Saturday, 08 April 2023 19:59

በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ

Written by  ሀይማኖትግርማይ ከኢሶግ
Rate this item
(1 Vote)

ከአንድ አነስተኛ መንደር አጠገብ ከፀሀይ፣ ዝናብ፣ ወንጀል እና ከእራስ ለመሸሸግ ሰዎች የሚጠጉት የደን ክምችት ይገኛል። ከደኑ ትይዩ ከአንድ ሰው በላይ በማታስጠልል ጎጆ ውስጥ እትዬ ጥላነሽ ተጠልለው ይኖራሉ። ለነገሩ ሌላ ሰው ላስጠልል ቢሉስ አይደለም ቤታቸውን የአከባቢውን ጠረን ማን ደፍሮ ይሞክረዋል። እትዬ ጥላነሽ “በእኔ የደረሰው ለጠላቴም አይስጠው” እያሉ ኣላፊ አግዳሚውን ከሩቅ ከመመልከት በቀር ለሚሰነዘሩባቸው የንቀት አይኖች እና ፀያፍ ንግግሮች ምላሽ አይሰጡም። በዚህ መሀል የሰው እንቅስቃሴ ቀነስ ሲል ዓለም ወደ ግራ እና ቀኝ እያማተረች፣ ዘንቢል አንጠልጥላ፣ ከአይኗ፣ እጇ እና እግሯ በስተቀር ሙሉ ሰውነቷን ተከናንባ፣ የሰውን አይን በፈጣን እርምጃ የምትቀዳደም ይመስል በቅጡ ቅርፅ ባልያዙ ድንጋዮች እየተደነቃቀፈች እትዬ ጥላነሽ ጋር ትመጣለች። የቤታቸው ደጃፍ ጋር እንደደረሰችም “እትዬ ጥላነሽ የሚቀመስ ነገር አምጥቼሎታለው” በማለት ከዘንቢሉ ውስጥ በፌስታል የተቋጠረ ምግብ ትሰጣቸዋለች። ከዛም ለአትሌቶች የሚደወለው ደውል የተደወለ ይመስል ዓለም በሩጫ ከአከባቢው ትሰወራለች።
የዓለም ሩጫ የሚካሄደው በአከባቢው ሰው መኖሩን ከጠረጠረች ብቻ ነው። ካልሆነ ግን ለተወሰኑ ደቂቃዎች ከእትዬ ጥላነሽ ጋር የንግግር ሩጫ ታደርጋለች። ትንሽ ጊዜ ሲኖራት ደግሞ እሷ ብቻ ሳትሆን እሳቸውም ይጫወታሉ። እሷ በመንደሩ ስለተፈጠሩ አዳዲስ ክስተቶች፤ እሳቸው ደግሞ ሰዎች ከመንደሩ ተሸሽገው በዛፎች ጥላ ስር ስለሚያከናውኗቸው ጉዳዮች። እሷ “እከሊት እና እከሌ እኮ ተለያዩ” እሳቸው “እሱ እንኳን ሰንበትበት ብሏል ከዛፎቹ ማዶ ከሌላ ሴት ጋር መታየት ከጀመረ” ተባባሉ። ዓለም ከተል አድርጋ “ታማ አልጋ ላይ ስትውል ነው የተዋት አሉ፤ ኧረ እንደውም የማይድን በሽታ ነው የያዛት ነው የሚባለው” አለች ድምፃን ዝቅ አድርጋ። እትዬ ጥላነሽ ምንም ምላሽ ሳይመልሱ እንደ ደራሽ ውሀ ከአይናቸው እንባ መፍሰስ ሲጀምር ወደ መጠለያቸው ገቡ። ንግግሯ ሌላ ሰው ሳይሆን እትዬ ጥላነሽ እንዳይሰሙት ተብሎ ድምፅ ዝቅ የሚደረግበት አይነት መሆኑ ትውስ አላት። እንዲሁም ካሰበችው ደቂቃዎች በላይ መቆየቷ እና የሰው እንቅስቃሴ መኖሩን ስታስተውል ሩጫዋን ተያያዘችው። የእትዬ ጥላነሽ እና የዓለም ትዕይንት የአንድ እና የሁለት ቀን አይደለም፤ የሁለት ዓመታት እንጂ።
