Saturday, 15 April 2023 20:09

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

Written by 
Rate this item
(0 votes)

እስቲ ስለ ሞት እናውጋ


አቈልቊዬ ፡ ባይ ፡ መሬቱን ፡
ቈስሎ ፡ አገኘሁት ፡ እግሬን ፡
ምን ፡ አሳዘነኝ ፡ ለእግሬ ፡ ቊስል ፡
ስሄድ ፡ እኖር ፡ ይመስል፡፡
(ከብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል


ሞት በስሙ ኗሪ ነው፡፡ ሶምሶን ሹሩባው ላይ ሀይል እንዳለው ሁሉ ሞትም ሀይሉ ስሙ ላይ ነው፡፡ ደህና ስም አጥፊ አጥቶ ይህ ሁሉ ዘመን ፋነነብን እንጂ፡፡ አንዳንድ ዘመን አለ ሞት ስሙ የሚገንበት፡፡ ሞት ስሙ ሲገን ለሞት የብልፅግና ወቅት ነው፡፡ ይሄንንም የኛን ዘመን የሞት የልምላሜ ዘመን ነው እላለሁ፡፡ ከተፈጥሮ ግብሩ በዘለለ በሰዎችና በተፈጥሮ ክስተቶች እየታገዘ ስሙን በየሜዳው የፃፈበት ለሰው የመከራ፣ ለሞት የተድላ ወቅት ነው፡፡ ሞትን መረሳት እንደሚገድለው እናምናለን፡፡ ምክንያቱም በስሙ ያለ ነዋ፡፡ ካልተጠራ ይሞታል፡፡
የዚህ ፅሑፍ አላማ፣ ሞት ቅጥራችንን እየዞረው ከሚኖር ከዚህ ዘመን ሰው ጋር፣ እንደው ሞታችን እርግጥ ቢሆን እንኳ፣ ሞትን እንዴት ባለ መንገድ ነው ማስተናገድ ያለብን የሚለው ላይ ለመምከር ነው፡፡ መቼም ከላይ የገባንባት መተከዣ መዲና ሳትገልጠን አትቀርም የሚል እምነት አለን፡፡አንድ እየተባለለት ነው አጥርም የሚወድቅ፣ እናም፣ እስኪ ሞትን ለመጣል ባንችል ለመነቅነቅ አንዳንድ ጉዳዮችን እንይ፡፡
ፈራና አሁንስ፣ ፈራን አቦ! ፈረንጆቹ አስቦኩን፡፡ እንዴት ያሉ ውለታ ቢሶች ሆነዋል አንተ፣ A living dog is better than a dead lion. ከሞትክ አትረባም ማለታቸው ነው አይደል? ቁርጣችንን ንገሩን እንጂ ጎበዝ! ይሄ በአንበሳ የሰማነው ጉዳይ ሰውም ላይ ይሰራ ይሆን? ከሞተው ሰውስ ድመቱ ትሻላለች፣ ቢያንስ ከአዋኪ አይጥ ታሳርፋለች ማለት ይሆን? ጉርብትናውስ? ፍቅሩስ? ፅዋውስ በአንድ ሽክና አፍ ገጥመን የጠጣነው? ሞት ሲመጣ ሁሉ ገለባ ነው ማለት ነው? በቃ በቃ ሁሉ እንዲሁ ባክኖ ቀሪ ነው? ይህ ማለት አንበሶቹ የታሪክ ጀግኖቻችን ውኃ በላቸው ማለት ነው? ወይስ ለነሱ ሲሆን የትርጉም ማሻሻያ እናደርጋለን? ኸረ ፈራን ጎበዝ! ኸረ የዚህን የሞት ነገር አንድ በለን ክንዴዋ!
አንድ!
