Saturday, 15 April 2023 20:10

የመልካ ጀብዱ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ሊገነባ መሆኑ ተገለፀ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

የመጀመሪያው ዙር የሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ ስምምነት ተፈጽሟል

በድሬዳዋ ከተማ የኖራ፣ የሲሚንቶና የብረት ፋብሪካዎችን ያካተተ የመልካ ጀብዱ ኢንዱስትሪያል ፓርክ በ540 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ሊገነባ መሆኑ ተገለጸ።
ግንባታውን የሚያከናውነው የቻይናው ሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ነው። በ106 ሄክታር መሬት ላይ የሚገነባውን የመልካ ጀብዱ ኢንዱስትሪያል ፓርክ የመጀመሪያ ምዕራፍ ግንባታ ለማስጀመር ናሽናል ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ ከሲኖማ ኢንተርናሽናል ኢንጂነሪንግ ሊሚትድ ጋር ባለፈው ማክሰኞ ሚያዝያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል ስምምነት ተፈራርመዋል።
ናሽናል ዌስት ሆልዲንግ፤ አገር በቀሉ ኢስት አፍሪካ ሆልዲንግና የቻይናው ዌስት ኢንተርናሽናል ሆልዲንግ በጋራ ጥምረት የሚሰሩበት ግዙፍ ኩባንያ ሲሆን በሰሜን ሸዋ ዞን በለሚ ከተማ በርካታ ፋብሪካዎችን የያዘውን እና በ600 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የሚገነባውን የለሚ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታ በታቀደለት ጊዜ እየገነባ እንደሚገኝም ይታወቃል።
የናሽናል ዌስት ሆልዲንግ ኩባንያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብዙአየሁ ታደለ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ አጠቃላይ ግንባታው 540 ሚሊዮን ዶላር የሚፈጅ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሲሚንቶ ፋብሪካ ግንባታ 243 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ይደረግበታል ተብሏል።
የኢንዱስትሪ ፓርኩ ግንባታ ሲጠናቀቅ በዓመት 700 ሺህ ቶን የማምረት አቅም ያለው የብረት ፋብሪካ፣ በቀን 1ሺህ ቶን የማምረት አቅም ያለው የኖራ ፋብሪካ፣ በዓመት 3 ሚ.ቶን የማምረት አቅም ያለው የሲሚንቶ ፋብሪካና ለተገጣጣሚ ቤቶች የሚውል ኮንክሪት ማምረቻ ፋብሪካዎችን የሚያካትት ሲሆን፤ ለ5ሺ ያህል ዜጎችም የሥራ ዕድል ይፈጥራል ተብሏል።የመልካ ጀብዱ ኢንዱስትሪያል ፓርክ ግንባታው ተጠናቅቆ በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር በዓመት ከመቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማስገኘት የሚችል ግዙፍ ፕሮጀክት መሆኑም ተገልጿል።
መልካ ጀብዱ ለዚህ ፕሮጀክት ግንባታ የተመረጠበትን ዋና ምክንያት ሃላፊዎቹ ሲያስረዱም፤ በዚህ የኢንዱስትሪያል ፓርክ ውስጥ በሚገነቡ ፋብሪካዎች የሚመረቱትን ምርቶች ለአጎራባች አገራት ገበያ ለማቅረብ ታቅዶ የተነደፈ እንደመሆኑ መልካ ጀብዱ ለታቀደው የኤክስፖርት ገበያ ለጅቡቲና በርበራ ወደብ ቅርብ መሆኑ፣ አካባቢው ላይ ያለው የጥሬ ዕቃ ክምችት ጥራትና ብዛት እንዲሁም ከወደብ ጋር የሚገናኝ የባቡር መስመር መኖሩ ተመራጭ አድርጎታል ብለዋል።




Read 1760 times