎች ካምፕ ውስጥ ገብተው እየሰለጠኑ መሆኑን የገለፀው አርቲስት አብርሃም ወልዴ፤ ከእነዚህ ውስጥ 15ቱ ስራቸውን አቅርበው ምርጥ አስሩ የሚለዩበት ውድድር ነው በነገው እለት  በቀጥታ ሥርጭት የሚከናወነው ብሏል፡፡
የባላገሩ ምርጥ ውድድር መጠናቀቅ ከነበረበት ጊዜ መዘግየቱን የጠቆመው አርቲስት አብርሃም፤ የዘገየበት ምክንያትም የኮቪድ-19 ወረርሽኝና የአገሪቱ አጠቃላይ አለመረጋጋት መሆኑን ገልጿል፡፡
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ባላገሩ ምርጥ አሻሽሎ የመጣው ነገር የአሸናፊዎች የገንዘብ ሽልማት መጠን እንደሆነ የገለፀው አርቲስት አብርሃም፤ በውድድሩ አንደኛ ለሚወጣ 3 ሚሊዮን ብር፣ ሁለተኛ ለሚወጣ 2 ሚሊዮን ብር፣ ሦስተኛ ለሚወጣ ደግሞ 1 ሚሊዮን ብር ሽልማት መዘጋጀቱን አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም፤ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ለሚወጡ ለእያንዳንዳቸው 100 ሺ ብር ሽልማት እንደሚበረከትም አርቲስቱ ተናግሯል።
የገንዘብ ሽልማት አሰጣጡን በተመለከተ በተሰጠው ማብራሪያ፤ አንደኛ ለሚወጣው ከተመደበው የ3 ሚሊዮን ብር ሽልማት፣ ለአሸናፊው በእጁ 1 ሚሊዮን ብር የሚሰጠው ሲሆን፤ 2 ሚሊዮን ብሩ ለሚፈራረመው የአልበም ኮንትራት አጠቃላይ ወጪ ይውላል ተብሏል፡፡ ሁለተኛ ለሚወጣው አሸናፊ ከተመደበው የ2 ሚሊዮን ብር ሽልማት፣ 500 ሺ ብር በእጁ የሚሰጠው ሲሆን፣ 1.5 ሚሊዮን ብሩ ለአልበሙ መስሪያ እንደሚውል ታውቋል፡፡ ሶስተኛ የሚወጣውና 1 ሚሊዮን ብር የሚሸለመው ደግሞ 250 ሺ ብር በእጁ ሲሰጠው፣ ቀሪው 750 ሺ ብር ሦስትና አራት ነጠላ ዜማዎች ይሰራበታል ተብሏል፡፡በውድድሩ ከ1ኛ -10ኛ የሚወጡት አሸናፊዎች በአንድ ላይ የሚሰሩት አንድ የጋራ አልበም እንደሚኖራቸውም በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል።ለአሸናፊዎች ሽልማት በአጠቃላይ 8 ሚሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን አንደኛ ለሚወጣው አሸናፊ የተመደበውን 3 ሚሊዮን ብር ጊፍት ሪል እስቴት ስፖንሰር ማድረጉ ተገልጿል፡፡ ሁለተኛና ሦስተኛ ለሚወጡ አሸናፊዎች ስፖንሰሮች ይፈለጋሉ ያለው አርቲስት አብርሃም ወልዴ፤ ይህንንም ኩባንያዎችና ተቋማት ስፖንሰር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በነገው ዕለት ከሚለዩት ምርጥ 10 ተወዳዳሪዎች ውስጥ ወደ መጨረሻው ዙር የሚያልፉት ስድስቱ እንደሚሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ አሸናፊዎች ከሁለት ወር በኋላ በደማቅ ሥነ ስርዓት ይሸለማሉ ተብሏል፡፡


Read 1478 times