ሞት የእግዜር እንግዳ ነው፡፡ ሰው ደግሞ በስነ ፍጥረት ባህሪው እንግድነት ስላለበት በእንግዳ የሚጨክን አንጀት የለውም፡፡ (እንስሳት ምድር ላይ በመንፈላሰስ በአምስት ቀን ይቀድሙን የለም ወይ፣ ያ ማለትስ የእንስሳት ሀገር ሰው ነን ማለት አይደለም ወይ፣ ነው እንጂ ጎበዝ እየተማመንን)
አያ ሞት እንግዳ ነው ብለናል፡፡ በር ይቆምና ‹‹ የመሸበት የእግዜር እንግዳ ›› ይላል፡፡ አቤት ድምፁ እንዴት ያስፈራል፡፡ ፍርሃት ደግሞ ሞት የሚገባበት ቀዳዳ ነው፡፡ ሰው ይሄን ሲሰማ፣ አንድም በፍርሃት ሁለትም በብድር መላሽነት በር ይከፍታል፡፡  ሞት ይገባል፡፡ ሲገባ ያኔ የሞት እንግድነት ያበቃል፡፡ ምክንያቱም ዐይን ያወጣ ባለጌ ነዋ፡፡ ሰዎች ሆይ ሞትን ከደጅ መልሱት፡፡ በራፋችሁ ቆሞ ሲለምን እንዲህ በሉት፣
  ‹‹… ቦታውን ሁሉ ሕይወት ሞልቶታል፣ ለሞት የሚሆን ስርፋ የለም ››
ፃድቁ ላዖ ሱም ረቡዕ በሚፀለይ ውዳሴው ይህንኑ ነው ያለው (መቼም ስሙ ሲነሳበት እንዴት ብሽቅ እንደሚል፣ አያ ሞት)
  ‹‹… He who knows how to live can walk abroad
Without fear of rhinoceroses or tiger.
He will not be wounded in battle.
For in him rhinoceroses can find no place to thrust their horn,
Tigers no place to use their claws,
And weapons no place to pierce.
Why is this so?
ምክንያቱም፣ He has no place for death to enter. ››
ከበር የመለስነው ሞት፣ በር ገንጥዬ እገባለሁ ካለስ አንልም? ካለማ አንድም ዘራፍ ብሎ መነሳት አንድም ከነመኖሩ መርሳት፡፡ ዘራፉ ይቆየንና ከነመኖሩ መርሳት ይቻላል ወይ? የሚለውን እንይ፡፡ the denial of death ስልታዊ ማፈግፈግ ነው፡፡ ልክ ጲላጦስ እጁን ታጥቦ ኢየሱስን እንዳስገደለው ያለ፡፡ ለሞት ጀርባ መስጠት፡፡ እኔ ጋ አይደለም የመጣው አልያም እኔ የለሁበትም ብሎ ማለት፡፡
የሞትን ሕልውና አለማወቅ እና ሞትን መካድ ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡ እስኪ በተናጠል ለማየት እንሞክር፡፡ አንደኛ፣ ሞት ብሎ ነገር መኖሩን ጭርሹን አለማወቅን አስመልክቶ ፍሩውድ ያለውን እናንሳ፣ ፍሩውድ ያለው ይህን ነው፡፡
‹‹… እንዲያውም ልንገርህ፣ The conscious ጭርሹኑ does not know death or time, in man’s physiochemical, inner organic recesses he feels immortal. ››
