Saturday, 08 April 2023 19:32

የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ የሚከውን መተግበሪያ ሥራ ሊጀምር ነው

Written by 
Rate this item
(0 votes)

መተግበሪያው ሙስናንና ህገወጥ አሰራርን ይቀርፋል ተብሏል


ቲዮስ ቴክኒሎጂ ከአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮና ከአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር፣ የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራን የሚያከናውን አዲስ ቴክኖሎጂ ሥራ ሊጀምር ነው፡፡
ተቋማቱ ለ5 ዓመት በጋራ ሊሰሩ የሚችሉበትን ሥምምነት ባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 26 ቀን 2015 ዓ.ም በሳፋየር አዲስ ሆቴል ተፈራርመዋል፡፡
በፊርማ ስነ ሥርዓቱ ላይ የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፍቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ሥራ አሥኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ፣ የትዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ፕሬዚዳንት አቶ ሀይሉ ገረሱና ሌሎችም እንግዶች ተገኝተዋል፡፡የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራን ቴክኖሎጂው በውጭና በሀገር ውስጥ ከፍተኛ ባለሙያዎች የበለፀገ ዘመናዊ መተግበሪያ ሲሆን የተሽከርካሪ ቴክኒክ ምርመራ ከሶስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ጠብቆ ውጤቱን ለማእከላዊ የመረጃ ቋት እንደሚያቀብል የቲዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮሰ አጥናፉ አብራርተው ይህም ሙሰኝነትንና ህገ-ወጥ አሰራርን በእጅጉ ከመቀነስ አኳያ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡
እስከ ዛሬ የነበረውን የቴክኒክ ምርመራ ክፍተት አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት የተሽከርካሪና አሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፍሬው ደምሴ፤ ተሽከርካሪዎች በምርመራ ተቋማት የምርመራ ሂደት ሳያልፉ፣ ህገ ወጥ ቦሎ እየወሰዱ መሆናቸውን አብራርተው፣ ይህም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱና የተሽከርካሪ ምርመራ ድርጅቶች ሊያገኙ የሚገባቸውን ገቢ በማሳጣት በተቋማቱም በአገር ኢኮኖሚም ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ሲፈጥሩ ቆይተዋል ብለዋል፡፡ ኃላፊው አክለውም፤ ደህንነታቸውና ጤንነታቸው ያልተረጋገጡ ተሽከርካሪዎች በስራ ላይ እየዋሉ በህይወትና በንብረት ላይ ከፍተኛ ጥፋት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመው፤ ቲዮስ ቴክኖሎጂ ያበለፀገው አዲስ  መተግበሪያ እነዚህን ሁሉ ተግዳሮቶች ከመቅረፍ አኳያ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው አስታውቀዋል፡፡
‹‹ ቴክኖሎጂውን ያበለፀግነው ትራንስፖርቱን ከማዘመን ፣ ህገ ወጥ አሰራርና ሙስናን ከማስቀረትና በህይወትና በንብረት ላይ የሚደርሰውን ጥፋት ከማስቀረት አኳያ አስበን ነው” ያሉት ደግሞ የቲዮስ ቴክኖሎጂ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ቴዎድሮስ አጥናፉ ሲሆኑ ፤ መተግበሪያው በአዲስ አበባ ከሚገኙ 60 የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት በ15ቱ ላይ የሙከራ ስራ ተሰርቶበት ውጤታማነቱ ተረጋገረጧል  ብለዋል፡፡
እንደ አዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ መረጃ የአዲስ አበባ (አ.አ)፣ የኢትዮጵያ (ኢቲ) እና የኮር ዲፕሎማቲክ (CD) ሰሌዳ ያላቸው ከ650 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች በአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ተመዝግበው የሚገኙ ሲሆን፤ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ330 ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎች ተመርምረው ቦሎ መውሰዳቸውንና እስከ በጀት ዓመቱ መጨረሻ ተመርምረው ቦሎ የሚወስዱ ተሽከርካሪዎች ቁጥር 450 ሺህ ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ በዕለቱ ተገልፃል፡፡

Read 1640 times