እትዬ ጥላነሽ ከ2 ዓመት በፊት ከ13 ዓመት የትዳር ቆይታ በኋላ የፀሎታቸው ምላሽ በሆነው ልጅ ተባረኩ።
ነገር ግን ልጅ የወለዱበት ቀን እንደ እሳቸው ንግግር ቡራኬ ሳይሆን እርግማን ሆነባቸው። የወለዱት ልጅ በህይወት አልነበረም፤ ልጅ ከወለዱበት ቀን ጀምሮ ለ2 ዓመታት ታመሙ፤ በሽታቸው ሰው የሚያስታምመው ባለመሆኑ ሁሉም አገለላቸው፤ ባለቤታቸውም ልጁ የተወለደ ቀን ቀበቷቸውን ፈተው ከአንዱ ጥግ ወደ አንዱ ጥግ ሲንጎራደዱ ከታዩ በኋላ የገቡበት አልታወቀም። ክፉንም ደጉንም አብረው አሳልፈው ለ13 ዓመታት ከእትዬ ጥላነሽ ጋር በትዳር የኖሩት አቶ ዳኜ በህይወት ይኑሩ ወይም ይሙቱ ቁርጡ ሳይታወቅ የችግር ቀንበሩን ለእትዬ ጥላነሽ እንዳሸከሙ አመታት ተቆጠሩ። እንደ ማንኛውም ቀን ስአት፣ ደቂቃ እና ሰከንድ ያለው ይህ እለት ለእትዬ ጥላነሽ ግን ተባዝቶ የ2 ዓመታት በሽታ ሆነባቸው። ከስጋዊ በሽታቸው ይልቅ መንፈሳቸውን ጠዘጠዛቸው።
ከተለመዱት ቀናት በአንዱ የተለመደውን በሽታቸውን እያስተናገዱ ባሉበት አለም እንደተለመደው እየተሯሯጠች መጣች። እትዬ ጥላነሽ ግን እንዳስለመዷት ደጃፍ ወጥተው ሊያጫውቷት ይቅርና ለጥሪዋ ምላሽ ለመስጠት ሰውነታቸው ከዳቸው። አለም እንደ ከዚህ ቀደም ፊቷን ሳትከናነብ እና ከወትሮው በተለየ መልኩ ወደ ጎጇቸው ይበልጥ ተጠግታ እየደጋገመች “እትዬ ጥላነሽ፤ እትዬ ጥላነሽ” አለች። ቀጠል አድርጋም “ዛሬ የሠርግ ምግብ ነው ያመጣሁሎት፤ ምን የመሰለ ሰርግ መሰሎት፤ የቀረ የመንደሩ ሰው የለም፤ እኔ ግን ምግቡን ይዤ ስሮጥ እርሶ ጋር መጣሁ፤ እንደዚህ አይነት አጋጣሚ በዓመት አንዴም አይገኝ፤ የማወራሎት ነገር ብዛቱ” ካለች በኋላ “አይይይይ.... ለብቻዬ ነው የማወራው፤ ምናልባት ዛሬ የማልመጣ መስሏቸው ደጀሰላም ሄደው ቁራሽ እየለመኑ ይሆን፤ አያያያይ.... ዛሬ ደግሞ እሳቸው ሳይኖሩ ቤቱ ብቻ ጠረኑ አይጣል ነው፤ ይህ ፌስቱላ የሚሉት እንዴት ያለ መረገም ነው ባካችሁ” በማለት ተናገረች። እትዬ ጥላነሽ በስቃይ እና በሰመመን ውስጥ ሆነው ንግግሯን እየሰሙ ቢቆዩም ምላሽ ሳይሰጧት እራሳቸውን ስተው ፍራሻቸው ላይ ወደቁ።......... በቀጣይ እትም ይቀጥላል!