ይህ ማለት፣ ደጅ ቆሞ ‹‹ ቤቶች ›› ሲል፡፡
  ‹‹ ማን ነው? ›› (ማለት፣ ተነስተህ ከመክፈትህ በፊት፡፡)
  ‹‹ እኔ ነኝ ›› (ስሙን አይናገርም? ሌባ)
  ‹‹ አንተ ማን ነህ? ስም የለህም? ›› (ጎበዝ! ደግ አደረግህ)
  ‹‹ ሞት ነኝ ››
      ‹‹ ሞት ምንድን ነው? አውሬ ነው? ሰው ነው? ካለዛሬም ስምህን ሰምቼው አላውቅ›› ብሎ ማለትን ይመስላል፡፡
ሞትን መካድ ላይ እንምጣ፣ ለዚህ ማሳያ ተመሳሳይ ምሳሌ እንጠቀም፡፡
  ሞት ደጅ ይቆምና በር እየቀጠቀጠ ‹‹ቤቶች›› ሲል፡፡
  ‹‹እዚህ አይደለም የተንኳኳው፣ ጎረቤት ካለ ቤት ነው›› ብሎ በማሰብ ምንም እንደሌለበት ሰው ፊትን ወደ ግድግዳ መልሶ ለጥ ማለት፡፡ ሞትን የምንክደው መኖሩን ካወቅን በኋላ ነው፡፡ እዚህ ጋር ነው ከፍሩውድ ጋር ልዩነት የሚፈጠረው፡፡
ሞት ባዳ ነው፡፡ ሞት ከሰው ወገን ስላልሆነ፣ ለሰው አይራራም፡፡ ብላቴን ጌታ ማህተመ ስላሴ ወልደ መስቀልስ ምን አሉ የሞትን ነገር ታዝበው ‹‹… የሰው እንግዳ ሲመጣ፣ ግባ ይሉታል ብላ ጠጣ፣ ያንት መላክተኛ የመጣለት፤ ይዋል ይደር የለበት ›› ሞት ክፉ እንግዳ ስለሆነ ውለታውን በክፋት ነው የሚመልሰው፡፡ እርሱ ከፍቶ ባይሆን እንኳ፣ ውጤቱ ለእኛ ስለሚከፋ እጁ እስኪገነጠል ቢያንኳኳ እንኳ፣ የኛ በር እንዳልተንኳኳ ማመን እስከሚቻለን ድረስ መፅናትን መለማመድ፡፡ እውነት ማን ይሙት! የትኛዋ ልጃገረድ ናት የምጥ ስቃይን ከወላድ የምትጋራ? ስሜቱን፡፡ ምጥ እንዲያም ብታውቅ እንጂ ሕመሙ አይሰማትም፡፡ ሞትስ እንደ ውልደት አይደለም ወይ? ሕመሙን ሆነ ደስታውን እስካልቀመስነው መች ይሰማናል፡፡ አይሰማንም፡፡ ሰውም እንዲሁ ነው፤ ስለ ሞት ያለው ግምት፡፡ ከጎረቤቱ ጥል ባይሆን እንኳ ሞትን በማሻገር፣ አንዱ ቀሪና ቀባሪ እርሱ እንደሆነ ይሰማዋል፡፡
ጋሽ ቤከርም ይህንኑ ነው ያሉት፣
‹‹… at heart one doesn’t feel that he will die, he only feels sorry for the man next to him. ››
ሌላው ጥያቄ፣ እንዴት ነው ሞት ላይ ዘራፍ የሚሉት? እና፣ ዘራፍ ያሉት ጠላት በዘራፍ አልበረግግ ቢልና ይልቁን ዘሎ ቢያንቅ ምን ያደርጋሉ? የሚለው ነው፡፡
ነገሩን ሁለት ቦታ ከፍለን ለማየት እንሞክር፡፡
ታግሎ ማሸነፍና፣ ታግሎ መሸነፍ፡፡ ታግሎ መሸነፍን፣ በታሪክም በዓይናችን ብሌንም ዐይተን በተማርነው መሰረት የሁላችን ሊባል ቁጥሮች ለጎደለን ለ99ኞቹ ትተን ፣ ታግሎ ማሸነፍን ለአንዱ እንሰጣልን፡፡
ዘጠኝ ሞት መጣ ሲሉት፣ አንዱን ግባ በሉት አላ፡፡
አንዱ ማን ነው?
እዚህ ጋ ጋሽ ቤከርን በድጋሚ ወደ’ዚህ ለመጥራት እንገደዳለን (ለማይረባ ነገር አመላለስንዎት አይደል ጋሼ… ይቅርታ)
‹‹ The hero was the man who could go into the spirit world, the world of dead, and return alive. ››
ሆድህ ገብቼ ደም ሳይነካኝ እወጣለሁ እንደማለት ያለ ነው ነገሩ፡፡ ይሄ ከሞት ግብግብ እግረ መንገዱን ሽልማት የሚገኝበት ነው፡፡ ሽልማቱ ደግሞ ጀግንነት ነው፡፡ ሞት ያልተፈራበት ዘመን አለ ቢሉ፣ ሰው አልነበረም ያኔ ብለን ለመጠየቅ እንደፍራለን፡፡ ስፓርታ ልጆቿን ለክብር ሞት መውለዷስ? ብትሉ፣ ሰው ሕይወቱን በትፍስህት ለሞት አያጫትም፣ ቢሳካለት እንኳ ሞትን ተሻግሮ ማየት አልቻለም፤ እንላለን፡፡ ሁሉም ሕይወት ሞት ፊት ኢምንት ነው፡፡ ያንን ማወቅ ለፈለገ ለእገሌ እሞታለሁ ያለ ጀግና አንገት ላይ ሰይፍ ያስደግፍ፡፡ ያኔ ጉራውና ትምክህቱ ለነፍሱ ቦታ ትለቃለች፣ ነፍስ ደግሞ ፈሪ ናት፡፡ ነፍስ የታሰረችበት ግድግዳ ነው ስጋ ማለት፡፡ ነፍስ ስጋን መሽጋ የምትኖር የሌላ ዓለም ዜጋ ናት፡፡ ድንገት የዜግነት ማጣሪያ ሲደረግ ትበረግጋለች፣ በስጋው እንጂ በነፍሱ ጀግና የሰው ዘር የለም፡፡ እንዲያው ልቡ ጀግኖለት እንደ ስፓርታውያኑ ወጠጤዎች ሞትን በድፍረት ቢጋፈጥ እንኳ ተመልሶ ገድሉን ለማፃፍ የሚሆን እድል አላገኘም፡፡ ካርል ዩንግ ይሄን የጀግንነት ጉዳይ ስነልቦናዊ ፍካሬ ይሰጠዋል፡፡ ነገር ግን ጉዳዩ ሰው የራሱን ሞት ከማሸነፍ በዘለለ በሌሎች (የሞት አገልጋይ ተደርገው በተመሰሉ monsters and force of evil) ላይ በመዝመትና እነሱን በማሸነፍ ጭምር ነው ይለናል፡፡ ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ አይደል ተረቱስ፣ እሱን ባይሆን መልዕክተኞቹን በመጠፍጠፍ የሰው ልጅ ንቀቱን አሳይቷል፡፡ ይሄን እምነት ለማሳየት በየጫካው እየዞሩ፣… እነማ አትሉም?
‹‹ እነ ሄርኩለስ፣ እነ ዳዊት፣ እነ ጊዮርጊስ፣ ጊለጋሜሽ፣ ሲጉርድ፣ ዘንዶና አንበሳ በጥፊና በቴስታ ሲዘርሩ፣… ክርስቶስ መጣና ታዲያ፣…
… አያይ እንደዚያ አይደለም፣… አንዱና ትልቁ (ጉልቤው) ሌላውን (ደካማውን) እየበላና እየገደለ መኖር ሥርዓተ ተፈጥሮ ነው፡፡ ማሸነፍ ያለብን ሞትን ነው፡፡ don’t kill the messenger፣… የቱ ሞኝ ነው ኮምፒውተሩን ቫይረስ ሲያጠቃው፣ ቫይረሱን ፀረ- ቫይረስ በማስረጨት ፈንታ አውጥቶ የሚወረውር? የቷስ ቂል ናት ስንት ፈዋሽ ፀበል (ቡሩክ ካህን) ባለበት ሀገር ቤቴ ሰይጣን ገባ ብላ ቤቷን ጥላ ብርር የምትል? ይሄ ሞኝነት ነው፡፡ ሞት ግድግዳ ነው፡፡ ግድግዳውን ማፍረስና መተላለፊያ ማበጀት ነው ያለብን፣ እኔ ያንን ነው ያደረግሁት፡፡ ››
ያለውን አደረገ፡፡ ይሄን ጀግንነት ያለተቀናቃኝ በምልዓት የተቆጣጠረው ኢየሱስ ብቻ ነው፡፡ ኢየሱስ የሰው ልጆች ጀግና ነው፡፡ ኢየሱስ ሞት ላይ ተረማምዶ ከማለፍ በላይ የጀግንነቱን ዜና በራሱ ጆሮ ለመስማት ችሏል፡፡ ከኢየሱስ ትንሳዔ ወዲህ ሞት እምብዛም ያልተፈራበት ዘመን ሆነ፡፡ ሰዎች እየሞቱ እያየ እንኳ ከሞት ባሻገር ስላለው ሕይወት ማወቁ ሰውን አፅናናው፡፡
ሞት ምን አለ ይሄን ጊዜ?