በዓለም የጤና ድርጅት መረጃ መሰረት በዓለም አቀፍ ደረጃ በአንድ ዓመት ውስጥ ከ50 እስከ 100ሺ የሚሆኑ እናቶች በወሊድ ምክንያት ለሚፈጠር ፊስቱላ ይጋለጣሉ። በዲላ ዩኒቨርስቲ ህይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ጥናት እና ምርምር የሚያደርጉት (አናቶሚስት) መምህር ቸርነት ሙሉጌታ እንደተናገሩት ፊስቱላ ማለት በሰውነት ክፍል ውስጥ የሚፈጠር ቀዳዳ ነው። ይህም በተፈጥሮ ሳይሆን በተለያየ መክንያት ከጊዜ በኋላ የሚያጋጥም ነው። የህክምና ባለሙያው “መገናኘት የሌለባቸው የሰውነት ክፍሎች በቀዳዳ አማካኝነት ሲገናኙ ፊስቱላ ተፈጠረ ይባላል” በማለት ተናግረዋል።
 በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ የሚከሰተው በምጥ ወቅት ሲሆን በቤት ውስጥ በሚወልዱ እናቶች ላይ በብዛት ይስተዋላል። በሽንት ቧንቧ እና በማህፀን በር ወይም በማህፀን በር እና በፊንጢጣ መካከል እንዲሁም በሁለቱም ቦታዎች ላይ ቀዳዳ ሊፈጠር ይችላል። ቀዳዳው መገናኘት የሌለባቸው የሰውነት ክፍሎች በማገናኘት ስርአቱን የሚያዛባ ነው።
በወሊድ ወቅት የሚፈጠር ፊስቱላ መንስኤ(ምክንያት)፤የሚወለደው ልጅ የራስ ቅል(ጭንቅላት) ትልቅ መሆን፤የሚወለደው ልጅ ጭንቅላት እና የእናት የዳሌ አጥንት አለመመጣጠን፤ ቤት ውስጥ [ከህክምና ተቋም ውጪ] መውለድ፤ በቀዶጥገና ልጅ ለመውለድ አገልግሎቱን አለማግኘት ወይም የቀዶ ጥገና አገልግሎት በማይገኝበት ስፍራ መውለድ፤በልጅነት ማለትም ያለ እድሜ ጋብቻ በመመስረት [ሰውነት የመውለድ አቅም ሳይኖረው] መውለድ በምክንያትነት ከሚጠቀሱ መካከል ናቸው፡፡
 “እናቶች በወሊድ ወቅት ለፊስቱላ ከተጋለጡ በኋላ ለማገገም (ከበሽታው ለመዳን) ምን ያህል ጊዜ ይፈጅባቸዋል” በሚል አዲስ አበባ በሚገኘው ሀምሊን የፊስቱላ ሆስፒታል መምህር ቸርነት ጥናት አድርገዋል። በጥናቱ ተካታች የሆኑት በ6 ዓመታት ውስጥ አዲስ አበባ ሀምሊን ሆስፒታሉ የታከሙ 434 እናቶች ናቸው። በጥናቱ የተካተቱት እናቶች ከ16 እስከ 75 ዓመት የእድሜ ክልል ውስጥ ይገኛሉ። 23 በመቶ የሚሆኑት እነዚህ እናቶች በአማካይ ከ11 እስከ 15 እድሜ ላይ ትዳር መስርተዋል።
በጥናቱ ውጤት መሰረት በወሊድ ወቅት ከሚፈጠር ፊስቱላ ለማገገም ማለትም ከበሽታው ለመዳን የ4 ሳምንት(1ወር) ጊዜ ይወስዳል። የጊዜው እርዝማኔ የሚያካትተው አንዲት እናት የፊስቱላ ቀዶጥገና ከተደረገላት ቀን ጀምሮ ከሆስፒታሉ አገግማ እስከወጣችበት እለት ድረስ ነው።
በመምህር ቸርነት ጥናት ውጤት መሰረት 72በመቶ የሚሆኑት እናቶች ናቸው ከፊስቱላ ማገገም የቻሉት። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በዓለም አቀፍ ደረጃ ከ81 በመቶ በላይ የሚሆኑ እናቶች በወሊድ ወቅት ከሚፈጠረው የፊስቱላ በሽታ አገግመዋል። “ወደ ህክምና ተቋም በቶሎ ሄዳ የታከመች እናት ቶሎ የመዳን እድል አላት” በማለት የህክምና ባለሙያው ተናግረዋል።  መምህር ቸርነት አክለውም  ፊስቱላ ተባብሶ ብዙ ችግሮችን ከማስከተሉ አስቀድሞ እናቶች ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ መልዕክት አስተላልፈዋል።

Read 632 times