  ‹‹ ተበላሁ! ››
ሞት ይሄን ማለቱ በሀገር ተሰማ፡፡ ሀገሬው ሞት ይሄን ማለቱን ሲሰማ የድል ድግስ ደገሰ፡፡ (ኸረ ዘፈን ያወጡም አሉ አሉ፣… ሞትዬ ሞትነት፣ ሞት’ለም ሞቱካ፣… አሃሃሃ፣… እንዲህ ያለው ፈሪ፣ ልፍስፍስ ነህ ለካ፣… ሆሆይ ናና…) በየድግሱ ሞት ላይ ተቅራራ፡፡ የኢየሱስ ትንሳዔ ለሰዎች፣ ሞት ማለት ከገቡበት የማይወጡበት እንዳልሆነ መልመጃ ሆነ፡፡ ይሄን ጊዜ ጋሽ ቤከር ሰልፍ አሳብሮ ገባና እንዲህ አላ፣
‹‹ when we see a man bravely facing his own extinction we rehearse the greatest victory we can imagine. ››
ሰው በየመቅደሱ፣ በየእድሩ፣ በየዛፉ ጥላ፣ በየጨብሲ ቤቱ፣ ጠረጴዛ በጡጫ እየመታ ጥርሱን እያፋፋቀ ተማማለ፡፡ አንዱ ጎበዝ ብድግ ይልና መሃላውን ይመራል ሌላው እየተከተለ እሱ ያለውን ይላል፡፡
‹‹ ከእንግዲህ በኋላ፣… ሞት ሆይ እግር ብላ፣… If I am like my all powerful father, I will not die. ››
ኦስትሪያዊው ዶክተር ዊልካልም ሪችም ይሄን መሃላ Character armor ብሎ ጠራው፡፡
እንበልና (በእንበልና ገብተው የእውነትን ቦታ ያገኙ ስንቶች እንዳሉ መረጃው ቢኖረንም) ቅድመ ክርስቶስ የነበረው የሰው ልጅ ሞትን ሲፈራው የነበረው፣ ሞት የሙከራ ዕድል ስለማይሰጥ ነው እንበል፡፡
በምሳሌ እንየው፡- ከ’ለታት በአንዱ ቀን፣… እንዲያው አንዱ ጥጋብ ልቡን ንፍት ያደረገው ወጠጤ፣ በሰላም ኑሮውን እየኖረ ካለበት ድንገት ብድግ ብሎ የሞትን ነገር ቢያጣጥል፣ አጣጥሎም ባይቀርና ካልገጠምኩት ሞቼ ልገኝ ቢል፡፡
‹‹ የታባቱንስና ደግሞ! አሁንስ ለማንም ጠቋራ (መቼም ፈረንጅ ይመስላል እንደማትሉኝ) መንቦቅቦቅ ሰለቸኝ ››
ብሎ ቢገጥመውና ሞት በአንድ ቃሪያ ጥፊ ጥሎት ያንን የመሰለ መኳንንት ሙትት ብሎ ቢቀር፡፡ እሱኮ ሀሳቡ የነበረው፣ ሞት ቢያሸንፈው ከንግዲህ ኋላ አንገቱን ሰብሮ ሊኖር፣ እንደሁ አድባር ቀንታው ሞትን ቢያሸንፈው ጊዮርጊስ እንደረገጠው ድራጎን ያለ ምስል፣ ሞትን ከእግሩ ስር ረግጦ የሚያሳይ ሀውልት አደባባይ አቁሞ ለመኖር ነበር፡፡ ሞት ግን አሰራሩ እንደዚያ አይደለም፣ ከተጣሉት ለእርቅና ለሽምግልና የሚሆን ጊዜ አይሰጥም፡፡ እንዲያው ዝግት ያለ ነገር ነው፡፡ ይህ እንዴት ማለት ነው? ለነገ የሚሆን እቅድ ይዘህ ከአልጋ ትወጣና ነገን ብትጠብቅ ብትጠብቅ ሳይመጣ ቢቀር፣ ይሄም በቀላል እንግልጣርኛ
‹‹ any schoolboy can do experiments in the physics laboratory to test various scientific hypothesis. But man, because he has only one life to live, cannot conduct experiments to test whether to follow his passion [compassion] or not. ››
ኩንዴራ ከላይ ያለንን ሰምተን ‹‹ ልክ ብለሃል ›› ብለን ብዙም ሳንርቅ ሌላ አጣብቂኝ ውስጥ እንገባለን፡፡ አጣብቂኙ የመጣው ከታሪክ ነው፡፡
ቅድመ ክርስቶስ ያለው የሰው ልጅ ሞት የመጨረሻ አለመሆኑ ጠፍቶት ነው? የሚል፡፡ ‹‹እህሳ?›› ስንል፡፡ ነገሩ ወዲህ ነው ብሎ ይጀምራል አጣብቂኙ፣
‹‹ ዛሬ አይምሰላችሁ፣ ጥንት የሄለናውያንን ፍልስፍና የሚያራምዱ የዜኖ ደቀመዛሙርት የሆኑት ስቶይክሶች፣ ቡድሂስቶች፣ ሂንዱሂስቶች ሁሉ ሳይቀር ሞት ለሰው ልጅ የመጨረሻው እንዳልሆነና Infinite (የሰው ልጅ የቁጥር እውቀቱ አገልግሎት እስከሚያጣበት) ጊዜ ተደጋግሞ ተወላጅ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ ››
የአጣብቂኙን ነገር ችላ ለማለት ‹‹ የድሮ ሰው ምኑ ይታመናል ›› ብለን ልናጣጥል ስንጀምር፣ የድሮ ሰዎች አምላክ ከድህረ ክርስቶስ ሰዎች ነብይ አስነሳብና፡፡ እንደ ኒቼ ባሉ ባለ ጎፈሬ ሙስታሾች ስል ምላስ ሊያስገርፈን፡፡ ኒቼ ተነሳ ያንን ዞማ ፅዕሙን እያስተኛ፣
‹‹ የድሮ ሰው ምናምን እያልክ ነገር ከምታጣጥል ካሽ አውጣና መፅሐፌን ግዛኝ፣ እዛ ላይ ስለ Eternal recurrence የፃፍኩትን ታገኛለህ፣…››
ታዲያ እንዲህ ከሆነ ነገሩ የዛን ዘመን ሰው ሞትን ለምን ፈራ? ተብሎ ሲጠየቅ፣ እኛም መላምትን ለፈጠረ አምላክ ገለተ ጢሎሲ! እያልን መመልመት እንጀምራለን፡፡
መላምት 1፡- በዚህኛው ዓለም ያስኮረፉት ሞት (የድሮው ሞት ደግሞ ተበቃይ ነው) በሌላኛው ሕይወት ሲያገኛቸው መከራቸውን እንዳያበዛው በመስጋት፡፡ ማን ያውቃል ሞትም የTalien principle ተከታይ እንደሆነ? የናቀውን በንቀት፣ የተሳፈጠውን በስፍጠት የሚመልስ እንደሆን? ሞት ሲሳፈጥ ደግሞ አሟሟት በማክበድ ነው ሲባል ሰምተናል፣ ሲያደርግ ባናይም፡፡
መላምት 2፡- ድግግሙ ቅልሽልሽ ስላለው፡፡ አልያም ምን የመሰለው ከበርቴ አሳማ ሆኜ ብመለስስ ከሚል ከንቱ ስጋት?
ደግሞ ሞትን መፍሪያ ምክንያት ጠፍቶ ነው? እንዲያው ስታደክሙን እንጂ፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ታዲያ ሰው ምን በጀው? ብለን ከአፋችን ሳንጨርስ አጋፋሪሻ በቅሎአቸውን እየኮለኮሉ ከተፍ፡፡ በግራ ይሁን በቀኝ እጃቸው መፈክር ይዘዋል፡፡
  ‹‹ ሞትን ሽሹት! ›› የሚል የተፃፈበት፡፡
ጨዋታን ጨዋታ አይደል የሚያነሳው፣ ለመሆኑ አጋፋሪ ሞትን ሲሸሹ ነው ሲያባርሩ የሰነበቱት? ብሎ መጠየቅ አይከፋም፡፡ ምክንያቱም ሞት ሁሉ ሀገሩ ነዋ፡፡ ይልቅ አጋፋሪ በፍርሃትም ይሁን በግብታዊነት ሞትን በንቃት ይከታተሉት ነበር፡፡ ንቃታቸው ሞትን ከጉያቸው አልለየውም፡፡ ባሰቡት ቁጥር ሞት ቅርባቸው እንዲገኝ ሆነ፡፡ ለመሸሽ ባሉት ልክ እየቀረቡት በአንፃሩ ሞት ያለቀጠሮ እንዳያስቱት ብሎ ሲሸሽ እንደኖረ አድርገንም ማሰብ ይገባል፡፡ ይባስ ብለን፣ አጋፋሪ ሞትን ሳይሆን ሙታንን ነበር ሲሸሹ የነበሩት ብንልስ? ለምን አንልም ለምለም አንደበት እስካለን፡፡
እናም በስተመጨረሻ፣… ጋሽ ኩንዴራ The stupidity of people comes from having an answer for everything ብሎ እፍኝ ስላሳከለን መልስ ኪሳችን ቢኖርም ታላቅ የመታዘዝ ባሕል እድሜው እንዲረዝም ሲባል ጠይቀን እንወጣለን፡፡
1.  ከሚከተሉት ምርጫዎች መካከል እንደው ይሄ ለኔ ይበጀኛል ያላችሁት ላይ አክብቡ?
  ሀ. ቤቴን በሕይወት ሞልቼ ለሞት የሚሆን ቦታ ማሳጣት
  ለ. ሞትን ታግዬ ማሸነፍ
  ሐ. ከነመኖሩ ርስት አድርጌው መኖር
  መ. እንደ አጋፋሪ መሸሽ
  ሠ. መልሱ እዚህ የለም
  ረ. እዚህ ከሌለ የት ነው?
(በስተመጨረሻም፣ በእኚህ ከላይ በጥቂቱም ቢሆን በጠቀስናቸው ግለሰቦች (በላዖ ዙ፣ በኤርነስት ቤከር፣ በፍሩውድና በአጋፋሪ) ሕይወት ውስጥ ስለተፈከረው ሞት ለመጨዋወት የያዝነውን የመንደርደሪያ ሀሳብ ዳግም የምንመለስበት ስለሚሆን፣ አትጥፉ ለማለት ነው፡፡)
                

Read 1258 times